>

በካድሬዎች ግዞት የተያዘች አገር...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

በካድሬዎች ግዞት የተያዘች አገር…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

 

በካድሬዎች ግዞት የተያዘች አገር ሁሌም ዘፈኗ፤ “ናኑ ናኑ ናዬ … የተሰቀለውን ማን ያወርድልናል” ነው?!?
በታሪካችን ሙሉ ካድሬዎች ከሌላው ዜጋ በላይ ናቸው። ሕዝብ የስልጣን ባለቤት ባልሆነበት አገር ሁሉ በገዢዎቹ ብቻ ሳይሆን በነሱ ሎሌውች አገዛዝ ስር ይወድቃል። ውሎ እና አዳሩም በካድሬዎች ፈቃድ ብቻ ይወሰናል። አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር በቀበሌው ውስጣ ካሉ መቶ ሺ ሰዎች በላይ ሚዛን ይደፋል። ይፈራል፣ ይከበራል፣ ያለው ሁሉ ይፈጸማል። በየደረጃው አንድ የወረዳ፣ የዞን ወይም የክልል ሹም እንዲሁ በሚያስተዳድረው ግዛት ስር ካሉ በሚሊየን ከሚቆጠሩ ሰውች ሁሉ ይበልጣል። ያሻውን ይናገራል፣ የጠላውን ያሳስራል፣ ያፈናቅላል፣ ቤት ያፈርሳል፣ መሬት ይነጥቃል። የወደደውን ደግሞ እንዳሻው ይሾማል፣ ይሸልማል።
አካሚው ጠፋ እንጂ ኢትዮጵያስ ክፉኛ ታማለች። በካድሬዎች ቅኝ የተያዘችው አገራችን እና ሕዝቧም ግራ የተጋቡ ይመስላል። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካድሬዎች ዘርፈው ያራቆቷት እና በድንቁርናቸው ያደነዘዙት ሕዝብ ዛሬ ደግሞ ማሊያ በቀየሩ የብልጽግና ሹመኞች ሲሸማቀቅ እና ስጋት ላይ ሲወድቅ ማየት ያሳዝናል።
የአንድ አገር ጤንነት፣ ሰላም እና ብልጽግና የሚለካው በሕዝቧ ውሎ አዳር ነው። መሪዎች እና ፖለቲከኞች እነሱ ጤና በሆኑት ልክ፣ እነሱ እስኪያቅራቸው በበሉት ልክ፣ እነሱ በደላቸው፣ እነሱ በሰላም ወጥተው በሰላም በገቡ ቁጥር፤ ሕዝብ ጤናው ተጠብቆ፣ ቁንጣን እስኪይዘው በልቶ፣ በምቾት ተደላድሎ፣ ሰላሙ በሪፐብሊካን ጋርድ ተጠበቆ፣ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባ ይመስላቸዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በበርካታ የአገሪቷ ክፍሎች በሰላም ውሎ በሰላም ማደር ብርቅ ሆኗል። ዛሬም የኢትዮጵያ እናቶች ደም እንባ ያለቅሳሉ። ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በግፍ ታስረው የፍትህ ያለህ ይላሉ። ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች በጉልበተኛ ካድሬዎች ቤታቸው በላያቸው ላይ ፈርሶ ከነልጆቻቸው ሜዳ ላይ ተጥለው ያለቅሳሉ። ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች በብሔራቸው እና በጏይማኖታቸው ተለይተው ለወሬም በማይመች አሰቃቂ ሁኔታ ሰውነታቸው ተቆራርጦ ይገደላሉ (መተከል ውስጥ የአንድ አማራ ወጣት አንገት ተቆርጦ የአጥር ሽቦ ላይ ተንጠልጥሎ የሚያሳይ ፎቶ ዛሬ በጠዋቱ ተመለከትኩ)። አይ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄድን ይሆን?
በካድሬዎች ቅኝ ግዛት የተያዘ አገር እጣፈንታው ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። በአገር ሀብት የተደላደሉ እና ያለ ሕዝብ ፈቃድ ሥልጣንን የሙጥኝ ያሉ ካድሬዎች ከብልጽግናው ይልቅ ለብልግና ቅርብ ናቸው። ኢትዮጵያ ባለሥልጣን ቶሎ ከሚባልግባቸው ጥቂት የአለም አገሮች መካከል ግንባር ቀደሟ ነች። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች በዋነኝነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። አንደኛው ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ስላልሆነ አናቱ ላይ የተሰቀሉትን ሹሞች ሲባልጉ ማረቅ እና ማውረድ አይችልም። ባይሆን ለአሥርት አመታት  “ናኑ ናኑናዬ … የተሰቀለውን ማን ያወርድልኛል” የምትለዋን የሙሉቀንን ዘፈን እየተቀኘ ሥልጣን ላይ የተሰቀሉት ሰዎች ደክሟቸው ወይም አንሸራቷቸው እስኪወድቁ አንጋጦ ይጠብቃል።
ሁለተኛው ችግር ፖለቲካን እና መንፈሳዊነትን ቀላቅሎ ስለሚያይ የፖለቲከኞችን ብልግና እንደ እዝጌር ቁጣ ስለሚቆጥረው “እሱ ያመጣውን እሱ ይመልሰው” ወይም “እሱ ይገስጣቸው” እያለ ካድሬዎችና ሹሞች ሲባልጉ፣ ሥራውን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን፣ ተስፋውን፣ ልጆቹን፣ አገሩን ነጥቀው ሲያራቁቱት እንደየ እምነቱ ፈጣሪው ጋር ሄዶ እንባውን ወደሰማይ እየረጨ “ወይ ፍረድ ወይ ውረድ” ሙግት ይጀምራል። ይህን ስነ-ልቦናውን ጠንቅቀው የሚያውቁት ካድሬዎች እና ሹማምንት ለሕዝብ ቁጣ ግድ የማይሰጣቸውም ለዛ ነው።
ለዛም ነው በኛ አገር ሹም የሚሻረውም ሆነ የሚቀጣው ከአለቆቹ ሲያፈነግጥ ብቻ የሆነው። ሕዝብ አስቀየምክ፣ ሕዝብ በደልክ፣ የሕዝብ ሃብት ዘረፍክ፣ የሕዝብ ቃል አጎደልክ ተብሎ የሚሻር እና የሚወቀስ የለም። እንደውም አበጀህ ይመስላል አጥፊው ይሾማል፣ ይቀባል፣ ካባ ይደረብለታል። ሽመልስ ባህር ዳር ላይ ያጠለቃት ካባ ብዙ ትናገራለች።
የኢትዬጲያ ሕዝብ የአገሩ እና የሥልጣኑ ባለቤት እስኪሆን ድረስ የመጣንበትን መንገድ እንመላለስበታለን። ከዚህ አዙሪት ለመወጣት አንዱ መንገድ ቀጣዩ ምርጫ ሊሆን ይችላል። ስለምርጫው ቀሰፊው በሌላ ጽሑፍ እመለሳለሁ።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic