>
5:18 pm - Friday June 16, 5595

ደርግ - ጐሠኛ አገዛዝ ወይስ በኦሮሞ ተወላጆች የበላይነት ይመራ የነበረ አገዛዝ? (ከይኄይስ እውነቱ)

ደርግ – ጐሠኛ አገዛዝ ወይስ በኦሮሞ ተወላጆች የበላይነት ይመራ የነበረ አገዛዝ?

ከይኄይስ እውነቱ

‹‹መስከረም 2/1967 በኢትዮጵያ የሲኦል በር ተበርግዶ የተከፈተበት ወይስ የለውጥ ፋና የተለኮሰበት? ደርግ አፍቃሪ ኢትዮጵያ ወይስ የኦሮሞ ብሔርተኞች?›› በሚል ርእስ 3 ሰዓት የሚጠጋ ግሩም ዝግጅት በርዕዮት ሜዲያ ተላልፎ አድምጬአለሁ፡፡ እንደ አንድ አድማጭ በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንና አዘጋጁን ቴዎድሮስን ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡ 

ሆን ተብሎም ይሁን የወያኔ የግፍ አገዛዝ ካስከተለው ምሬት በመነሳት የደርግ አገዛዝን በኢትዮጵያዊነት የማይታማ፣ የአንድነት ፖለቲካ ወኪል አድርጎ የመሳል ሁናቴ በአብዛኛው ሕዝብ ውስጥ እንዲናፈስ ተደርጎና ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ተቀባይነት አገኝቶ የዘለቀ ይመስላል፡፡ የዚህ አስተያየት አቅራቢ የግርማዊ ቀኃሥ ዘውዳዊ መንግሥት ሲያከትም የ8 ዓመት ልጅ የነበርኹ፤በደርግ ዘመን በ70ዎቹ መጨረሻ ከፍተኛ ትምህርት የተከታተልኹ፤ በውድቀቱ ዋዜማ ደግሞ የሥራ ሕይወት የጀመርኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ስለ ወያኔና የሱ ውሉድ የሆነውን የአሁኑን የኦሮሞ ጐሠኞች አገዛዝ ከደርግ ጋር በማነፃፀር ስለሚነገረው አስተያየት ከአንዳንድ ወዳጆቼ ጋር ስንወያይ ሁሌ የምላቸው የጋኔን በጎ የለውምና ከአጋንንት መካከል መምረጥ አያስፈልግም፤ የጐሠኞች አገዛዝ ሥርዓት ለሆነው የወያኔ ቆሻሻ አገዛዝ ያበቃንና መደላድሉን ሁሉ የፈጠረላቸው ደርግ ነው እላቸው ነበር፡፡ 

በባህላዊው ዘውዳዊ ሥርዓት እና በመጨረሻም በተደረገው ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሕዝብ ለምክርቤት ተወካዮቹን የሚመርጥበት ሕገ መንግሥታዊ የዘውድ ሥርዓት በማቆም ከሠለጠነውና በማደግ ላይ ካለው የዓለም ማኅበረሰብ ጋር በሥልጣኔና በዕድገት ጎዳና ላይ ለመራመድ ዝግጁ የነበረችውን ኢትዮጵያ የደም ምድር በማድረግ፣ ለሺህ ዘመናት ከዘለቀው የሀገረ መንግሥትነት ታሪኳ፣ ከባህላዊ፣ አምልኮታዊ (አልቦ እግዚአብሔር የሚል ሰይጣናዊ ርዕዮት በመጫን)፣ ሀገረ-በቀል እሤቶቿና ቅርሶቿ (ደርግ የጃንሆይን አገዛዝ ከመጥላቱ የተነሳ በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት አጥር ላይ ቀኃሥ የሚለውን በብረት የተቀረፀ ምልክት ለማጥፋት ሲፍቅ እንደነበረ አስታውሳለሁ) ጋር እንድትፋታና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አስተካክሎ ሙልጭ ደሀ ያደረገ አረመኔ አገዛዝ ነው – ደርግ፡፡ በዚህ አገራዊ ጥፋት ውስጥ በተቃውሞ ስም ከደርግ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ያልነበራቸው በዙሪያ ተሰባስበው የነበሩት የፖለቲካ ኃይሎች ድርሻም ጉልህ መሆኑን መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ 

የውይይቱ ተካፋዮች ስለ ደርግ አገዛዝ ባህርይ/ምንነት፣ በኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና የግዛት አንድነት ደቅኖት ስለነበረው ሥጋትና አደጋ፣ በሕዝቧ ላይ ስላደረሰው ሰቈቃና ግፍ፣ የታሪክ አረዳድ፣ ስለ ኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ቤ/ክ የነበረው አመለካከትና የፈጸመው ግፍ፣ ባይገባውም ይከተለው ስለነበረው የተውሶ ርዕዮት፣ ወዘተ. ያቀረቡትን ሃሳብና አቋም በአመዛኙ እስማማበታለሁ፡፡ 

ስለ ደርግ አገዛዝ የተሠነዘረውን የጐሣ ፍረጃ ሃሳብና አቋም በሚመለከት ግን ተዐቅቦ (ረዘርቬሽን) አለኝ፡፡ ይህም ተዐቅቦዬ የደርግ ‹መንግሥት› የኦሮሞ ተወላጆች የሠለጠኑበት ‹መንግሥት› መሆኑን ከመካድ የሚመነጭ አይደለም፡፡ ይልቁንም ደርግ ከተዋቀረበት የ5ቱ ድርጅቶች (መኢሶን፣ ወዝ ሊግ፣ ኢጭአት፣ ሰደድ፣ ማሌሪድ) መሪዎችና በመንግሥቱ ውስጥ ከሚገኙ ቊልፍ ባለሥልጣናት የኦሮሞ ተወላጅነት እንዲሁም ቀንደኛ የጐሣ ድርጅት የሆነው ኦነግ ጥንስስ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር የተቈራኘ መሆኑ፣ አገዛዙን ባጠቃላይ እንደ ሕወሓትና ወራሹ የዐቢይ አገዛዝ የጐሣ ያደርገዋል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰን ከሆነ ልዩነት ይኖረኛል፡፡ ወታደራዊው የደርግ አገዛዝ እንኳን በኦሮሞ ጐሠኞች የበላይነት የሚመራ መንግሥት ለመመሥረት ቀርቶ አመጣጡን ከመነሻው ስናይ (ከየክፍሉ የተወጣጡ የበታች መኮንኖች የራሳቸውን ጥያቄ ይዘው የመጡበት እንጂ) የመንግሥትን ሥልጣን ለመረከብ እንዳልነበር  እንረዳለን፡፡ ምናልባትም ይህ የጐሠኛነት አስተሳሰብ እላይ በተጠቀሱት ድርጅቶች ውስጥ የነበሩ ልሂቃን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ በአንፃሩም ‹‹የደርግ መንግሥት የነገድ ስያሜ ይሰጠው ከተባለ የኦሮሞ መንግሥት ነው፡፡›› የሚለው የወንድሜ አቻምየለህ አገላለጽ በኦሮሞ ተወላጆች የበላይነት የሚመራ መሆኑን ለመግለጽና አንዳንድ ፖሊሲዎችን በነሱ ፍላጎት አማካይነት ለማስፈጸም መቻሉን ለማመልከት ብቻ ከሆነ ሊያስማማን ይችላል፡፡ 

አንድ አገዛዝ ነገድን/ጐሣን መሠረት ያደረገ ነው ለማለት መመዘኛው ምንድን ነው? ባገዛዙ ቊልፍ አመራር ላይ የተቀመጡት ሹማምንት በአመዛኙ ከአንድ ነገድ/ጐሣ የተውጣጡ መሆናቸው ነው? ይሄ ሕጋዊና መዋቅራው ሆኖ እስካልተተከለ ድረስ፣ ሹማምንቱም ለተሰየሙባቸው የኃላፊነት ቦታዎች ሙያዊ ብቃት እስካላቸውና ሥልጣናቸውን በሕግ አግባብ እስከተጠቀሙበት ድረስ ችግር ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የአገር የበላይ መተዳደሪያ ከሆነው ሕገ መንግሥት ጀምሮ በበታች ሕጎች ጭምር የተደገፈ ከሆነ፣ በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅሮችና አሠራሮች ውስጥ የተዘረጋ ሥርዓት ከሆነ፣ ሕጉንና መዋቅሮቹንም ተጠቅሞ በአፍም፣ በመጣፍም እንዲሁም በተግባር ለአንድ ነገድ/ጐሣ ያደላ ሥርዓት በማቆም በዜጎች መካከል ልዩነትን ከፈጠረ ግን ያለ ጥርጥር ይህ የአገዛዝ ሥርዓት ጐሣን መሠረት ያደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ በደርግ ዘመን ይህ ዓይነት የጐሣ ሥርዓት ሰፍኖ ነበር ለማለት የሚያስችል ማስረጃ አላገኘሁም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ የነገድ/ጐሣ ማንነቱ ሳይጠየቅ የመረጠው ክ/ሃገር ሄዶ ከመኖርና ኑሮውን ከመምራት፣ ሥራ ከመቀጠር፣ መኖሪያ ቤት ከመሥራት፣ በገጠር የሚኖረው ገበሬ (የመንግሥትና ካድሬዎቹ ጭሰኛ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ) የመጠቀም መብት ብቻ የሚያገኝበት የመኖሪያና የእርሻ መሬት ባለይዞታ የመሆን፣ በመረጠው ቋንቋ የመማርና የመጠቀም፣ ተወልዶ ካደገበት ወይም ኑሮውን ከመሠረተበት ቦታ በጐሣ ማንነቱ ምክንያት ያለመፈናቀል፣ የመሳሰሉት መብቶችና ጥቅሞች የሚነፈግበት ሁናቴ አልነበረም፡፡ እነዚህ ሁናቴዎች ግን የደርግ መብት አክባሪነትን ያሳያሉ እያልኹ አይደለም፡፡ ደርግ አብዮታዊ ርምጃ እያለ ያለ ፍርድ ዜጎችን ሲፈጅ የነበረው በጐሣ ማንነት እየለየ አልነበረም፡፡ ደርግ ለአገር ህልውና አደጋ ነበር ከተባለ ሲከተላቸው በነበሩ አጥፊ የጦረኛነት፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ወዘተ. ካልሆነ በቀር ሕዝብን በማንነት በመከፋፈሉ አልነበረም፡፡

በእኔ አረዳድ ደርግን በትክክል ይገልጸዋል ብዬ የማስበው በመብትም፣ በነፃነትም ረገድ ዘርን መሠረት ሳያደርግ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ አስተካክሎ የበደለ፣ ሁሉንም መናጢ ደሀ ያደረገ፣ አገራችን በብዙ ድካምና ጥረት ያፈራቻቸውን በዕውቀትና በልምድ የበሰሉ÷ አገራቸውን የሚወዱ ታላላቆችን፣ ከጠላት ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ የፈጸሙና አኩሪ ገድል ያላቸውን አርበኞችን ፣ በተለይም ባንድ ምዕተ ዓመት የማናገኛቸውንና በሠለጠነው ዓለም ካሉ የሙያ አቻዎቻቸው ጋር በተመሳሳይ ደረጃ የሚገኙ ምርጥ የጦር መኮንኖችን እምሽክ አድርጎ የበላ፣ ሕዝብና አገርን ያዋረደ፣ ሁነኛ መካር በማጣቱ ወይም ባለመስማቱ ለአገራችንና ለሕዝባችን ዕዳ ሆኖ ያለፈ ጨካኝ አገዛዝ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ እስከ መጨረሻው ሕቅታ የንጹሐን ዜጎችን ደም በማፍሰስ የሰከረ፣ ለአገሩ ሲዋደቅ የኖረን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትኖ የሸሸና ለዘረኞች አሳልፎ የሰጠ ዕኩይ አገዛዝ በየትኛው መመዘኛ ነው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት ጠበቃ የሚሆነው? 

ሌላው በተዐቅቦ የያዝኩት ነጥብ ከገጠር መሬት ሥሪት አኳያ ደርግ በዓዋጅ ያደረገውን ሥር ነቀል ለውጥ ይመለከታል፡፡ ስለ መሬት ሥሪት ያለኝን ሃሳብና አቋም በሚመለከት በዘመነ ወያኔ የጻፍኩትን አጭር ማስታወሻ በሚከተለው አገናኝ ድረ ገጽ ማግኘት ይቻላል (https://www.ethioreference.com/amharic/Reflections ስለ መሬት ሥሪት፤ ጥቂት የውይይት መቀስቀሻ ነጥቦች

ደርግ ገበሬውን የመሬት ባለቤት ባያደርግም የሀብት፣ የማንነት፣ የአገር ባለቤትነት መገለጫ (ለአገዛዞች ደግሞ የሥልጣን ምንጭ) የሆነው መሬት በጥቂቶች እጅ ከተያዘበት ሥሪት አላቆ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕጉ በተወሰነው መጠን ባለይዞታ እንዲሆን ለማከፋፈል በመነሻው ላይ ያደረገው ጅማሮ መልካም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እየዋለ እያደረ ገበሬው በይዞታው በመብቱ ወሳኝ መሆኑ ቀርቶ አገዛዙ በፈጠረው የገበሬ ማኅበርና ባሠማራቸው ካድሬዎች አማካይነት ለሥልጣኑ ማጠናከሪያ መዋቅር በማድረግ ገበሬውን የካድሬዎች መጫወቻና የመንግሥት ጭሰኛ አድርጎት አረፈ፡፡ በመሆኑም በወያኔና በኦሕዴድ ለሚመራው ኢሕአዴግ በተግባር መጥፎ ምሳሌ በማስቀመጥ ከመሬት ጋር ለሚታየው ግፍና ግዙፍ ንቅዘት በር ከፍቷል ለማለት ይቻላል፡፡

Filed in: Amharic