>
9:50 pm - Tuesday March 21, 2023

እስክንድርን እስላም ጠል፣ ጃዋርን ጳጳስ ገዳይ አስገዳይ አድርገህ ዘብጥያ ታወርዳለህ.. .!!! (ዘመድኩን በቀለ)

እስክንድርን እስላም ጠል፣ ጃዋርን ጳጳስ ገዳይ አስገዳይ አድርገህ ዘብጥያ ታወርዳለህ.. .!!!

 
ዘመድኩን በቀለ

 ሽመልስን ጻድቅ አድርገህ በተላላኪዎችህ በኩል ካባ ታለብሳለህ፣ ታከለ ኡማን ወርቅ በወርቅ አድርገህ ስታበቃ  ፓርቲህ የመላእክት ስብስብ ስለመሆኑ….  ጆሮ ገብ በሆነ ዲስኩርና ተረት ተረትህን ልታደነዝዝ ማይክ ትጨብጣለህ ያኔ ተደጋፊ ተደማሪዎችህ ከየጎሬያቸው ብቅ ብቅ እያሉ ውዳሴ ያዘንቡልሀል ሺህ አመት ንገስ ይሉሀል…
•••
ሽመልስ አብዲሳን ካባ እየሸለምክ፣ ብልጽግናን እንደ መላእክት ስብስብ እያስመሰልክ ትደሰኩርና ለመጪው ምርጫ ከጫወታ ውጪ ሊያወጡህ የሚችሉትንና እርግጠኛ የሆንክባቸውን የባልደራሱን እስክንድርን ነጋን እስላምና እና ኦሮሞ ጠል። ጃዋር መሐመድን ክርስቲያን እና ዐማራ ጠል ጳጳሳትን ገዳይ አስገዳይም አድርገህ ከሰህ ዘብጥያ ታወርዳቸውና በዚያ ትቆልፍባቸዋለህ።
•••
አሁን ጃዋር ጳጳሳትን ሊገድል ነበር ስለተባለ የእስክንድር የግፍ እስር ሊዋጥ ነው ማለት ነው። በመተከል የታረዱት፣ ከአንድ ቤት 7 ነፍስ የጠፋበት፣ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችና ዐማሮች የጅምላ ጭፍጨፋ ጉዳይ አጀንዳው ሊቀየር ነው ማለት ነው። በሆሣዕና፣ በከምባታና በሃዲያ በመሎለሃም በደቡብና በኦሮሚያ የመስቀል ደመራን እንዳያከብሩ የተከለከሉ ኦርቶዶክሳውያን ጉዳይ አጀንዳቸው በጃዋር ክስ አጀንዳ ሊቀበር ነው ማለት ነው አይደል?
•••
ከሞቱት፣ ከተገደሉት፣ ከታረዱት ምስኪን ካህናት፣ ምእመናን፣ አረጋውያን፣ ሴቶችና ህጻናት በላይ ገና በስም ላልተጠቀሱ፣  ለማይታወቁ ሊገደሉ ነበር ለተባሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ሊቃነ ጳጳሳት ነበሩ ተብሎ የኦሮሚያው የዘር ማጥፋትና የመተከሉ ጭፍጨፋ መረሳሳት የለበትም። እስክንድር ነጋም በዚህ አጀንዳ ተውጦ የወንጀለኞች ማጀቢያ የጭዳ ዶሮ ሆኖ መቅረብ የለበትም። ለጃዋር እስር እስክንድርን ማጀቢያ፣ የዘር ማጥፋቱን ወንጀል መሸሸጊያ ማድረግ የለብንም።
•••
የኢትዮጵያ ህዝብ ትንሽ ነገር ስታደርግለት ያመሰግንሃል። ለማስቀየስ፣ አጀንዳ ለማስቀየርም ይመቻል። ባለ ሾርት ሚሞሪ ነው የተባልነው እኮ እንዲሁ እንደዋዛ አይደለም። ለክተውን፣ ገምግመውን፣ ተመራምረው የደረሱበትም ነው። እናም አጀንዳ አንቀይር። ለእኔ ሊገደሉ ነበር ተብሎ አጀንዳ ከቀረበባቸው ሊቃነጳጳሳት እና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ይልቅ ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዘ ዕለት ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ ያለማቋረጥ በከፍተኛ ቁጥር የሚገደሉት፣ የሚታረዱት፣ የሚፈናቀሉት፣ የሚሰደዱት፣ ሃብትና ንብረታቸውን የሚዘረፉት፣ የሚቃጠል የሚወድምባቸው፣ በኢኮኖሚ እንዲደቅቁ የሚደረጉት ኦርቶዶክሳውያን ያሳዝኑኛል። አጀንዳ አንቀይር።
•••
በእኔ በኩል ራሴን ማደስ ይኖርብኛል። ከዛሬ ጀምሮ ቢያንስ ለ7 ቀን ማረፍ ይኖርብኛል። በውስጥ መስመር የሚላክልኝን ዘግናኝ ግፍ እያየሁ ተረጋግቼ ማውራትም፣ ተረጋግቼ መጻፍም የምችል ስላልመሰለኝ ትንሽ ማረፍ እፈልጋለሁ። ከቴሌግራምም፣ ከዩቱዩብም፣ ከፌስቡክም ቢያንስ አንድ ሱባኤ ለ7ቀን ለማረፍ ወስኛለሁ። ትንሽ ልረፍ።
•••
24 ሰዓት፣ 7ቱንም ዕለታት፣ 12ቱንም ወራት፣ 365 ቱንም ቀናት የዓመቱን ሙሉ እኚኚ ችክ ማለቴንም ታስታውሳላችሁ። እናም ጥቂት ቀን ልረፍ። ለልጆቼም ጊዜ ልስጥ። በቂ እንቅልፍም ልተኛ፣ ለሌሎች ወንድሞቼም የመናገርና የመጻፍ ዕድልም ልስጥ። ዓየር ምድሩን ሁሉ ተቆጣጥሬ አላናግር፣ አላጽፍ ያልኩም ስለመሰለኝ ገለል ልበል። እናም ትንሽ ልረፍ።
•••
እናንተ ግን አጀንዳ ግን አትቀይሩ። ደብረ ሊባኖስን ሰብራችሁ ግቡ እያለ በአደባባይ በህዝብ ፊት የሰበራና የግድያ ዐዋጅ ያወጀውን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ከወንጀል ነጻ አድርገህ አስቀምጠህ፣ ካናዳዊውን ደጀኔ ኢብሳን በቦሌ አየር መንገድ በቀይ ምንጣፍ ላይ አስወጥተህ ሸኝተህ ስታበቃ፣ ነፍጠኛ፣ ወራሪና ለማኞችን ወደ መጡበት መመለስ ነው ብለው በሸንጎ የደሰኮሩትን እነ ኦቦ ቀውሲ በላይ መኮንንን፣ ኃይለሚካኤልን፣ በጀት በጅተህ ተንከባክበህ ይዘህ፣ በኦሮሚያ ኦርቶዶክስንና ኦርቶዶክሳውያንን ለማጽዳት በግልጽ እየሠራህ ስታበቃ ጃዋር ጳጳሳትን ሊያስገድል ነበር ብለህ ብትለኝ አልሰማህም። ስንቱን ኦርቶዶክሳዊ ሲያሳርድ፣ ሲያስገድል ከርሞ “ ጃዋር ኦቦሌሰ ኬኛ፣ ኦሮሞን ኦሮሞ ሂንአጄሱ ስትል ከርመህ ድንገት ዛሬ ጳጳሳት ሊያስገድል ነበረ ብትለኝ አልቀበልህም። አዛኝ ቅቤ አንጓች ሁላ። አቡነ ሄኖክ ከወለጋ ወደ ሻሸመኔ የተቀየሩት እኮ የአሁኖቹ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ሰዎች ሊገድሏቸው ስለዛቱባቸው መስሎኝ። ጃዋር ያኔ መች ሃገር ውስጥ ነበር? ብልጽግናስ የጽድቅ ሥራ ለኦርቶዶክስ እየሠራ ነው እንዴ? መንጋውም ቢሆን ጥንቃቄ ብታደርጉ መልካም ነው። ከብልጽግና ሴራ ተነሥታችሁ ሊገደሉ የነበሩት እገሌ፣ እገሌ የተባሉ ሊቃነ ጳጳሳትና ከማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ እገሌና እገሌን ይሆናል ብላችሁ በመላ ምት ለሴራው ጠንሳሾች ሰርግና ምላሽ የሆነ ወጥመድ ውስጥ አትግቡ። ከዚያ በመላ ምታችሁ መሰረት ልክ እንደ ህዝብ አስተያየት መስጫ ግብአት ተጠቅሞ በመላ ምታችሁ መሠረት የተባሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የማኅበሩ ልጆች ላይ እርምጃ ወስዶ “ ብዬ ነበር ” የሚል ቲአትር እንዳይሠራብን እንጠንቀቅ። “ ገዳዮቹ ደግሞ ጳጳሳቱ የሚመገቡበትን ሆቴል እንዲያጠኑ ብሎ ክሱ ላይ መስፈሩ የክሱን አስቂኝነት ይገልጠዋል” ተረጋጉ ፍሬንድ።
•••
ለማንኛውም ልረፍበት። ዛሬ መስከረም 12/2013 ዓም በዕለተ ሚካኤል ዕረፍቴን  እጀምርና እግዚአብሔር ካደረሰን መስከረም 19/2013 ዓም በዕለተ ቅዱስ ገብርኤል ዕረፍቴን እፈጽማለሁ። እረፍቱ ካልበቃኝ ጥቂት ቀናትን እጨምርበታለሁ።
•••
በተረፈ ከብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ጋር የጀመርነውን ለዳሰነች ተፈናቃዮች የሚደረገውን ዕርዳታ ከብፁዕነታቸው ጋር ከተወያየን በኋላ ፈቃደኛ ለሆናችሁ ሰዎች ብፁዕነታቸው የከፈቱትን የባንክ አካውንቱን እሰጣችኋለሁ። በጀመርናቸው በጎ ሥራዎችም ዙሪያ በቴሌግራም፣ በኋትስ አፕና በቫይበር መወያየቱን እንቀጥላለን። ካናዳ የምትገኙትና “ ወገን ለወገን” የሚለውን ግሩፕ የከፈታችሁ እነ ኤልሳም ከኦሮሚያ ተፈናቅለው ሰሜን ሸዋ የፈሰሱትን በመርዳቱ በኩል ከፕሮፌሰር ዳምጠው ጋር የጀመራችሁትን አጠናክራችሁ ቀጥሉበት። የከበዳችሁ ነገር ብቻ ካለ ደውሉልኝ። በአሩሲ ቤቷ የተቃጠለባትን ልጅ ለመርዳት የወሰንከው ኃይልዬም በፈለከው ሰዓት ደውልልኝ። የአዲስ አበባው የተፈናቃዮች እርዳታ አመቻች ቡድንም ሆነ የአሜሪካው ማኅበረ ካህናት በፈለጋችሁት ሰዓት ብትደውሉ ካልተኛሁ በስተቀር ለመመለስ ዝግጁ ነኝ። ከዚያ በተረፈ ግን ሌሎቻችሁ ግን ተፋቱኝ።
•••
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘር ጥፋት መከላከያ ድርጅት Otage Eotc አማካኝነት የታወጀውን የ3 ቀናት የቲዊተርና የፌስቡክ የሃሽታግ ዘመቻ ትቀላቀሉ ዘንድ ዛሬ ወደ ማታ ላይ እለጥፍላችኋለሁ። እስከዚያው እስከዛሬ በፌስቡክ ገጼና በቴሌግራም ቻናሌ ላይ የለጠፍኳቸውን ጦማሮች መለስ ብላችሁ አንብቧቸው። የዛሬ 3 ወር የጀመርኩትን የዩቲዩብ ቻናሌንም ደጋግማችሁ ጎብኙልኝ።
👉 ፌስቡክ ፡ www.fb.com/zemedkunbekeleb
Filed in: Amharic