>
5:13 pm - Thursday April 19, 1618

መተከል... ኮንሶ...!!! (አቶ በለጠ ሞላ - የአብን ሊቀመንበር)

መተከል… ኮንሶ…!!!

ብዙ መተከል ብዙ ኮንሶና  ሻሸመኔዎች እየተፈፀሙ የገዥዎቻችን አንዲት ዛላ ፀጉር እንኳ አልሸበተችም!

አቶ በለጠ ሞላ – (የአብን ሊቀመንበር)

አብይ አህመድ ከፍተኛውን ስልጣን ይዘው “የኢትዮጵያ መሪ” ተብለው ከተሰየሙ 2 አመት ከ6 ወር ገደማ ሆናቸው። ይህ ግዜ ኢትዮጵያ እንደሀገር እጅግ ከተፈተነችባቸው ታሪካዊ ወቅቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ሚሊዮኖች ተፈነቅለዋል፣ ሽህወች ሞተዋል፣ ቢሊዮን ንብረት ወድሟል፣ በርካታ ሽህ ዜጎች በድንኳንና በቤተ እምነት ተጠልለዋል፣ ታዋቂ የሀገር ሰወች ደመ ከልብ ሆነው ቀርተዋል፣ ዜጎች ተሰቅለዋል፣
 ተወግረዋል፣ ታርደዋል፣ ዜጎች በክረምት ሳይቀር በላያቸው ላይ ቤታቸው ፈርሷል፣ 15 አመት ሙሉ አጠራቅመው ይደርሰናል ብለው የተመኙት ቤት “የለም!” ተብለዋል፣ የሀገር አንዱ ክፍል ተለይቶ ምርጫ አድርጓል፣ ሀገር በጥቅሉ ተጨንቃለች፣ አርቲስቱም፣ ገበሬውም፣ ነጋዴውም፣ ሀኪሙም፣ አስተማሪውም፣ ተማሪውም፣ ፓስተሩም፣ ዲያቆኑም፣ ኡስታዙም፣ ህፃናቱም ይሁን አዋቂው ወይንም አዛውንቱ ሁሉም ተጨንቀው ስለ ሰላም መጥፋት፣ ስለ ፍትህና እኩልነት ይጮሀሉ፣ በዚህ ላይ የኮሮና ወረርሽኝ ሁላችንንም ግራ አጋብቶን ቆይቷል በየእለቱም የሞት ቁጥር አሻቅቧል።
——-
መንግስት ባለበት አገር  ዜጎች እንደ አውሬ እየታደኑ ሲገደሉ ማየት እጅግ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም። በየወሩ የሰቆቃ ዜናዎች መስማት የተለመደ ሆኗል። በዚህ ሳምንት በመተከል የተፈጸመው ሰቆቃ እና በኮንሶ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የዜጎች ህይወት ጠፍቷል። የመተከሉ ጥቃት በተደራጁ ኃይሎች የተቀነባቀረ መሆኑን በመንግስት አካላት ተገልጿል። የዜጎችን ህይወት መታደግ፣ ጥቃትን ማስቆም፣ አመጸኞችን መቆጣጠር እና ግጭቶችን ማብረድ የመንግስት ኃላፊነት ነው።
ይህ ሁሉ ጭንቀት የበዛበት ዘመን ላይ ሀገርን መምራት፣ ሀገርን ከጥፋት ለማዳን መስራት እጅግ ረፍት የለሽ ትጋትን የሚፈልግ አስጨናቂና አድካሚ ሀላፊነት እንደሚሆን አምናለሁ።
 ዜጎች በየዕለቱ የጥቃት ኢላማ እየተደረጉ በሚታረዱበት እና በአሰቃቂ ሁኔታ በገፍ በሚገደሉበት አገር ለማህበረሰቡ የደህንነት ዋስትና መስጠት የተሳናቸው የብልጽግና ሹማምንቶች እርስ በርስ ለመወዳደስ፣ ለመሸላለም እና ካባ ለመጎናጸፍ ሲሯሯጡ ማየት ያሳፍራል። ድርጊቱን ማንም ይፈጽመው፣ በማንም ላይ ይፈጸም የድርጊቱ መደጋገም ግን መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተሳነው መሆኑን ነው የሚያሳየው።
የሚደንቀው ጉዳይ ይህ ሁሉ ሲሆን ገዥዎቻችን አንዲት ዛላ ፀጉራቸው አልሸበተችም። ለምንስ ይሸብታሉ??!!
————–
ሁሌም እንደምንናገረው አማራ ጠል ህግና መዋቅር ገዥ ሆኖ እስካለ ድረስ ብዙ መተክሎች፣ ብዙ ሻሸመኔወች ይፈፀማሉ …. ይህ ሁሉ ሲሆን ከኛ የሚጠበቀው መተባበር፣ አንድነትን ማጠንከር፣ ትግሉን መቀላቀልና መታገል እንዲሁም አጠናክሮ ማስቀጠል ነው። ይህ ሲሆን ትግሉ በሁሉም ቦታ ይቀጣጠላል።
—————-
አሁንም መተክል!!
Filed in: Amharic