>

በወቅታዊ ጉዳዬች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ!!!

በወቅታዊ ጉዳዬች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ!!!

*
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መስከረም 9 እና 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝባችንን ባጋጠሙት ወቅታዊ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
1/ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕዝባችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ጥቃት በተመለከተ፦
አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ማንነትን መሰረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ተጨባጭ መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዚህም ከ160 በላይ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተጨፈጨፉ ተገንዝቧል፡፡
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራው ሕዝብ ጥንተ እርስቱን ተነጥቆ፣ ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብቱ ተገፎ ለሦስት አሰርት ዓመታት ለዝርፊያ፣ ለመፈናቀል እና ለተደጋጋሚ የዘር ፍጅት የተጋለጠበት ነው፡፡ በተለይም ‹‹ለውጥ›› እየተባለ በሚጠራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በክልሉ ውስጥ ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረገው የዘር ማፅዳትና ሰብዓዊ ጥቃት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
ንቅናቄያችን ልክ ከሰኔ 22 እስከ 24 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ  የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ እንደገለገፀው ሁሉ በቤንሻንጉል ክልል የተፈፀመው ጥቃት ተራ የማኅበረሰቦች ግጭት ወይም የሽፍቶች ድርጊት ውጤት ሳይሆን በአማራ-ጠል ትርክት ላይ የተመሰረተ፣ ስልታዊ የሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል፡፡
በዚህ አሰቃቂ ጥቃት የትኅነግ ተቀጥላ የሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የቤንሻንጉል ክልል መንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ የአማራ ሕዝብንና የአገሪቱን ሰላም ለማሳጣት የሚታትሩ ባዕዳንና ውስጣዊ ኃይሎች ያሰማሯቸው የሽብር ቡድኖች እጃቸው እንዳለበት አብን ያምናል።
የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ሕዝባችንን(አማራ/አገው) በማንነታቸው እየመረጡ በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በኃይል አሰባስበው ለጅምላ ጭፍጨፋ ሲያዘጋጁ የክልሉ መንግሥት መረጃ እና ጥሪ እየቀረበለት ባለመድረሱ፤ የፌዴራል መንግሥቱም ባለው የደኅንነት መረጃ ተመርኩዞ ጥቃቱን ለመከላከል ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አብን በጥብቅ ያምናል፡፡
አብን በሕዝባችን ላይ ከእንግዲህ ማናቸውንም አይነት ማንነቱን መሰረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊታገስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን እየገለፀ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትኄ ካልተበጀለት ጉዳዩ  ከአማራው አልፎ ታላቅ ብሔራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ፦
ሀ. መሳሪያ የታጠቁ ገዳዮችን በመደገፍና እንዳላዩ በማለፍ ለጥቃቱ መዋቅራዊ ከለላ የሰጡና በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የዘር ማጥፋቱ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤
ለ. በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚኖረው ሕዝባችን አስተማማኝ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ፣ በየአካባቢያቸው የፖሊስና የደኅንነት መዋቅሮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር፣ በማኅበረሰብም ደረጃ ደኅንነታቸውን የሚያስጠብቁበት አስቸኳይ መፍትኄ እንዲፈለግ፤
ሐ. የፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በአማራው ሕዝብ ላይ በሚፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ላይ የያዘውን ዳተኝነት እንዲያቆምና ችግሩን ለመከላከልና ከመሰረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ፤
መ. የአማራ ብልፅግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ በሦሥት ወራት ውስጥ ብቻ ሁለት እጅግ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ወንጀሉን በስሙ ከመጥራት ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ በመፈለግ ረገድ ያሳየው አቅም እና ፍላጎት ከደረጃ በታች መሆኑና ከእንግዲህም ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ ከዚህ አካል ሊመጣ እንደማይችል ሕዝባችን በግልፅ እንዲገነዘበው፤
ሠ. ሕዝባችን በተከታታይ ለዘር ማጥፋት እና ዘር ማፅዳት ጥቃቶች የተጋለጠበት የቤንሻንጉል ክልል አማራው ፍጹም ሥነ-ሕዝባዊ አብላጫ እያለው ፖለቲካዊ ውክልና በማጣቱ የተነሳ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የክልሉ መዋቅር የነዋሪዎቹን መብቶች በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲከለስ ድርጅታችን አብን ያሳስባል፡፡
2/ በአማራ ክልል የደረሰውን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ በተመለከተ፦
በአማራ ክልል በዘንድሮ ክረምት ዝናብ ምክንያት በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች በአጠቃላይ በ6 ዞኖች በሚገኙ 36 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 164 ቀበሌዎች በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለፁ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል፡፡
በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ፣ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር በሊቦከምከም፣ ደራና ፎገራ ወረዳዎች በከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመጠቃታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ፡፡
አብን እነዚህ በጎርፍና በመጥለቅለቅ የተፈናቀሉ ወገኖች በአስቸኳይ የእለት እርዳታ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ይጠይቃል፡፡
በጎርፉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሊነሱ በሚችሉ የወባ እና ሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች ሕዝቡ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡
ተጎጂዎች ሰብሎቻቸው እና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንዲከናወኑ፣ ለመጪው ዘመንም የሚያስፈልጋቸውን ሁለገብ እርዳታ የማዘጋጀት ስራ እንዲሁም ለዘለቄታው በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ተመሳሳይ አደጋዎች ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትኄ እንዲፈለግ ይጠይቃል፡፡
በመጨረሻም በአማራ ሕዝብ ታላቅ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ አቅጣጫውን በመሳቱ በሕዝባችን ላይ ሥርዓት እና መዋቅር ሰራሽ ጥቃቶቹ ስጋት ደቅነውበት እንደቀጠሉ አብን ይገነዘባል፡፡
እጅግ ራስ ወዳድ በሆነው ሰፊ የፖለቲካ ውቅር ውስጥ ጨካኞች እና ያልተገሩ ስብስቦች በአማራው ላይ ጥቃታቸውን ባስቀጠሉበት አግባብ፣ ለኩርፊያቸው እና ለደም ጥማታቸው አማራ ቋሚ ግብር ወይም ማስያዥያ የሚሆንበት የፖለቲካ ድባብ በትግላችን መገፈፍ ይኖርበታል።
በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ያሉ ተዋናዮችንና በቸልተኝነትና በሴራ ተባባሪ የሆኑ አካላትን ጭምር ለማጋለጥ እና በኃላፊነት እንዲጠየቁ ለማድረግ አብን እንደሚሰራ በአፅንኦት ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡
በመጨረሻም አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለፅ ለመላው የአማራ ሕዝብና ለሕዝባችን ወዳጆች ከነገ ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም  ጀምሮ እስከ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት በምናደርገው ጥቁር የመልበስ እና ተያያዥ የሐዘን መግለጫ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ አብን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic