>

የ”እሪታ ቀን” ሕዝባዊ ሠልፍ ለሁለተኛ ጊዜ ተሸጋገረ

የ”እሪታ ቀን” በሚል መሪ ቃል፣ በአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ም/ቤት አነሳሽነት በመዲናችን አዲስ አበባ ያሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስመልክቶ በተለይም ማዋን ወደ ማኅበራዊ ቀውስ እየመሯት የሆኑትን የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክና የትራንስፖርት ችግሮች እንዲቀረፉ ለማሳሰብ ህዝቱ የተቃውሞ ድምፁን እንዲያሰማ ታቅዶ የነበረው ሕዝባዊ ሰልፍ ቀኑ ለሁለተኛ ጊዜ ተሸጋገረ፡፡የፓርቲው የአዲስ አበባ ም/ቤት መጋቢት 28 ቀን 2006 ዓ.ም ሊያደርግ አቅዶት የነበረው ሰልፍ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት የሰልፍ እውቅና ሰጪ ክልል ተቀባይነት አለማግኘቱን በደብዳቤ ቢለገፅም ፓርቲው ‹‹ሕጋዊ ሰልፍ ማድረግ እችላለሁ›› የሚለውን ሀሳብ ይዞ በመግፋቱ ሳቢያ የከንቲባ ጽ/ቤት ለሚያዚያ 05 ቀን 2006 ዓ.ም መሥተዳድሩ ሰልፉን ፈቅዶ ነበር፡፡

ሆኖም በተጠቀሰው ዕለት ኮካ ኮላ ስፖንሰር ያደረገው የሩጫ ውድድር በመኖሩ ሳቢያ በዛሬው ዕለት ሰልፉን ከፓርቲው ጽ/ቤት በመጀመር በቀበና አደባባይ አድርጎ ጃንሜዳ ላይ ማጠናቀቅ እንደሚችሉ የከተማው መስተዳድር ረቡዕ ሚያዚያ 01 ቀን 2006 ዓ.ም እውቅና ሰጥቶ ነበር፡፡ ፓርቲው ግን ሰልፉን በነገው ዕለት ከፅ/ቤቱ ተነስቶ መገናኛ ”ዲያስፖራ አደባባይ” ድረስ ሊያደርግ ቢያቅደም መሥተዳድሩ ረቡዕ ጥዋት በፃፈው ደብዳቤ ቦታው የተለያዩ መሠረተ ልማቶች የሚደረጉበት መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ደብዳቤው አያይዞም የመገናኛ አደባባይ ወደሲ.ኤም.ሲ፣ ወደኮተቤ፣ወደጉርድ ሾላና ወደሾላ መኪኖች የሚተላለፉበት እና ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚበዛበት በመሆኑ ሰልፉ ተቀባይነት ቢያገኝም በቦታው በተጠቀሱት ምክንያቶች የተነሳ ሰልፉን ማድረግ እንደማይቻል አስታውቋል፡፡

ፓርቲው በበኩሉ በአጭር ቀናት ውስጥ በቂ ቅስቀሳ ሳያደርግ ሥራ በሚበዛበት በዛሬው ዕለት ተገቢውን ሰልፈኛ ማግኘት ስለማያስችለው የሰልፉ ቀን እንዲታዘም ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ መሥተዳድሩም ሰልፉ የሚደረግበትን ቦታ እና ቀን በሚቀጥለው ሳምንት ለፓርቲው እንደሚያሳውቅ በደብዳቤው ቢያሳውቅም ፓርቲው ግን በቀኑ ላይ ተወያይቶ ከወሰነ በኋላ ሰልፉ በሚፈቀድበት ቦታ ላይ ከፋሲካ በዓል በኋላ ሚያዚያ 18 ወይም 26 ቀን 2006 ዓ.ም በቂ ቅስቀሳ በማድረግ ሰልፉን እንዲያካሂድ የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ተናግረዋል፡፡(ምንጭ ዕንቁ መጽሔት)

Filed in: Amharic