>

የሚገደሉት 5 ሊቃነ ጳጳሳትና 2 አገልጋይ አባቶች እነማን ናቸው? (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

የሚገደሉት 5 ሊቃነ ጳጳሳትና 2 አገልጋይ አባቶች እነማን ናቸው?

ብርሀኑ ተክለያሬድ

ትኩረት!! ትኩረት!! ትኩረት!!
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ በጃዋር መሐመድ ላይ ባቀረበው 3 ኛ ክስ ዝርዝር ላይ “……… ሰኔ 17/2012 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 5 ስዓት ከሀረርና ከአርሲ የመለመላቸውን 15 (በግምት) ወጣቶች በኦፌኮ ቢሮ ሰብስቦ በማህበረ ቅዱሳን ስም የተሰባሰቡት የኦሮሞ ገዳዮች ነፍጠኞች ለትግላችን እንቅፋት በመሆናቸው ማስወገድ አለብን በማለት የ5 ሊቃነ ጳጳሳትና የ2 የቤተክርስቲያን አገልጋይ አባቶችን ስም፣የስልክ አድራሻና በተመሳሳይ ስዓት ለመግደል ያመች ዘንድ የሚጠቀሙበትን መኪና፣የመኖሪያ አድራሻ፣የሚመገቡበትን ቦታ በማጥናት እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ሰጥቷል” ይላል።
የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እውነትነት በማስረጃ ማረጋገጥ የሚጠይቅ ሆኖ ነገር ግን የጠቅላይ ቤተክህነት ህግ ክፍልና የቅዱስ ሲኖዶስ ፅ/ቤት ጥቂት ጥያቄዎችን በማንሳት አደጋው አሁንም  ያላለፈ መሆኑን ማረጋገጥና መጠንቀቅ ይጠይቃል።
-ሊገደሉ የተዘጋጁት ሊቃነ ጳጳሳትና አገልጋይ አባቶች እነማን ናቸው? በምን መስፈርትስ ተመረጡ?
-ጠቅላይ አቃቤ ህግ በነጃዋር ላይ ይህን ክስ ሲመሰርት ወንጀሉን ሊፈፅሙ ተልእኮ የተቀበሉ ወጣቶችን በቁጥጥር ስር አውሏል? (በክሱ ላይ በግምት 15 የሚል የግምት ቁጥር የተጠቀሰ በመሆኑ ሁሉንም በቁጥጥር ስር አላዋለም ብለን እንመን)
-እነዚህ አባቶችም ሆኑ ስሙ የተጠቀሰው ማህበር ጥቃት ሊደርስባችሁ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ነበር?
-በክሱ ዝርዝር መጨረሻ “የተለያዩ ግድያዎችን ሊፈፅሙ በህቡዕ የተደራጁ እያንዳንዳቸው 10 አባላት ያሏቸው ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ በርካታ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ሲመራ…….” የተባለ በመሆኑ እነዚህ ቁጥራቸው ያልታወቀ የተባሉ ህቡዕ አደረጃጀቶች ነገስ ጥፋቱን እንደማይፈፅሙ ምን ማረጋገጫ አለ?
እኒህና ሌሎችም የቤተክህነቱ ህግ ክፍል ዛሬ ነገ ሳይል ሊያጣራቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው። ካሳለፍነው ይልቅ የሚቀረን ይበልጣልና እውነተኛ መረጃ ይዞ ቆፍጠን ብሎ መጋፈጥ ሳይሻል አይቀርም።
ንቃህ መዋቲ!!!
Filed in: Amharic