>

የተባበረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወደፊት! (ከባልደራስ- መኢአድ  ቅንጅት  የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ)

የተባበረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወደፊት!

 
 
   ከባልደራስ- መኢአድ  ቅንጅት  የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

 

* የባልደራስ -መኢአድ ከፍተኛው ምክር ቤት  ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ ክቡር  አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ሆነውም ቢሆን የባልደራስ-መኢአድ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ እኚህን የህዝብ ልጅና  መሪ መንግስት በፍጥነት ከእስር እንዲለቅም ምክር ቤቱ በጽኑ አሳስቧል
 ኢትዮጵያ ሀገራችን  ከገባችበት ምስቅልቅል ፓለቲካዊ ችገሮች ለማውጣት በቅንጅት መስራት አስፈላጊነቱን  የተረዱት የመላው ኢትዮጽያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ እና  ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ የካቲት 29/2012 ዓ.ም በመኢአድ  ጽህፈት ቤት ባደረጉት ስብሰባ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንጅት ለመስራት ያደረጉትን ስምምነት ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል ፡፡
የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ተመስርቶ ለህዝብ ይፋ በተደረገ በቀናት ውስጥ ዓለማቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ /  Coved 19 /   ወደ ሀገራት መግባቱን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ4 ሰው በላይ መሰብሰብ በመከልከሉ 20 አባላት ያሉት የቅንጅቱ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ለማድረግ ተቸግሮ  ቆይቷል::
የሁለቱ ፓርቲዎቸ ቅንጅት  አላማ በሃራቸን ኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የፖለቲካና የለሂቃን ክፍፍል በማጥበብ ብሎም በሚመጣው ምርጫ ላይ ተቀናጅቶ በመወዳደር አብላጫውን የህዝብ ድምጽ ይዞ መንግስት በመመስረት ሃገራችን ኢትዮጵያ  አንድነቷና ህብረቷ ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ብሎም ከፍተኛ የሆኑሃገራዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያችን በሰላምና በልማት ጎዳና ላይ ከፍ ብላ እንድትራመድ ለማድረግ ነው፡፡
የባልደራስመኢአድ የጋራው  ምክር ቤት በ09/01/2013  ዓ.ም ባደረገው  ስብሰባ የቅንጅቱን ፕሬዚዳንት ፣ ም.ል ፕሬዚዳንት  እና ሥራ አስፈፃሚውን በሙሉ ድምፅ መርጧል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሶስት አስርት ዓመታት በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ  አቶ እስክንድር ነጋ  አድልዎንናኢፍትሃዊነትን በብዕራቸው በመታገል የሚታወቁት ናቸው። ነገር ግን ዛሬም እንደገና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ይህ ውንጀላና እስር  በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ  እንደሆነ  የሚያምነው የባልደራስ -መኢአድ ከፍተኛው ምክር ቤት  ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ ክቡር  አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ሆነውም ቢሆን የባልደራስ-መኢአድ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ እኚህን የህዝብ ልጅና  መሪ መንግስት በፍጥነት ከእስር እንዲለቅም ምክር ቤቱ በጽኑ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸውና በተደጋጋሚ ለእስር የተዳርጉትን የነፃነት ታጋዩን አቶ ማሙሸት አማረን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን አቶ ማሙሸት አማረ  ለህግ የበላይነት ለዴሞከራሲ ስርአት ግንባታ የከፈሉትን ወደር የሌለው መስዋእትነትና ቁርጠኝነት የቅንጅቱ ምክር ቤት ያደነቀ ሲሆን በቀጣይነት ትግሉን በመምራት ቅንጅቱ በአሸናፊነት እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ምክር ቤቱ እምነቱን ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ ለሌሎች ፓርቲዎችም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከባልደራስ መኢአድ ጋር አብሮ ለመስራት የጠየቁትን ፓርቲዎች በቅርቡ አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚጀምር የገለጸ ሲሆን ሌሎች ከቅንጅቱ ጋር ለመስራት   ፍላጎት ያላቸውን ፓርቲዎች  የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ቅንጅቱን እንድትቀላቅሉ ሲል ጥሪውን አቅርቡዋል።  መላው የኢትዮጵያ ህዝብም ከቅንጅቱ ጎን በመሆን ያልተቆጠበ ድጋፉን እንዲሰጥ በታላቅ ትህትና ጥሪውን አቅርቡዋል፡፡
ምክር ቤቱ በመጨረሻም በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን በቅርቡ በቤንሻንጉል ክልል በንጹሃን አርሶ አደር  ወገኖቻችን ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ  የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እና ለመላው ህዝባችን  አምላክ መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን ሲል ተጎጅዎችን ያጽናናል ። ምክርቤቱ ይህንን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እያወገዝ መንግስት ሙሉ ሃላፊንቱን ይወስዳል ሲል አሳስቡዋል፡፡ በወልጋ፣ በሚዛን ቴፒ፣ በሐረር፣ በደራና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁ ቡድኖች አማካኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ሲሆን በቀጣይም አስከፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የመከላከል ርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክር ቤቱ ያሳስባል፡፡
በሌላ በኩል በጎርፍ መጥለቅለቅ በአዋሽ  ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም በመተሃራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እንዲሁም በጣና ዙሪያ ባሉ  ጉማራና ርብ ወንዞች መሙላት በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ህይወታቸውንና ንብረታቸው ላጡ ወገኖቻችንም ከልብ ማዘናችንን እየገለጽን መላው ህዝባችን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአኩሪ ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ ባህላችን  በመደገፍ ሃላፊነታችንን እንድንወጣ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል ።
ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ /  Coved 19 /   ወደ ሀገራች መግባቱን ተከትሎ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት መላው ህዝባችን ሳይዘናጋ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቡዋል፡፡
በመጨረሻም የሀገራችንን ኢትዮጵያ  መፃዒ እጣፈንታ የተሻለ ለማድረግ  በምናደርገው ወሳኝ ትግል ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የምትኖሩ የቅንጅቱ  ደጋፊዎች የሚጠበቅባችሁን ትግል እንድታደርጉልን  ጥሪያችንን እናቀርባለን ።
 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
  መስከረም 11/01/2013 ዓ.ም
Filed in: Amharic