>
5:18 pm - Friday June 15, 5066

አብይ አህመድና የሳፕራሙራት ኒያዞቭ መፀሐፍት...!!! (ካሳ አበሳው)

አብይ አህመድና የሳፕራሙራት ኒያዞቭ መፀሐፍት…!!!

ካሳ አበሳው

* የአብይን “መደመር”  በየትምህርት ቤቱ እንደገባ ሰምተናል፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የአብይን መፀሐፍ ቤት ለቤት መጋታችን አይቀርም፣ ሌላ ፓርቲ የለም ያለን የ’መደመር’ መፀሐፍ ደራሲ  ነገ ጠዋት ተነስቶ ሌላ ሀሳብ የለም ሌሎች መፀሐፍቶችን አቃጥሉ እንደማይለን ማስተማመኛ የለንም…!
 
ቱርኬሚኒስታን የምትባል ሀገር ሳፕራሙራት ኒያዞቭ የሚባል እብድ ገጥሟት ነበር፣ የሶቭየት ህብረት አካል እያለች በዋና ጸሐፊነት (First Secretary) ለ6 ዓመት፣ ሶቭየት ህብረት ስትፈርስና ቱርኬሚኒስታን ሉአላዊ ሀገር ሁና ስትወጣ ለተጨማሪ 15 ዓመት በፕሬዝዳንትነት ነድቷታል፣
የሳፕራሙራት አንድ ጥሩ ባህሪ ግልጽነቱ ነው፣ “እኔ በህይወት እያለሁ ሌላ መሪ እንዳትጠብቁ” ብሎ ለሀገሬው እቅጩን ነግሮታል፣ ህግ አውጪው ክፍል የህይወት ዘመን ፕሬዝዳንት (President for Life) መሆኑን ነጋሪት ጋዜጣ ላይ አትሞለታል፣ ቮድካ አብዝቶ ጠጥቶ ሲያበቃ ሳት ብሎት “ሳፕራሙላት ስልጣን ይልቀቅ!” ያለ ሰው አንቀጽ ተጠቅሶበት በከባድ ወንጀል ይጠየቃል፣ ህዝቡም ቁርጡን አውቆ መላዕከ ሞት እስኪወስደው ለ21 ዓመት ጸጥ እረጭ ብሎ ተገዝቶለታል፣
የሶቪየት ህብረት ፈራርሳ ቱርኬሚኒስታን ጎጆ ለመውጣት ጉድ ጉድ በምትልበት ወቅት ሳፕራሙራት እጅግ ገራም ሰው ነበር፣ የገበያ ኢኮኖሚና የዲሞክራሲ ዋና አቀንቃኝ ነበር ይላሉ በቅርብ የሚያውቁት ሰዋች፣ ይህን ቀና አስተሳሰቡን አይተው ነው “ሽግግሩን ምራው፣ አንተው አንተው አሻግረን፣ ባንተው መጀን” ብለው የሽግግር መንግስቱ ፕሬዝዳንት አደረጉት ፣ ወዲያው “የቱርኬሚንስታን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (Democratic Party of Turkmenistan)” የሚሰኝ ድርጅት አቋቋሙ መንግስት መሰረተ፣ በነገራችን ላይ የህይወት ዘመን ፕሬዝዳንት ያለው ይህ ስሙ ውስጥ “ዲሞክራሲያዊ” የሚል ቃል ያለው ድርጅት ነው 🙂 ተቀናቃኞቼ የሚላቸውን ሰዋች ጥርሱን በነቀለበት ስታሊናዊ ዘዴ ከሩቅ አስቀራቸው፣ ፓርቲውን በአጎብዳጅና አጎንባሽ ሞላው፣ በዚህ ተመለስ፣ በዛ ተቀለስ የማይባል ሰው ሆነ፣
በስልጣኑ አፍላ ወቅት መፀሐፍ ፅፍያለሁ ብሎ መጣ፣ “የቱርኬሚንስታን ያለፈ ታሪክ፣ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ፣ የወደፊቱ እጣ ፈንታዋን፣ እንዲሁም ዜጎቿ ሊኖራቸው የሚገባውን ስነ-ምግባር በ158 ገፅ ቀንብቤዋለሁ” አለ፣ መፀሐፋ ለስጋም ለነብስም ይሁናችሁ ብሎ ለህዝቡ ሰጣቸው፣
የመፀሐፋ ርዕስ “ሩህናማ” አለው፣  ይህ መፀሐፍ ሁሉንም እውቀቶች አሟልቶ ይዟል ትፕብሎ ስለታመነ ሌሎች መጸሐፎች በመብራት ተፈልገው እንዲቃጠሉ ተደረገ፣ መፀሐፍ የተዘጋጀው ለገጽታ ግንባታ፣ የህዝቡን መንፈስ በአሉታዊ መንገድ ለመግራትና ከፍ ለማድረግ፣ ታሪክን ገንቢ በሆነ መልኩ ለመተርጎምና ለመረዳት፣ ነባሩን ባህል ለመግረዝ፣ እውነትና ስህተትን ለመበየን ወዘተ እንደሆነ ተነግሯል፣
“It was intended to serve as the “spiritual guidance of the nation” and the basis of the nation’s arts and literature, by creating a positive image of the Turkmen people, a heroic interpretation of its history, the review of Turkmen customs and the definition of “moral, family, social and religious norms for modern Turkmens”
ይህን መፀሐፍ ማንበብ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ከመፀሐፍ የወጡ ጥያቄዋችን መመለስ የግድ ነው፣ በትምህርት ተቋማት እንደ አንድ የትምህርት አይነት ይሰጣል፣ ለስራ ቅጥር የሚደረጉ የቃልና የፅሑፍ ፈተናዋች የሚለኩት የሰውየውን የሙያ ብቃትን ሳይሆን “ሩህናማ” ን ምን ያህል አንብቧል የሚለውን ነው፣
“ይህን መፀሐፍ ሶስቴ ያነበበ መንግስተ ሰማያት እንደሚገባ ፈጣሪ ነግሮኝል” እስከ ማለት የደረሰ ሰው ነው፣
_____________
የአብይ አህመድ እና ሳፕራሙራት እየተመሳሰሉብኝ ተቸግሪያለሁ፣ ሳፕራሙራት የሌኒንና የስታሊን ግርፍ ስለሆነ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ብሎ ሀገሪቷን ሀውልት በሀውልት አድርጓታል፣ አብይ ፓርክና የውሀ ፏፏቴ መርጧል፣
ሁለቱም መንፈስ ከታደሰ ስጋ ይጠግባል ባዬች ናቸው፣ ራሳቸውን የከበቡት በአጎብዳጅና አጎንባሽ ነው፣ ከኔ በላይ አዋቂ የለም፣ እውነትና መንገድ እኔ ነኝ ባዬች ናቸው፣  ሀገርን የሚያህል ነገር በግል ሀሳብና ፍላጎት ለመምራት አልተጨነቁም፣
የአብይን “መደመር”  በየትምህርት ቤቱ እንደገባ ሰምተናል፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የአብይን መፀሐፍ ቤት ለቤት መጋታችን አይቀርም፣ ሌላ ፓርቲ የለም ያለን የ’መደመር’ መፀሐፍ ደራሲ  ነገ ጠዋት ተነስቶ ሌላ ሀሳብ የለም ሌሎች መፀሐፍቶችን አቃጥሉ እንደማይለን ማስተማመኛ የለንም፣
ምን እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳንረዳ “መደመር” የመንግስት የስራ ቋንቋ ከሆነ ሁሉት አመት አልፎታል፣ እንኳን ተራው ህዝብ ሚኒስቴሮቹም ያወቁት አልመሰለኝም፣ ደራሲው ራሱ የገባው አልመሰለኝም፣
Filed in: Amharic