>

ብአዴን መርገሙ (መስፍን አረጋ)

ብአዴን መርገሙ

 

መስፍን አረጋ


የሀገራችን ቀውስ በተወሳ ቁጥር

የሰላሟ ፀሮች ቢጠሩ በዝርዝር

ዋና ዋናወቹ የሚባሉት አንኳር

ወያኔና ኦነግ የሻቢያ ፍጡር

ብቻ ናቸው ብየ እከራከር ነበር፡፡

 

ነገር ግን በቅርቡ በፊት ከጥቂት ቀን

ሽመልስ አብዲሳን ያብይን በቀቀን

ካባ ሲያለብስ ሳይ የኢንሳው ተመስገን፣

 

ከሁሉም የከፋው እጅግ ያለመጠን

የኢትዮጵያ መርገም መሆኑን ብአዴን

ፍንትው አርጎ እሚያሳይ በራልኝ ብርሃን፡፡

 

የኢንሳው ተመስገን  አሳፋሪ ካባ

ሰላሳ ዓመት ወስዳ ወደኋላ ስባ

ድጋሚ አሳየችኝ ያለፈውን ደባ፡፡ 

 

ኢህአደግ በሚባል የማታለያ ልብስ

ወያኔ ሲነሳ ጦቢያን ሊያፈራርስ፣

ማርኮ በሰለበው በቅጥቅጡ ፈረስ

ተጭኖ ባልነበር ‹‹ባማራው›› አጋሰስ፣ 

እንኳን ደሴን አልፎ አዲሳባ ሊደርስ

ባልረገጠ ነበር የማይጨውን ቅያስ፡፡

 

ባኋላም ሲመጣ ሊወጋው ኢሳያስ

ለሁለት ተከፍሎ ሲቀረው አንድ ሐሙስ፣

አዲሱ ለገሰ የአማራው ሐጎስ

ከሞት አተረፈው ወግኖ ከመለስ፡፡

 

ከዚያም በመቀጠል አለና ዋል አደር

ደመቀ ፈልጎ ጌታውን መቀየር

ወደ ኦሮሙማ ሎሌነቱን ሲያዞር

ወያኔ ወደቀ አንድ ቀን ሳያድር፡፡

 

አሁን ደግሞ ዐብይ የኦነጉ አለቃ

ከወያኔ ዘመን በከፋ ሰቆቃ

የጦቢያን መከራ ለማርዘም የበቃ

በመታዘሉ ነው በደመቀ ጫንቃ፡፡

 

የኦሮሙማ ጦር፣ ሚሊሻ የገዳ

የለማ ትርሃስ የዐብይ መከዳ፣

የሰላማዊን በር ጥሶ ገብቶ ጓዳ፣

ሕጻን፣ ሴት፣ አዛውንት አጋድሞ መደዳ

ከማረድ በስተቀር ሰው እንደ ፍሪዳ፣

አለያም በገደል ሰውን እንደ ናዳ

ከመወርወር በቀር እንደ ጉራፋርዳ፣ 

 

ከታጣቂ ጋራ ገጥሞ ተኩስ ዒላማ

ወግቶ እየተወጋ ደምቶ እየደማ

አሸንፎ አያቅም ባንዲትም አውድማ፡፡

 

የመሣርያ ዓይነት ታጥቆ እስካፍንጫ

ሰለሳ ዙር ስልጡን ሰላሳ ቢንጫጫ

የመጨረሻ ዕጣው መሆኑን ሙቀጫ

ሰሜን ሸዋ አጣየ ነው ማረጋገጫ፡፡

 

እወክልሃለሁ ብሎ በሚያላግጥ

ተደርጎ ነው እንጅ አጣጥፎ እንዲቀመጥ፣

በነፍጥ የሚመጣን ለመመለስ በነፍጥ

የሸዋን ገበሬ ማንም እንደማይበልጥ

ስሙ ምስክር ነው ነፍጠኛ እሚያናፍጥ፡፡

 

አደባባይ ቁሞ ሁኖ እርግጠኛ

ሰብረናቸዋል ሲል ሽሜ ባፋንኛ

ውነቱን ነውና አትበሉት ጉረኛ፡፡

 

የተሰበረው ግን በሆዱ እየተኛ

ነው እንጅ ብአዴን የጎጠኞች ጌኛ

ያነፋፈጡ ሊቅ አይደለም ነፍጠኛ፡፡

 

ዐብይ አህመድ አሊ ሊቁ የሽወዳ

ቤተ መንግስት ገብቶ በውሻ ቀዳዳ

ዙፋኑን ጨብጦ መንጋ እየነዳ

ባፉ እየደለለ በግብሩ እየጎዳ፣ 

 

የቀመመውን መርዝ ከቅጠል የኦዳ

ጦቢትን ለውርደት ሐበሻን ለፍዳ

ማስጎንጨት የቻለው በመደመር ኮዳ፣

ዋናው አጋፋሪ መርዙን የሚቀዳ

ስለሆነለት ነው ‹‹ያማራው›› ወራዳ

ብአዴን የሚሉት የባንዳወች ባንዳ፡፡

 

ብአዴን ፍጥረቱ ነውና የሎሌ

ራሱን የሚሸጥ ለግማሽ አሞሌ

የተሻለ ሲያገኝ የሚሮጥ አለሌ፣

 

የበለጠ እሚከፍል አግኝቶ ከጨሌ

ወያኔን ሲከዳው ይሄ አልባሌ

ወያኔ እንደገባ ቀጥታ መቀሌ፣

 

ዐብይም ቢደርሰው የወያኔ ዕጣ

ሁሉንም ጣጥሎ ሳይዝ አንድ ሻንጣ

ንፋስ አይቀድመውም ከሀገር ሲወጣ፡፡

 

አማራውን መስለው አማራ እንዲነክሱ

እሱ እየቆረሰ እነሱ እየላሱ

ስም ያወጣላቸው ወያኔ ከኪሱ፣

 

ዋልዋ ተፈራ፣ ለገሰ አዲሱ

ጥሩነህ ተመስገን፣ ጥላሁን ንጉሱ

ደመቀ ቢወገድ ከነግሳንግሱ፣

 

የጦቢያ ነቀርሶች ወያኔና ኦነግ

ሁሉም ስለሆኑ የብአዴን ሐረግ

በሰዓታት እድሜ ይላሉ ጥውልግልግ፡፡

 

ለመጣ ለሄደው እሽክርና ሲቆም

ያሽከር ግልጋሎቱ ይበልጥ እንዲጠቅም

ሲያስፈልግ በክልል ሲያስፈልግ ባገር ስም

ልማዱ ነውና በጌታው /መሰየም/፣

 

ዐብይ አሸክሞ የኦነግን ሸክም

ገዳን እንዲያስፋፋ ተንገዳግዶ የትም

አዴፓ ቢለውም እየሾመለት ሹም፣

 

የቡድኑ ዓላማ እቅዱና ሕልሙ 

ነውና ማገልገል ጦቢያን ለሚያደሙ

እኔ ብየዋለሁ ብአዴን መርገሙ፡፡

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic