>

ሞት ከታቀደባቸው በፊት የሞቱት ፍትሕ ይቅደም! (አባይነህ ካሴ)

ሞት ከታቀደባቸው በፊት የሞቱት ፍትሕ ይቅደም!

አባይነህ ካሴ

*  በክሱ ሰነድ አጋግሞ የ”ፖለቲካ” ዳቦ መጋገር እንደተፈለገ ግልጥ ነው። ከግለቱ የማትረፍ ዘዴ የተለማመድናት ናት። እነ ጃዋር የተከሰሱበትን እንደሚያደርጉ በዐዋጅ የተናገሩ ሰዎች ናቸው። ያኔ ሳይጠየቁ አሁን መጠየቃቸው ለምን የሚባልበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ያንን በሚያስረሳ አዲስ ድርሰት ልባችንን መስረቅ ልክ አይመጣም
ወንድማችን ነው ያሉት የገንዘብ ጎርፍ ያፈሰሱለት የሚድያ ጣቢያ ማቋቋሚያ የበጀቱለት ጥበቃ የመደቡለት አሁንም በመንግሥት ሥልጣን ላይ መኾናቸውም አልተቀየረም። ይከስሱታል እንጅ አይፈርዱበትም። እንዲያውም በዚህ አያያዝ ሜንጫውን ያቀርቡለት ይኾናል። ኹለት መንግሥት ሲል በጀ ብለው ከርመዋል።
ታስሯል ማለት እና እንደ ብሔራዊ ቡድን ስፖርተኛ ሆቴል ገብቷል ማለት እስኪምታታብን ያደረሰውን አካሔድ በድለላ ሌላ ገጽ መስጠት ቂሎች ስለኾናችሁ እኔ ላሞኛችሁ ነው ነገሩ። ኢትዮጵያውያን “ባለ ሾርት ሜሞሪ ናቸው” የሚለው የአፍ ወለምታ ሳይኾን ሃይማኖት ኖሯል ለካ። ማረሳሻዋ ደግሞ የዐቃቤ ሕግ ክስ ናት።
በሊገድሉ ነው ክስ ልባችንን ለመስረቅ ከምትለፉ የገደሉትን ለፍርድ አቅርቡ። ገዳዮች እናንተ ሳላችሁ ሌላ ገዳይ መያዛችሁ ፍትሐዊ አያደርጋችሁም። ጄኖሳይድ ለመፈጸሙ ፍንጭ የሰጡ ባለሥልጣናት ገለል እየተደረጉ(ምናልባትም እየተሳደዱ) ገዳዮች እየተሾሙ እየተሸለሙ አይደለምን?
የሞቱት እያሉ ሞት በተደገሰባቸው ክስ ልብን ማሞቅ ተገቢ አይደለም። ነገሩ ኦርቶዶክስን የማጥፋት ጄኖሳይድ መኾኑ ከማይሸፋፈንበት ደርሷል። በእኛ ደም የፖለቲካ ትርፍ ማስላት ጭካኔ ነው።
ሰውየውም እኮ “ለኹለተኛ ጊዜ በአሸባሪነት በመከሰሴ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል” በማለት በችሎት ፊት ተናግሯል። ግን ማን ይፈርድበታል? ተከሳሹ – ፈራጅ ነዋ።
፭ ጳጳሳት እና ፪ የማኅበረ ቅዱሳን መምህራንን የመግደል ሴራ እንደነበረ መገለጡ ቢያስቆጣንም ዜናችን አይደለም። በሰፋ ጥቃት ላለ ይህ ዜናው ወይም ሰበር ዜናው እንደምን ይኾናል? እየኾነ ላለው ማጠናከሪያ ሴራ ቢኾን እንጅ የምንገኘው በመኾን ላይ ባለ ጀኖሳይድ ውስጥ ነው። ገዳዮች ሳይጠየቁ አቃጆች መከሰሳቸው ያሳስበናል። ተናብበው የሚሠሩ አካላት የተለያዩ መስሎን መደናቆር አያስፈልግም።
Filed in: Amharic