>

ዛሬም እንደ ትናንት? !? (ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም)

ዛሬም እንደ ትናንት? !?

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

“ዶ/ር ዓቢይ መለስ ዜናዊ ባነጠፈለት ኮሮኮንች መንገድ ላይ ሳይጨነቅ እየተጓዘ ነው፤ ጠጠሮችን በመልቀም  ኮረኮንቹን መንገድ ለማለስለስ መሞከር የሚያዋጣ አይመስለኝም።” ይላሉ። እኔም ይህን እላለሁ። ዶ/ር ዓብይ፣ እንዳብዛኛው ሕዝብ በተቆፈረለት ቦይ እየፈሰሰ ነው። የቦዩ ብልሽትም መጥለቅለቅን እያስከተለ በሰው መፈናቀል፣ አካል መጉደልና ሞት፤ በሃብት መቃጠልና መዘረፍ እያስከተለ ነው። ይህን ስርዓት እንዴት መያዝ እንዳለበት የሚያውቅ፣ ለማስተካከልም ቁርጠኝነት ያለው መሪ እስክናገኝ ድረስ ችግራችን ይቀጥላል።
አብይ አህመድ የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ተስኖታል፤ አንድም መሠረታዊ የሆነ የሕግና የፖሊሲ ሥራ ለሁለት ተኩል አመት አላየነም፤ እውነተኛ የሕዝብ መሪዎች ይገደላሉ፣ ይታሰራሉ፤ ሌቦችን ሚኒስትር አድርጎ ይሾማል። ውይይት ተብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተወያይ ሳይሆን እንደ አወያይ፣ እኩያ ሳይሆን የበላይ ሆኖ ይሰየማል፤ ለመማር የተዘጋጀ ሳይሆን አውቆ የጨረሰ ይመስላል። እንዲህም የአገር መሪ የለ?!!!
የኢትዮጵያ አንድነት መሠረቶች የትውልድ ቦታ (አገር)፣ ቋንቋና ሃይማኖት ናቸው ይሉናል። አንድነታችን እየጠፋ ያለው እነሱን ነክተን ይሆን? ይህ ብቻም አይደለም። የሕዝብን መሪነት ስልጣን የያዙ ሰዎች የዜጋን መብትና የሕዝብን ደህንነት ሚዛን መጠበቅ ሲያቅታቸው የአንድነት መሠረቶችን ንደው ቡድንን መጠለያ ዋሻ፣ ግለሰብን የጊዜያዊ ጥቅም ተገዥ ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት አገር እየጠፋ ነው። ሌላው ጉዳይ ይህን ተከትሎ የመጣው የዜጎች፣ የጎሳዎች እኩልነት መደፍጠጥ ነው። ብዙው ትንሹን ከዋጠ፣ ምን እኩልነት አለ። ለዚህም መፍትሔው በተለይም ኦሮምያና አማራን ጨምሮ ከጎሣ የወጣ ተመጣጣኝ ክልልሎችን መፍጠር፣ ህገ መንግስተቱን ማሻሻል፣ የፓርቲዎችን የምስረታ ህግ ማስተካከል፣ ይህን ልዩ ሃይል የሚባል የክልል የመከላከያም በሕግ ማገድ ያስፈልጋል።
ሌላውና አሳፋሪው ጉዳይ ክብራችንና ኩራታችን ለዶላር የሸጥን ባሮች መሆናችን ነው። ዘመናዊው ትምህርትም፣ እራሳችን አስጠልቶ ለዚሁ የሚያዘጋጅ ነው። ምክንያቱም ከእኛነታችን የተፋታ፣ በፈረንጅ አማካሪዎች የሚመራ ስለሆነ እና ኅልዮቱ በተግባር የተደገፈ አለመሆኑ ነው። የመሬት ባለቤትነት ጉዳይም በደንብ ሊታሰብበት ይገባል። ከመሬት የበለጠ ምን ሃብት አለንና። ለመፈናቀል፣ ለሌቦችን እየዳረገን ያለው ይኸው ሃብት ነው።
“ሃይማኖት ያለፖለቲካ (ሥልጣን) አይቆምም፤ ፖለቲካ ያለሃይማኖት ሥልጣን አይቆምም፤ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ሃይማኖት በመንግስት፣ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም የሚለው ማወናበጃ ሐሰት መጋለጥ ያስፈልገዋል።” ይሉናል። እንደገባኝ፣ ይህ ሃሳብ ሴኩላሪዝምን ይቃወማል። ትክክል ነው ብንልስ እንዴትና የትኛው ሃይማኖት ነው ከመንግስት ጋር ስልጣን የሚጋራው? ሁሉም ካልንስ እንዴት ነው ስልጣን የሚጋሩት? እንደኔ የባለሥልጣኖች ሃይማኖተኝነትና ተጽእኖውን መቆጣጠር እንዳለ ሆኖ የሴኩላሪዝምን ሃሳብ መቃወም እብደት ነው። ሃይማኖት ወደ ስልጣን ይምጣ ማለትም የጨለማውን መንገድ መምረጥ ነው።
Filed in: Amharic