>
5:28 pm - Tuesday October 9, 1466

መጽሐፈ ጨዋታ፡ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ...!!! (መስፍን ተፈራ)

መጽሐፈ ጨዋታ፡ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ…!!!

መስፍን ተፈራ

የሰውን ገንዘብ የለመደ ሹም ልክ ሥጋ እንደለመደ ጅብ ነው! ፈጽሞ አይቻልም…!
‹‹አለቃ ዘነብ›› በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን የነበሩ ሊቅ ናቸው፡፡ ለንጉሡ ጸሐፌ ትዛዝ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በተጨማሪም የአጼ ሚኒሊክ አማካሪ እንደነበሩም ይነገራል፡፡ አለቃ ዘነብ በሚያዘጋጇቸው ሰነዶች ላይ ሥማቸው ሲጠቀስ ‹‹አለቃ ዘነብ ኢትዮጵያዊ›› በሚል ነው፡፡ ስንቱ ‹‹ዘብሔረ ቡልጋ››፣ ‹‹ዘብሔረ ዘጌ››፣ ‹‹ዘብሔረ ሌላም ሌላም›› ሲል እሳቸው ብቻ ራሳቸውን ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ብለዋል፡፡ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ባንድ ወቅት ስለአለቃ ዘነብ ሲናገር “ምናልባት እሳቸው ራሳቸውን ‘ኢትዮጵያዊ’ ለማለት የተገደዱት አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ አንድነት ካለው ቀናኢ ፍላጎት የመነጨ ሊሆን ይችላል” ሲል ግምቱን አስቀምጦ ነበር።
ለማንኛውም አለቃ ዘነብ ጥሩ ጫዋታ አዋቂና እንደ መፈላሰፍ የሚነካካቸው ሰው ነበሩ። እያዋዙ ማጫወትን፣ ቁምነገር ማስጨበጥን፣ ያልታየውን መፈተሸን ያውቁበታል፡፡ ደግሞ ጨዋታቸው ለሥጋም፣ ለነብስም የሚሆን አይነት ነው፡፡
ከጨዋታቸው ላይ እስኪ ትንሽ ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ…
….
ድንጋይና ጭቃ ቢቀጣጠሉ ታላቅ ቤት፣ ረጅም ቅጥር ይሆናሉ፤ እናንተም መሬታውያን ሰዎች እንደዚህ ብትረዳዱ ጥበባችሁና ኃይላችሁ ከሰማይ በደረሰ፡፡
…..
እግዚአብሔር ፈሪ ነው፤ እኛ በድለነው ልጁን ልኮ ‹‹ቀስ ብለህ ተዛምደህ ና!›› ብሎ በልጁ ታረቀን፡፡ አሁን ምን ያድርጉኛል ብሎ ነው? ለካ በየቤቱ ፍርሀት አይታጣም፤ እኛ ስለበደልነው የምንክሰውን እሱ ካሰን፡፡ እንግዲህ ወዲህ ሥጋችን ከሆነ በሰበብ በአስባብ ብለን እርስቱን እንካፈለዋለን፤ ‹‹ጥቂት ስጋ እንደ መርፌ ትወጋ›› እንደሚሉት እንኳን ልጁን ልኮ ተዛመድን፡፡
…..
የሰውን ገንዘብ የለመደ ሹም ልክ ሥጋ እንደለመደ ጅብ ነው፡፡ ፈጽሞ አይቻልም።
“ባለጠጋ ወደ መንግስተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ መሔድ ይሻላል” ይላል፡፡ ከእርሱ የበለጠ ባለጠጋ አለን? እርሱ በመንግስተ ሰማያት ይኖር የለምን? ይህንን እያመካኘ የሰው ገንዘብ አሻግሮ ማየቱ ምንድነው?
ከዚህ ቀድም አታስቡ እያለ ገንዘባችንን ሊያስበላብንከን፤ ወዲያው ተርቤ አላበላችሁኝም! ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም! ታርሼ አላለበሳችሁኝም! ታምሜ አላያችሁኝም! እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝም! ታስሬ አልጠየቃችሁኝም! ይላል፡፡ ይህን ያህል ስድስት ቃል ምን ያናግረዋል፡፡ …. ከኛ ወገን የተራበ፣ የተጠማ፣ የታረዘ የሌለ መስሎት ይሆን ከሰማይ ተሰዶ መጥቶ ተርቤያለሁ፣ ተጠምቻለሁ፣ ታርዣለሁ ማለት ምንድነው? ሰማይን የሚያህል ሰፊ ሀገር ይዞ አባቱ እዚያ አያበላውም፣ አያጠጣውም፣ አያለብሰውም? ልጁስ ሲቀላውጥ ነውር አይፈራምን?…. እያለ አለቃ ዘነብ ይጠይቃል፤ ይጫወታል፡፡ በነገራችን ላይ ከመቶ አርባ አመት በፊት የተጻፈ ነው፡፡
(ቀንጭቤ ያቀረብኩትን ጽሁፍ ከዚህ ዘመን አማርኛ ጋር እንዲስማማ አድርጌ በመጠኑ ነካክቼዋለሁ…)
ምናልባት መጽሐፉን የማግኘት እድል ለሌላችሁ፣ ገበያም ላይ ስለማይገኝ በሶፍት ኮፒ (PDF) ቀጥሎ ያለው የቴሌግራም ቻናል ውስጥ ታገኙታላችሁ:-
Filed in: Amharic