>
5:28 pm - Monday October 10, 7740

ነገረ አፈትላኪ...!!!  (መስከረም አበራ)

ነገረ አፈትላኪ…!!! 

መስከረም አበራ

“አፈትልኮ የወጣ” የሚል መረጃ  እምብዛም የማያጓጓኝ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ፡፡ “ለምን?” ብትሉኝ እነዚህ አፈትልከው ወጡ የተባሉ የኦህዴድ ባለስልለጣናት ያወሯቸው ንግግሮች ሚናየን እንድለይ ትልቅ ውለታ የዋሉልኝ ቢሆኑም በጣም የምወደውን ባህሪየን ስለነጠቁኝ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ እነዚህ አፈትላኪ ወሬዎች ሰውን ከመጠራጠር በፊት ማመንን የሚያስቀደመውን ማንነቴን ሳልወድ በግድ ስለወሰዱብ አፈትላኪ ወሬ መስማት ሳስብ Frustrate ያደርገኝ ጀምራል፡፡ ለወትሮው ሰውን የምጠራጠርበት ምክንያት ካላየሁ በቀር ማመንን ከመጠራጠር አስቀድም ነበር፤ አሁን ግን እድሜ “ለአፈትላኪ ዜና” ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ አንዳች ሃይል ይህ ቅደምተከተል ተቀያይሮብኛል፡፡ አዝናለሁ!
ለማንኛውም ዛሬ አፈተለከ የተባለውን የኢንሳ መረጃ “ኦቦ አፈትላኪ ዜና” ስዩም ተሾመ አጋርቶኝ ሰማሁት፡፡መረጃውን የሰማሁት በወዳጄ ኤርሚያስ ወይም በጠ/ሚው ኋላ ተሰልፌ አልነበረም፡፡በጎራ ተሰልፎ መራገጡ፣የአንዱ ቲፎዞ ሆኖ ሌላውን ማበሻቀጡ እስከ አንገታችን ለተነከርንበት የፖለቲካ ውስብስቦሽ የሚያባብስ እንጅ የሚረዳን ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡የተገኘውን መረጃ መመርመር ያለብን ፈቀቅ ልንልበት ከምንፈልገው የዲሞክራሲ መንገድ ለመግባት ምን ያህል ይረዳናል ከሚል አንፃር ; እስካሁን ፈቀቅ ማለት ያልቻልነውስ ለምንድን ነው? በሚል መንፈስ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡
 ከዚህ አንፃር መረጃው የያዘው አዲስ ነገር አልታየኝም፡፡ ኢህአዴግ ሚዲያዎችን ጃም እንደሚያድርግ መለስ ዜናዊንና በረከትስምዖንን በመሰሉ ከባድ ሚዛን ፖለቲከኞች አንደበት “ጃም ማድረግ ስራችን ነው፤አቅማችንን ስናደራጅ ቪኦኤንም ጃም እናደርጋለን፣አሜሪካን ሃገር የማይሰማ የዜና አውታር እኛ ሃገር ምን ይሰራል ሲሉ”  አፈትላኪ ዜና ሳንጠብቅ ስራቸውን ግልፅ ባለ ሁኔታ የኢቲቪን ካሜራ እያዩ ነግረውናል፡፡ ጃም ሲደረግ ደግሞ  ስንት ከተፎ አሽከር የነበረው መለስ ዜናዊ ራሱ ወርዶ ጃም ለማድረግ የሰው ስልክ እየተከተለ እንደማይሮጥ፣ቁጭ ብሎ የሚዲያዎችን የአየር ሞገድ እንደማይለካ ግልፅ ነው፡፡ስለዚህ አብይ ጃም አደረገ የሚለው ለእኔ ምንም አዲስ ነገር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ባይሆን “ኢንሳ ባለሁበት ሰዓትም ሆነ መቼም ቢሆን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚጎዳ ነገር አላደረግኩም፤የኢንሳ ቆይታየንም የምኮራበት ነው” የምትለዋ የጠሚው ንግግር ባትደገም ጥሩ ነው፡፡
ህዝብ አማራጭ መረጃ እንዳያገኝ አደንቁሮ መግዛትን ከማሳለጥ የበለጠ ህዝብን የሚጎዳ ነገር ኣላደረግኩም ማለት እንዴት ነው? ይህስ የሚያኮራው በምን ስሌት ነው? ጃም አድራጊውን የመረጃ ቀበኛ ሰራዊት በየቀኑ ሪፖርት እያዳመጡ የህዝብ ንቃተ ህሊና እንዳይዳብር ከማድረግ ሌላ ምን በደል አለ? ያኔ ግራ ቀኝ ማገናዘብ የሚችልበትን መረጃ የተነፈገው ህዝብ መስሎኝ ዛሬ የሚተራረደው? አብይ በዚህ ስራው የሚኮራ ከሆነ “ሙያችንን ህዝብ ሚዛናዊ መረጃ እንዳያገኝ የማድረጉን የገደል ጉዞ ለማሳለጥ አንጠቀምም” ብለው የወጡ ኢንጅነሮች ምን ይበሉ?
መረጃውን የሰጠው ሰውየ ከነዚህ ወገኖች አንዱ ነው:: ስለዚህ የአብይን ኩራት መኩራት ያለበት እሱ ነው፡፡ በንግግሩ ሁሉ በጣም እያመሰገንኩት የሰማሁት ሰው ነው፡፡ በተለይ በስተመጨረሻው “አብይን እኔ ብጠላውም ጠንካራ ጎኖቹን ማጠልሸት አልፈልግም” ያለበት ጨዋ ማንነቱ በጣም አስተማሪ ነገር የያዘ ነው፡፡ እኛ አድማጮችም በአብይ ወይም በኤርሚያስ ጀርባ ተሰልፈን ለመራገጥ ከምንጣደፍ እንዲህ ያለው አስተማሪ ነገር ላይ ብናተኩር የተሻለ ይመሰለኛ፡፡ በሃገራችን የዘረኝነት ንፋስ የእኔ ዘውግ ያደረገው ሁሉ ልክ ነው በሚልበት የልክፍት ዘመን የራሱ ዘውግ ሰዎች የሚመሩት መንግስት ከሚሰራውን ግፍ ጋር አልተባበርም ብሎ፣የሚያውቀውን መረጃ ለጋዜጠኛ እስከማጋራት የደረሰው የሰውየው ማንነት ገዘፍ ብሎብኛል፡፡
ስለዚህ እኔ የምሰለፈው በአብይ ወይም በኤርሚያስ አለያም  በአበበ ገላው ተቃራኒ ወይም ተዛማጅ ሳይሆን ከእውነት ጋር ከወገነው መረጃ ሰጭ ግለሰብ ጋር ነው! ከነጨዋነቱ፣ዘረኝነትን ከሚፀየፍበት ቅላፄው፣የጠሉትን ሰው እንዳይበላ እንዳይዘራ አድርጎ የማራከሱን ልማዳችንን ችላ ብሎ ሁሉን ነገር በልኩ ለመግለፅ የሄደበት መንገድ፣ሃገሩ በተቃዋሚዎች ጠብሰቅ ያለ ትግል ወደፊት መራመድ አለመቻሏ የሚቆጨው ቁጭት፣የሚያውቀውን ብቻ ለመናገር ያለው ዝግጁነት እጀግ የሚስመሰግነው ነው፡፡ ሌላውን ተውት፤ የማናውቀው ነገር የለም!
Filed in: Amharic