የኦሮሚያ ፖሊስ ተጓዦችን “አዲስ አበባ አትገቡም ” ብሏል፤ ነገ ፓስፖርትና ቪዛ ይጠይቃል ….
አ.ሚ.ማ
* ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ የነበሩ ተሳፋሪዎች ሱሉልታ ከደረስን በኋላ በኦሮሚያ ፖሊስ እንድንመለስ መደረጉ አግባብ አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።
አማራ ሚዲያ ማዕከል/
ከአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋር ቆይታ ያደረጉት የታታ እና መርቸዲስ ተሳፋሪዎችና ሾፌር እንደሚሉት ዛሬ መስከረም 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሱልልታ ቢደርሱም ለሰዓታት ሲፈተሹ ከቆዩ በኋላ ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል።
ተሳፋሪዎቹ እንደአብነትም ከባህር ዳር፣ከፍኖተ ሰላም፣ከቡሬና ከሌሎችም አካባቢዎች ተሳፍረው ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ገልፀው ይሁን እንጅ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮምሽንና የክልሉ ልዩ ሀይል አባላት እንደመለሷቸው ተናግረዋል።
በጉዞ ላይ ውለው ከቀኑ 9 ሰዓት ሱሉልታ ቢደርሱም የተለያዬ ፍተሻ ሲያደርጉ አምሽተው ከቀኑ 11:30 ላይ “አዲስ አበባ መግባት አትችሉም፤ አዲስ አበባ ምን አላችሁ?” በማለት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
ፖሊሶቹ መታወቂያ ተቀብለው ካዩ በኋላ ተመለሱ ሲሉን ለምንድነው የምንመለስ ብለን በመጠየቃችን የተደበደብንም አለን ሲሉ ተሳፋሪዎች የደረሰባቸውን እንግልት የገለፁ ሲሆን መንገድ ላይ አደጋ ቢደርስብን ተጠያቂው ማነው ሲሉ የጠየቁት ተሳፋሪዎች የፍትህ ያለ ሲሉ ተማፅነዋል።
የተሳፋሪዎችን ቅሬታ ይዘን ወደ ኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ ለአቶ ሞገስ ብንደውልም መረጃው የለኝም ብለዋል።
ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ለምን ይከለከላሉ? ካሉ በኋላ ጉዳዩን አጣራዋለሁ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከቀናት በፊትም በተመሳሳይ ወጣቶች ናችሁ፣ ወደ አዲስ አበባ ለምንድን ነው የመጣችሁ? በሚል እንዲመለሱ የተደረጉ ተሳፋሪዎች መኖራቸውም ይታወሳል።
ከተሳፋሪዎች፣ከሾፌሩና ከአቶ ሞገስ ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ ይጠብቁ።