>

ፈቅደው የሞቱትን ዳግም መግደል አይቻልም!!! (ተዋሕዶ ባልተቋረጠ ጥቃት) አባይ ነህ ካሴ

ፈቅደው የሞቱትን ዳግም መግደል አይቻልም!!! (ተዋሕዶ ባልተቋረጠ ጥቃት)

አባይ ነህ ካሴ

 

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ሀገር አቀፍ ቅርጽ አለው። ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ። 
 
ሐሰተኛው እና ርዕዮተ ዓለማዊው ጥቃት በመላው ሀገሪቱ ተሠራጭቷል። 
በሰሜን ኢትዮጵያ አዲስ ያልኾነ ነባር ጥቃት እንደቆየ ይታወቃል። ሰሞኑን ከታላቁ የዋልድባ ገዳም የወጣው ዜና ሒደቱ መቀጠሉን አመላካች እንጅ የመጀመሪያ ነው ማለት አይደለም። ቤተ ሚናስ ውስጥ በምናኔ ካሉት መነኮሳት እየተለዩ ጥቃት የደረሰባቸው መኖራቸውን ሰማን። ነገሩ ከማሸማቀቅ እስከ ማስገደድ እስከ ግድያ የደረሰ ነው። የተወሠኑት ስደት ጀምረዋል። በየበረሃው የተበተኑት ቁጥራቸው አልታወቀም። እንግልቱ በዝቷል።
የኦርቶዶክስን አከርካሪ የመስበሩ ፕሮጀክት እንደገና ማንሠራራቱን ያጠይቃል። ፀሐይ የማይጠልቅበት እውነት አለ። ፈቅደው የሞቱትን እንደገና መግደል አይቻልም። ቀድሞ ወደተዘጋጀላቸው ዘለዓለማዊ ሕይወት በተጨማሪ ክብር እንዲገቡ ከማፍጠን በቀር ሌላ ምንም ማድረግ አይቻልም። አስኬማውን በራሳቸው ሲደፉት ያኔ ነው የሞቱት።
ቋርፍ በልተው ከሚኖሩበት በኣት እያወጡ ማጥቃት በራስ ላይ የሚመጣን መከራ ከመጨመር በቀር ቤሳቤስቲን አያስገኝም። የላመ የጣመ ቀርቶ ደረቁን መቁነን እንኳ የሚያገኙት በቀን አንዴ ነው። ከእነሷውም ኩርማን። ተው እንጅ ግፍ ይብቃ!

መልእክት

በመተከል የተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት ከጆሯችን ሥር እየጮኸ ፍትሕ ርትዕ ይጠይቃል። አያስተኛም። የሰኔ ፳፫ቱ ፍጅት በዐይናችን ብሌን እየተመላለሰ ብርሃናችንን እንደነጠቀን አለ። ሰብሰብ ደርጀት ብለን ለመሥራት እስካልወሠንን ብዙ ሰቅጣጭ ዜናዎችን ከመስማት ከመመልከት አንተርፍም።
በር ማንኳኳት ድል አይደለም። በተለያየ አሰላለፍ ብዙ አንኳኩተን ይኾናል። ሠናይ ነው። ማንኛውም በር የሚያንኳኳ ሁሉ ዓላማው በር ማንኳኳት ከኾነ ከግቡ ይልቅ በጥባጭ የመባል ዕድሉ ይሰፋል። ከአጥር በር በላይ ላያሳልፍ ይችላል።
ብዙ ዓይነት ስብስቦች አሉን። መብዛታቸው ጸጋ የመኾኑን ያኽል ተግዳሮት የመኾናቸውም በር ዝግ አይደለም። መናበብ አለባቸው። ለአንድ ዓላማ በተለያየ አቅጣጫ መሥራት ለወቅታዊው ጥቃት ዓይነተኛ መድኃኒት ነው። የመናበቡ ስንስል ከሌለ መጠፋፋት ሊመጣ ይችላል። ተመጋጋቢ የሚኮንበትን ስንስል (network) ልባሞች ይሠሩታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ለኦርቶዶክሳውያን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሞት ያልተደገሰበት አልተገኘም። መዲናዋ አዲስ አበባም ሳትቀር። ከቤተ መንግሥቷ እስከ ዳር ግዛቷ ኦርቶዶክስን የጠላች አገዛዝ ሥራ ላይ ተጠምዳለች። እኛ ደግሞ እርስ በእርስ መጠማመድ ላይ ተጥደናል። እንዴት ይኾናል?
ለኢሬቻ ማክበሪያ የይዞታ ማረጋገጫ ለመስጠት የሚፈጥን፤  በአንጻሩ ደግሞ በሀገሪቱ የፍትሐ ብሔር የቦታ ይዞታ ሕግ መሠረት ከይርጋ ጣሪያው በላይ በባለቤትነት ይዛቸው የኖረቻቸው የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መካናት ታንቀው ተይዘዋል። የኢሬቻን ይዞታ ለመናገር ደመራ በመስቀል ዐደባባይ ይከበራል የሚል መቅድም የሚሠራ ደግ አገዛዝ አለን።
ሆሳዕና ሰልችቷት መብቴ ሳይከበር የዐደባባይ በዓል አላከብርም አለች። ማን ሊኾን ባለ ሳምንት? አጋርነታችንን በምን እንግለጥ?
Filed in: Amharic