>
5:28 pm - Saturday October 10, 7807

ሳስበው ሁለት ጠ/ሚኒስትሮች የሚያስፈልጉን ይመስለኛል (ግርማ በላይ)

ሳስበው ሁለት ጠ/ሚኒስትሮች የሚያስፈልጉን ይመስለኛል

ግርማ በላይ


  

መሞታችን ካልቀረ በደምብ እየቀለድን እንሙት፡፡

ኢትዮጵያ በትንሹ ሁለት ጠ/ሚኒስትሮች እንደሚያስፈልጓት በዚህን የመጨረሻ የሚመስል ዘመን የገባችበት አጣብቂኝ በግልጽ ይናገራል፡፡

አንደኛው – አበባና የዛፍ ችግኝ እየተከለ – (ሊያውም ክረምትን ሳይጠብቅ በየካፊያና ዝናቡ በብዙ ቢሊዮኖች!) – መናፈሻ እየሠራ – ከተማ እያስዋበ የሚያስመርቅና በዚያም የሚኩራራ፣ የሚደሰትና የሚኮፈስ ጠ/ሚኒስትር  ሲሆን፡-

ሁለተኛው – በሀገራችን ላለፉት 30 ዓመታት ሥር ሰድዶ የተንሠራፋውን ዘረኝነት ከመባቀያው ቆርጦ በመጣል የዘር ፍጂትን የሚያስቀርና የሀገራችንን ሕዝብ በአንድነት አሰልፎ ችግሮቿን በመቅረፍ ለእውነተኛ ዕድገትና ብልጽና የሚተጋ ጠ/ሚኒስትር፡፡

ሌሎች የሰላምና የልማት ተግባራት በሚኒስትሮችና በምክትል ሚኒስትሮች ቆራጥ አመራር የሚከናወኑ ይሆናሉ፡፡

… ዩኒቨርስቲ እያለሁ አንድ ጓደኛየ ሦስት የሰውነት ቅርጾችን አዋህዶ በአንድ ሰውነት ውስጥ በማስቀመጥ ይወድ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንዷ ፀጉሯ በጣም ቆንጆ ነው፡፡ አንደኛዋ የሰውነቷ ቅርጽ ልዩ ነው፡፡ ሦስተኛዋ ደግሞ መልኳ እጅግ ውብ ነው፡፡ የሦስቱ ተማሪዎች ውበት አንድ ላይ ሲሆን እንጂ ከተለያዬ የስበት ኃይሉ እስከዚህም ነው፡፡ እግዜር አሟልቶ አይሰጥም፡፡ እንደሀገር የኛም ችግር ይሄው ነው፡፡ ዕውቀት ሲኖረን ጥበብ ይጎድለናል፤ ገንዘቡን ስናገኘው ማስተዋሉን እናጣለን፡፡ ለዚህ ነበር ጓደኛየ እነዚያን በቅርብ የምናውቃቸውን ሦስት ልጃገረዶች (‹ሴቶች ልጆች› ለማለት ማሰቤን ተረዱልኝ)በምናቡ አንድ እያደረገ ሊወድ የተገደደው፡፡

አቢይ አህመድ ግላዊ ባሕርይው የሆነውን ይሁን በሥራው ግን ከሀገር ጠ/ሚኒስትርነት ይልቅ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ሚኒስትርነት ወይም ለትያትር ቤት ሥራ አስኪያጅነትና የትወና ሥራ ይበልጥ የቀረበ ነው፡፡ በትያትር ዓለም የፈለግኸውን ገጸ ባሕርይ ወክለህ መተወን ስለሚቻል እንደውነተኛው ዓለም ለትዝብትና ለወቀሳ አትዳረግም፡፡ በትወናው ዓለም የምትላበሰው ገጸ ባሕርይ ከመድረክ ውጪ ስለማይከተልህ  ያኔ ራስህን ነህና ነፃ ነህ፡፡ የኦቴሎው ኢያጎ ለምሣሌ ተውኔቱ ላይና ከተውኔት ውጪ ይለያያል፡፡ አቢይ ግን 24/7 ቲያትረኛ ሆኖ ማየት የትወናው ሂደት ዕረፍት የለሽና አድካሚ ከመሆኑ አኳያ አስደናቂና ብዙውን ጊዜም አሳዛኝ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቅዋሜው ከቤት ውስጥም ሊጀምር እንደሚችል መገመትም እንችላለን፡፡ ለምን ቢባል በቤትም ትያትሩ ከዚያ እኛ ከምናውቀው ተውኔታዊ አዩ ጩፋዊ ጂዶው እንዳይብስ ያሰጋልና፡፡ ከ”ክርስቶስ ጋር በቀጥታ በሥልክ የሚነጋገሩ” ቄንጠኛ ጴንጤዎች ከቸርች እስከ ፓላስ እያሽቃነጡባቸው ነው ይህችን ሀገርና ይህን ምሥኪን ሕዝብ፡፡ ከየትኛውም ጎራ ጥሩ ክርስቲያን ማግኘት የተቸገርንበት ሁኔታ ነው ያለው – በኢሕአዲግኛ አገላለጽ፡፡ ይህን አገራዊ ችግር ለማጥፋት ወይ ድማ ለመቀነስ በግልጸኝነት አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያስችለን ሁኔታ ውስጥ አይደለንም፡፡ እንቀልድ! በመከራ ጊዜ ቀልድ ጥሩ ነው፤ ሃሳብን ያረሳሳል፡፡ ጭንቀትን ለጊዜው ይገፋል፡፡

ሀገርን መምራት ቀላል አይደለም፡፡ ሀገርን መምራት ለታይታ ከሚደረግ የተክለ-ሰውነት የገጽታ ግንባታ በእጅጉ የበለጠ ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ ወንዝ መጥለፍ፣ መናፈሻ መሥራት፣ ከተሞችን ማስዋብ በራሳቸው ግሩም ናቸው፡፡ ያለለት ለዚያ ደረጃ መድረስ ትልቅ መታደል  ነው፡፡ እንደኛ ዓይነቱ ወደንና ፈቅደን ባልተወለድንበት የዘር ሐረጋችን ምክንያት በቀስትና በጦር፣ በጥይትና በሠይፍ፣ በዱላና በገጀራ፣ በሜንጫና በላውንቸር በየዕለቱ እየተገደልንና ብልታችን ሳይቀር እየተቃፈፈ ወጥቶ መሬት ላይ እየተዘረጋ፣ ያልተወለዱ ሕጻናት ከሆድ ተቆራርጠው ወጥተው ለመቀጣጫነት መንገድ ላይ እየተጣሉ፣ ሕጻናትና እናት አባቶች በጭካኔ እየታረዱ …. ለዘመናት ያፈራነው ጥሪት በሴከንዶችና ደቂቃዎች ውስጥ የእሳት እራት እየሆነ… ይህንን ዐረመኔያዊ ድርጊት የሚያበረታታና ተባብሶም እንዲቀጥል ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያደርግ መንግሥታዊ ተቋም ከላይ እስከታች በግልጽ በምናይበት ሁኔታ… “ሸገር መናፈሻን ኑ መርቁልኝ” ብሎ በወታደራዊ ልምምድ የታጀበ ትርዒት ማሳየት ፍች-አልባ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ይህን አስከፊ ሀገራዊ ሁኔታ መካድ ይቻላል፤ የዚህን ሰቆቃ የዞረ ድምር ውጤት መለወጥም ሆነ ማስቀረት ግን ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ሁሉም የእጁን ያገኛል፡፡ አድልዖን የማያውቅ ደሞዝ ከፋይ ጊዜ ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ ሀገራችንን ችግሯን ተገንዝቦ ቁምጣውን ለ24/7 ሳያወልቅ ለይስሙላ ሳይሆን የድሃ ሕዝቡ ቁስል ተሰምቶት ባራባሶ ጫማ ተጫምቶ ላይ ታች እያለ የሚያስተዳድረንና የደም ዕንባችንን የሚያብስ መሪ ያስፈልገናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደናስሩዲንና እንደዶን ኪሾት፣ እንደአለቃ ገ/ሃናና ቻርሊን ቻፕሊን ያሉ ቀልደኛ መሪዎችን በአሁኑ የመከራ ዘመን ብቻም ሳይሆን ወደፊትም መቼም አትፈልግም፡፡ እኛ የሚያስፈልገን መሪ ሁለት ከመቶ ለማይሆነው ደልቃቃ የማኅበረሰብ ክፍል ብቻ እንደእንትን በየመድረኩ ተሸሞንሙኖ የሚቆም ሳይሆን ከ98 በመቶ ለሚበልጠው ድሃና ከድህነት ወለል እምብዝም ላልራቀው ወገናችን የሚያዝን፣ አዝኖም ከሙስናና ከምዝበራ የጸዳ ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥርዓት በመዘርጋት ዘርንና ሃይማኖትን ከምንም ሳይቆጥር ለሁሉም ዕድገትና ልማት የሚተጋ ነው፡፡ የምንፈልገው መሪ ሰው ሠራሽ ልዩነቶችን በጣጥሶ ያለፈ ንቃተ ኅሊና ያለው፣ ሰዎችን በችሎታቸውና በትምህርታቸው እንዲሁም ባካበቱት ልምድ በመለካት በሃቅ አወዳድሮ ተገቢውን ሰው በተገቢው ቦታ የሚመድብ ነው፡፡ ሌላውን ቱሪማንቱሪ ገለባ ሁላ እስኪያንገሸግሸን አየነው፤ ሰው የለም!! 

ዛሬ ሌሊት ብዙ የዩቲዩብ ገጾችን ስጎበኝ አደርኩ – “ጉረኛ!” ካላላችሁኝ – እንደሌሎች ብዙዎቹ ሌሊቶች ሁሉ፡፡ ይሄ አቢይ የሚባል ፌዘኛ ጠ/ሚኒስትር ምድረ አክቲቪስትንና ምድረ ጸሐፊን እስከምን ደረጃ እየከፋፈለውና እርስ በርስ እያባላው እንደሆነ ተረዳሁ፡፡

የበላን ያብላላዋል፡፡ አንዳንዱ ጌታዬ ለምን ተነካብኝ ብሎ ለእንጀራ ገመዱ ሲል ክፉኛ ሲብሰከሰክ ታየዋለህ – ኅሊና ግዛምዛ የለም፤ ወደ እሪያዎች ጋጣ ተጥሏል፡፡ ጭንቅላት በሆድ ተለውጧል፡፡ ያኔ ታዲያ የወጧን ነገር ለጊዜው እንርሳትና ይቺ የአንዲት እንጀራ ነገር ትዝ ትልሃለች፡፡ ትዝብትህን ስትቀጥልና ብዙዎቹን ሚዲያዎች እየለዋወጥክ ስትመለከት “ምነው ባይበላስ ቢቀር” የሚለው የቴዲ ዘፈን ትዝ ሊልህ ይችላል፡፡ እኔማ “እንዴ! ይቺ ድህነቴ ምን አለችኝ! ሽህ ዓመት ለማይኖረውና 60 እና 70 ሲገባ እንደጉሊት ጣሣ ተጠረማምሰን ለምንታየው ለዚህ ዘመን ዕድሜ ነው ይሄ ሁሉ መባላትና በውሸት አዙሪት እየተንደባለሉ ለትዝብት መዳረግ? ” እላለሁ፡፡ በእውነት ይገርማል እኮ! አንዳንዱ ካድሬ እኮ ከአቢይ በላይ አቢይ ለመሆን ይቃጣዋል፡፡ ውሻ በበላበት መጮኹ ውሻ ስለሆነ ነው – ሰውስ?

እንትና የሚባለው አክቲቪት እንትና የሚባለውን አክቲቪት በስድብና በዘለፋ ሲሞልጭ ለነገየ አይልም፡፡ እንዴ – በነገር ስንወራረፍ እኮ የክት ስድባችንን ሁሉ በአንዴ ዘርግፈን ለነገ መቸገር የለብንም ጎበዝ! ስንሰዳደብ እንኳ እንተዛዘን እንጂ! “አየህ! እንትናዬ እንዲያ ብሎ የተናገረው ሥልጣን ፈልጎ ስላጣ ነው፡፡ ስልክ ሁሉ ደውሎ ሥልጣን እንዲሰጡት ጠይቆ አልተሳካለትም፡፡….” ይልልሃል አንዱ ቱባ ካድሬ – እሚገርምህ ይህ ካድሬ ትናንትናና ከትናንት ወዲያ በአቢይ መንግሥት አመራር አንገታቸውን በቆንጨራ ስለተቀነጠሱት ዜጎች ትንፍሽ አይልም፤ ስለአቢይ የተረኝነት አባዜና ስለሚታየው ግልጽ የኦሮማይዜሽን የ“ኬኛ ፖለቲካ” ለመተቸት አቅምም ፍላጎትም የለውም – ደሞዙ በሰላ ጩቤ ይጨረገዳላ፡፡ ስለዛሬ ዘጠኝ ዓመት ሰነድ ግን ከመቀመጫው ብድግ በሚያስደርግ ንዴት እንደሽሮ ይንተከተካል – ውይ አፈር ያብላኝ! እኔን ብሎ መካሪ – ተሳስቼ እኔም እንደነሱው ስሜታዊ ሆንኩና አረፍኩት፡፡ ለማንኛውም የተባለው ሰው በርግጥም የጠየቀውን ነገር ጠይቆስ ቢሆን ምንድን ነው ኃጢኣቱ? ኢትዮጵያ የርሱስ ሀገር አይደለች እንዴ? በሙያው ቢያግዝ ምንድን ነው ጥፋቱ?

… የት ውስጥ  ነው ያለነው? ወዴትስ እየሄድን ነው? የአንዲት እናት ልጆች መሆናችንን እንዴት ረሳነው?  አንጎላችንን ምን በላብን? ከቀሪው የእንስሳት ዓለምስ እንዴት ልንወርድ ቻልን? ብዙ እንስሳት እኮ በብዙ ነገር ይበልጡናል፡፡ እኔ ሳውቅ ጅብ ጅብን አይበላውም – ለምሣሌ፡፡ እኛ ግን በነገርም በተግባርም እየተባላን ነው፤ አክቲቪስት “ሀ” አክቲቪስት “ለ”ን በስድብና በዛቻ ካጥረገረገው በአካል ቢያገኘው እንደቄሮ በሜንጫ አንገቱን እንደማይቆርጠው ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ ኧረ አቅል ጀባ ወገኖቼ! ኧረ ቆም ብለን እናስብ ግዴላችሁም! የተማረም ያልተማረም አንድ ሜዳ ላይ ተገናኘና ሁላችንም ደናቁርት ሆነን አረፍነው እኮ! አቢይን ለማሳጣትም ሆነ ለመደገፍና ክቡር ወንዑድ ለማድረግ የምትሹ ወገኖችም አቅል ግዙ፡፡ የምትቃወሙ በአግባቡ ተቃወሙ፤ የምትደግፉም በአግባቡ ደግፉ፡፡ ሰውነት ላይ ከማተኮር ሃሳብ ላይ አተኩሩ፡፡ ስትቃወሙም ሆነ ስትደግፉ ደግሞ ደርዝ ያለው ተጨባጭ ነገር ይዛችሁ እንጂ በስሜትና በልኩስኩስ ነገር ላይ አትመርኮዙ፡፡ እንዴ! ጊዜና ተሞክሮ ያብስላችሁ እንጂ! የምን የኋሊት ሩጫ ነው፡፡ ከመንደርተኞች ተራ የቡና ተርቲብ ወሬ ወጣ በሉ፡፡ ማደግ ይቻላል፡፡ በተባለው ውስጥ ሊባል ያልተፈለገን ለማለት ዳገት ቁልቁለት ከመቧጠጥ የተባለውን ብቻ ተንትኑ፡፡ ፀጉር ስንጠቃ ይቅርባችሁ፡፡ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌለውን ነገር ከማምጣት በተነሣው ነገር ብቻ ተወያዩ፡፡ ከጥላቻ ደግሞ ውጡ፡፡ ጥላቻ ተጠዪውን ብቻ ሳይሆን ጠዪውንም ጭምር ነውና የሚጎዳው ከመጠላላት አዙሪት እንውጣ፡፡ መፈቃቀር ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ልበ–ክፍትነት ብዙ አወንታዊ ዋጋ አለው፡፡ … ያቺ ጥይት የሆነች ሴት ጸሐፊ ግን ልጅ ይውጣላት፡፡ የሌሎችን ስም ስላልጠራሁ እንጂ መስኪ መስኪዋ ብላት ደስ ባለኝ ነበር፡፡ እባካችሁ ሁሉም ለሚያልፍ ነገር ዝም ብለን አንጨቃጨቅ፡፡ በስማም! 

ወገኖቼ! ይሄ ነፃነት የሚሉት ነገር ጎጂ ነው፡፡ አንድ ሰው እንዳሻው የመናገርና የማድረግ ዕድል ሲያገኝ ነገሮች እንዴት እንደሚበለሻሹና በምን ፍጥነት ከቁጥጥር ውጭ ሊወጡ እንደሚችሉ በቀላሉ ለመረዳት የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ማየት ነው፡፡  የመሳደብ ነፃነት ያገኘ የመሰለው እንዴት እንደሚሳደብ፣ የዘረኝነት ነፃነት ያገኘ የመሰለው በዘረኝነት አረንቋ ገብቶ እንዴት እንደሚግማማ፣ የመዝረፍ መብት ያገኘ የመሰለው እንዴት በሀብት ሽቅብ እንደሚሽቀነጠር፣ የመግደል ሥልጣን ያገኘ የመሰለው የሚጠላውን ወገን እንዴት አድርጎ አሰቃይቶና አዋርዶ እንደሚገድል፣ … ለመገንዘብ ከአሁኒቷ ኢትዮጵያ የበለጠ አስረጂ የለም፡፡ እነዚህ ኹነቶች ጎልተውና ግዘፍ ነስተው የሚታዩት ደግሞ እውተነኛ መንግሥት ሳይኖር ነው፡፡ መንግሥት እንዲኖር እንጸልይ ይልቁንስ — ወደሚያዋጣኝ ምሣየ ልሂድ – ደኅና ዋሉ ወይ እደሩ፡፡ ለነገር የሚፈልገኝ ካለ ባለመመለስ ለመተባበር ዝግጁ ነኝና አድራሻየ ይሄው – gb5214@gmail.com

Filed in: Amharic