>
5:28 pm - Thursday October 10, 9968

ፍትህን ደጋግመው እየሰቀሏት ነው‼️ (አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት)

ፍትህን ደጋግመው እየሰቀሏት ነው‼️

አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት

“ፖሊስ አቶ ልደቱ የአደራ እስረኛ ስለሆነ እሱን መፍታት ሥልጣን የለንም እያለ ነው….ትላንት በ100 ሺህ ብር ዋስትና ይውጡ የተባሉት  አቶ ልደቱ አያሌው ዋስትናው ተከፍሎም ዛሬ ማለዳ ድረስ መውጣት አልቻሉም። “
የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በትናንትናው ዕለት በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በስጠው ትዕዛዝ መሰረት ብሩ የተከፈለ ቢሆንም ዛሬ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ብናመራም የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልተከበረም።
ትላንት” መሽቷል” ያለው ፖሊስ ዛሬ ጠዋት ደግሞ “የመፍታት ስልጣን የለኝም የአደራ እስረኛ ናቸው” ይላል ….።
የሚፈታ ባለስልጣን እየተጠበቀ ነው። ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አለማክበር ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያ ለምን እኔ የፈለኩትን አልወሰባችሁም የተባሉ ሁለት ዳኞች ተደብድበው ታስረው መፈታታቸውን ዘግበን ነበር።
የፓርቲያቸው የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ዛሬ ጠዋት ልደቱን ሊያስፈቱ ሲሄዱ የገጠማቸውን ይህን ጽፈዋል:-
“ከድጡ ወደ ማጡ ይልሃል ይሄ ነው። የአቶ ልደቱን የማስፈቻ ትእዛዝ ይዘን የቢሾፍቱ ከተማ መምሪያ የተገኘነው በጠዋት ነበር።
ማስፈቻውን  ይዘን መርማሪውን ስናናግረው አስደንጋጭ መልስ መለሰልን። አቶ ልደቱ እኛ ጋር ያለው በአደራ ነው ስለዚህ እሱን የመፍታት ስልጣን የለኝም።
አዳማ ምስራቅ ሸዋ ፍትህ ቢሮ ሂዱና ይፈታ ብለው ፓራፍ ያድርጉበት አሉን። ነገሩ ስላልጣመን ይሄን ማለታችሁን በደብዳቤ ግለፁና ስጡን ስንል ይሄ የተለመደ አሰራር ነው አቶ ልደቱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በአደራ ተቀምጠዋል በሚል ጥያቄያችንን ውድቅ አደረገብን።
 እኛም ወደ አዳማ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ ዘንድ ቀርበን ጉዳዩን አስረዳን። ከፍርድ ቤት በላይ አይደለንም። ትእዛዙ የተፃፈለት አካል ነው ትእዛዙን መፈፀም ያለበት ብለው እየሳቁ ሸኙን። እያዘንን ወደ ቢሾፍቱ መምሪያ ተመልሰን የተባልነውን ለመምሪያ ሃላፊውን ነገርነው።
ሃላፊው ለምን ሄዳችሁ መሄድ አልነበረባችሁም ካለ በዃላ ከኛ አቅም በላይ ነው የሚመለከታቸው አካላት እየመጡ ነው ከሰአት ተነጋግረን እንወስናለን አለን።የተገላቢጦሽ አህያ ወደ ሊጥ ውሻ ወደ ግጦሽ ይሉሃል። ለማንኛውም ለአቃቢ ህግ ይግባኝ የመጠየቂያ ግዜ አየተጠበቀ እንደሆነ ከሞላ ጎደል ገምተናል። ፍትህን ደጋግመው እየሰቀሏት ነው።
የባሰ አታምጣ‼️”
Filed in: Amharic