* ሀገር ሰርታ ያስረከበች ባለ ታሪክ
መሬት ከጠላት ነጻ ያወጣች አርበኛ
ቀን ከሌሊት አገሪቷን በጸሎት የምትባርክ
ቅድስት ቤተክርስትያን ይዞታዋን ልትነጠቅ አይገባም
ፍትህ የሌለባትና ህግን የማታከብር ሆናለች፡፡ ተቋማዊ ጸረ ኦርቶዶክስነት ያኘኩትን ምግብ እንደመዋጥ ተፈጥሮአዊ ዑደት መስሏል፡፡ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ከሞራል መደርደሪያ ወርደው ሜዳ ናቸው፡፡ በዚያ ልክ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖችን እንባ እንዴት እንደተሸከመች እግዚአብሔር ይወቅላት፡- ሆሳዕና
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደርና ቀጥሎም የከንባታና ሥልጤ ዞን አስተዳደር ያደረሱትና አሁንም እያደረሱ ያሉት ግፍ የሥላሴ ልጅነትን ለተቀበለ ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህ ግፍ እነሱ ላይ ብቻ የደረሰ ሳይሆን ሁሉም የእምነቱ ተከታይ ላይ የተፈጸመ በየትኛውም ህግ ተቀባይነት የሌለው ግፍ ነው፡፡ ለአርባ ዓመታት ቤተክርስቲያኒቱ ስትጠቀምበት የነበረውን ህጋዊ ይዞታዋን ያለ ህግ ነጠቋት፡፡ ለብዙ ዓመታትም የይዞታ ማረጋገጫ እንዲሰጣት ልጆቿ እጅግ ክርስቲያናዊ በሆነ ምግባር ሆነው ሲጠይቁ ከረሙ፡፡ ኦርቶዶክስን ማጥፋት አጀንዳ አድርገው በአስተዳደሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ባለሥልጣናት ግን በሚዘግንን ማን አለብኝነት ይዞታ ከልክለው፣ ቦታውንም ነጥቀው ይኸው ዛሬ በ2013ዓ.ም የከተማው ምዕመን የአደባባይ በዓሉን መስቀልን በአደባባይ አያከብርም፡፡
ጉዳዩ ወደ ክልሉ ቢሄድም፣ ክልሉ በተደጋጋሚ ቦታው ለቤተክርስቲያን እንደሚገባ ፈርዶ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲሰጣት ቢወስንም፣ የተወሰነውን ተግብረው ምላሹን እንዲያሳውቁት ከበታች ያሉትን በደብዳቤ ቢያሳስብም 50000 ካሬ ሜትር መሬት ተወስዶባት በምትኩ ለይስሙላ 20ሺህ ካ.ሜ ተስቷት የነበረቸው ቤተክርስቲያን ዛሬም የካህናቶቿንና አዛውንት ምዕመናንን እንባ ይዛ እንደ ቆመች ነው፡፡ ይባስ ብሎ የከተማው መስተዳደር ምትክ ተብሎ ለጊዜአዊነት የተሰጣትን 20ሺ ካሬ ሜትር መሬት ይዞታነቱን ለቤተክርስቲያን እንደማይሠጥ፣ የአደባባይ በዓላትን በምታከብርበት ጊዜ ብቻ ሌሎችም አቢያተ እምነቶች እንደሚያደርጉ ማዘጋጃ ቤቱን አስፈቅዳ ማክበር እንደምትችል፣ ከዚያ ውጭ ባለው ጊዜ መዝናኛ ቦታ ሆኖ አስተዳደሩ እንደሚያስተዳድር ግልጽ በሆነ ደብዳቤው አሳውቋል፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታ የክልሉን ውሳኔ ይጻረራል፣ የገዛ የቤተክርስቲያኒቱን መሬት ነጥቆ ባይተዋር ያደርጋታል፣ አድርጓታልም፡፡ በጊዜአዊነት ተሰጥቷት የነበረውን የ20ሺህ ካሬ ሜትር ካርታን እሰጣለሁ ብሎ የነበረ ቢሆንም የገዛ ቃሉን አጥፎ፣ በማን አለብኝነት ህዝበ ክርስቲያኑን እያሰቃየ ይገኛል፡፡
እስቲ ቅን ሕሊና ያለው ሁሉ ይፍረድ!! በምን መስፈርት ነው የክልልን መመሪያ እንቢ ብሎ በተቃራኒ የቆመ የከተማ አስተዳደር ያለ ተጠያቂነት የሚገኘው; የትኛውስ የሀገሪቱ ህግ አግባብ ነው ህጋዊ መብትን በህገ ወጥ የሥልጣን ሠንሰለት ደፍጥጦ በማፈን፣ ሊያውም በዓለም አደባባይ ሀገሪቱ እኮራበታለሁ የምትለውን የመስቀል በዓልንም እንዳይከበር በማድረግ የህዝብ መሪዎች መሆን የሚቻለው;
በሀገር አቀፍ ደረጃ ኦርቶዶክሳዊያን ላይ ግልጽ የሆነ የግፍ አገዳደል ሲፈጸም እያየን እዚያ ደግሞ የመስቀል ማክበሪያ ቦታን ባለመቀማት እንኳን ትንሽ የርኅራሄ ልብ ሊያሳዩን አልወደዱም፡፡ ኦርቶዶክስ ተገድሎ ሌሊት ለአራዊት በሚሰጥባት ሀገር እዚያ ደግሞ የሆሳዕና ክርስቲያኖችን ባለማንከራተት ራሱ ተረጋግተን የልብ ህመማችንን እንድናዳምጥ አልፈቀዱልንም፡፡ የሐገሪቱ መሪ ኦርዶክስ ሀገር ናት ብለውን ነበር፡፡ በርግጥም እውነታው እሱ ነው፡፡ እዚህ ደግሞ ሀገር የሆነችውን ቤተክርስያን ይዞታዋን ይነጥቋታል፡፡ በልጆቿ ህመም የሚሳለቁ በዝተው፣ በምዕመኗ ሞት እንደ ዜጋ ይቅርና እንደ ሰው ልጅ እንኳ አልታዘነላቸውም፡፡
ኦርቶዶክሳዊነት ወንጀል አይደለም ፍትሕ!!