የነ እስክንድር ጉዳይ ብቻ በፈጠነ የፍርድ ሂደት የሚከንፈው ለምን ይሆን?
መስከረም አበራ
ጄነራል መንግስቱ ነዋይ በተንጋደደው የጃንሆይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከተናገረው ረዥም ንግግር ውስጥ
‘እኔላይ ሞት ለመፍረድ ያፈጠናችሁት የፍርድ ስርዓት ለደሃው ህዝብም ብታደርጉት ጥሩ ነበር ፣ለእኔ የሞት ፍርድ እንዲህ የምትፈጥኑ ሰዎች ደሃውን ገበሬ በረዥም የፍርድ ቀጠሮ የምታሰቃዩ ናችሁ….’ የሚል አይነት ነበር። (ቃል በቃል ላልለው እችላለሁ፣መልዕክቱን ግን አልሳትኩም)….
ተመሳሳዩን ዛሬ በነእስክንድርና አስቴር ፍርድ በእያየን ነውና እኛም እንጠይቅ ፨ለነእስክንድር ሲሆን የፃፈው ባያፍር አንባቢውን የሚያሸማቅቅ ክስ ከአራምባና በቆቦ ተገጣጥሞ በፍጥነት ቀርቧል። የክሱ ዝርዝር በሚያስገርም የፍሰት መፋለስ መንግስት በተከሳሹ ላይ ጥርስ የመንከሱን ብርታት፣የአዲስ አበባ ኬኛን ጥብቀት ብቻ በሚያስመሰክር ሁኔታ የተቸከቸከ የስሜት ጥርቅም ነው፨ሆኖም በፍጥነት ክስ ለመሆን ደርሷል።
አቃቢተ ህጓ ከንቲባ ከመሆናቸው በፊት፣ጠ/ሚው በተሰየሙበት እኛም በተከታተልነው መድረክ የነ እስክንድርን አበሳ ባወሱበት በዛው ንግግራቸው በርካታ ፋይሎችን አንቀሳቅሰው ፍትህ እንደሚያሰፍኑ ደስኩረው ነበር፨”ሴትዮዋ ራሳቸው ፍትህን ይመስላሉ” የተባሉትም የዛው ሰሞን መሰለኝ፨
ሆኖም በዛ መድረክ ላይ ከተነሱ ወንጀሎች ውስጥ በፍጥነት እየሰገረ ያለው እነ እስክንድር ጉዳይ ብቻ ነው።ሌሎቹ መዝገቦች የት ገቡ?ይህ በነእስክንድር ላይ የታየ የፍርድ በፍጥነት ለምን በዛ መድረክ በተነሱ መዝገቦች ላይ አልታየም?በመድረኩ አቃቢተህጓ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
– አግኝተን ይዘናቸዋል ያሏቸው አስራ ሰባቱን የደምቢዶሎ ተማሪውች ያገቱትን ወንጀለኞች ጉዳይ የት ደረሰ?
– በደቡብ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን ሁሉ ለፍርድ እናቀርባለን ያሉት እምን ላይ ደረሰ?(ነው በዛ ሰሞን ትዕቢት ትዕቢት ያለው የደቡብ ብልፅግና ባለስልጣን ነበረና እሱን ለማስፈራራት ነው?)
-የወንድም ጃዋር ነገርስ ወደኋላ የተገፋው ክሱ በቤተ-ዘመድ ጉባኤ ፀድቆ ወደ ፍ/ቤት እስኪላክ ነው?
– ነገውኑ ይጀመራል ተብሎ የነበረው የጀነራል ሰዓረ ገዳይ ነገርስ የውሃ በሽታ የሆነው እንዴት ነው?
-የአማራ ክልል ባለስልጣናት ግድያ ዶሲ እንደሚገላለጥም “ዕመት ፍትህ” የተባሉት ወ/ሮ አዳነች በዚሁ መድረክ ቃል ገብተው ነበር፤እና ከወዴት አለ?