>

ኢትዮጵያ ታላቅ ልጇን አጥታለች! (አቻምየለህ ታምሩ)

ኢትዮጵያ ታላቅ ልጇን አጥታለች!

አቻምየለህ ታምሩ

“የኢትዮጵያ ኃይሏ አንድነቷ ነው” በሚል ንግግራቸው የሚታወቁትና የኢትዮጵያ የዘመናት ድንበር ጠባቂ የሆኑት የአፋሮች መንፈሳዊ መሪ ሡልጣን ሐምፍሬ አሊ ሚራሕ በ74 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል! ሡልጣን ሐምፍሬ በቀ.ኃ.ሥ. ዘመነ መንግሥት የአፋር አስተዳዳሪ የነበሩት የቢትወደድ አሊ ሚራሕ ልጅ ሲሆኑ አባታቸው ከዚህ አለም ካለፉበት ከ2004 ጀምሮ አባታቸውን በመተካት ሕይወታቸው እስካለፈት ቀን ድረስ የአፋር ሕዝብ ሱልጣን በመሆን አገልግለዋል።
ሡልጣን ሐምፍሬ ካባታቸው ከቢትወደድ አሊሚራሕ ጋር በመሆን ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑትን የደርግንና የወያኔን የጭካኔ አገዛዞች ለማስወገድ በትጥቅ የታገዘ ትግል ጭምር ከፍለዋል። መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የዘመናት ድንበር ጠባቂዎች የሆኑትን አፋሮችን ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም ብሎ ለሁለት በመክፈል ኤርትራዊ አፋሮች ሲፈጥርና አገራችንን ያለ ባሕር በር ሲያስቀር “የአፋሮችን ኢትዮጵያዊነት እንኳን የዘመናት የኢትዮጵያ ድንበር ጠባቂ የሆኑት አፋሮቹ፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ የሚያውቁትና ሰንደቁን ሲያዩ ቀጥ ብለው የሚቆሙት ግመሎቻችንም ምስክር ናቸው” በማለት ቢትወደድ አሊ ሚራሕ የአፋርን ኢትዮጵያዊነት ያስረገጡበት ታሪካዊ ንግግር ወያኔ ጥርስ ውስጥ ከቷቸው ዳግም ተሰደው እንዲኖሩ ምክንያት ሆኗል።
መለስ ዜናዊ ቢትወደድ አሊ ሚራሕና ቤተሰባቸውን ማሳደድ ውስጥ የገባው፤ አንደኛ ቢትወደድ አሊ ሚራሕ ራሳቸው የአፋርን ኢትዮጵያዊነት የሚያስረዱ የታሪክ ምስክር በመሆናቸው ማስረጃ ለማጥፋት ሲሆን ሁለተኛ ምክንያት ደግሞ በዚያ የሽግግር መንግሥት ተብዮው ምክር ቤት ውስጥ ቢትወደድ አሊ ሚራሕ ያንን ታሪካዊ ንግግር ሲያደርጉ እዚያው የነበረው የመለስ ዜናዊ የመንፈስ አባት ኢሳያስ አፈወርቂ የቢትወደድ አሊ ሚራሕን ንግግር ሲሰማ ተናዶ የሽግግር መንግሥት ተብዮው ምክር ቤት አዳራሹን ጥሎ ስለወጣ የተናደደውን የመንፈስ አባቱን ኢሳያስን ለማስደሰት ነበር። መለስ ዜናዊ  በአፋር ላይ የመዘዘው የበቀል ሰይፍ በዚህ አላበቃም። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት “የኢትዮጵያ ኩዌት” ለመባል በቅታ የነበረችውንና ለዘመናት የኢትዮጵያን ድንበር ሲጠብቁ የኖሩ የአፋር ሡልጣኖች መቀመጫ ሆና የኖረችውን አሳይታን ታሪክ ለማጥፋ ከዋና ከተማነትም ፍቋታል። ሡልጣን ሐምፍሬ አሊ ሚራሕ ከታት በተያያዘው ንግግራቸው  መለስ ዜናዊ አሳይታን ከዋና ከተማነት የፋቀበትን ምክንያት ያስረዳሉ።
ያ ሁሉ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን መኳንንትና መሳፍንት፤ እንዲሁም ልጆቻቸው በወያኔና ኦነግ ዘመን አሰላለፋቸውን በማስተካከል ወገን ለይተው አዛዥና ናዛዥ ሆነው የኖሩትን ዘመን ሲክዱና  የወያኔና የኦነግን የነውረኛነት ፖለቲካ በማድመቅ ኢትዮጵያን ሲጎዱ ሲባጁ የኅሊና ሰው በመሆን የኖሩበት ዘመን እውነት በቅንነትና በሀቀኛነት ሲያስታውሱ፤ ትውልዱንም የወያኔና የኦነግ ልብ ወለድ ሳይሆን በወገንና በሃይማኖት ያልተለዩት አባቶቹ የሰሩትን የሚያኮራ ታሪክ ሲያስተምሩ ከኖሩ በጣት የሚቆጠሩ መተኪያ የሌላቸውና አንቱ ልንላቸው ከሚገቡ ጥቂት ታላላቅ አባቶቻችን መካካል ሡልጣን ሐምፍሬ አሊ ሚራሕ ቀዳሚው ናቸው።
በሰው ላይ ሞትን የሚያህል ከባድ እዳ አለና ሡልጣን ሐምፍሬ አሊ ሚራሕ ያሰቡትን ሁሉ ለመፈጸም ባለመቻላቸው እጅግ ያሳዝናል። እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው። ለወዳጆቻቸውና ለቤተሰባቸው በሙሉ ጽናትንና ብርታትን ፈጣሪ እንዲሰጣቸው ከልብ እመኛለሁ።
Filed in: Amharic