የአንዳንዶች ነገር …!!!
ሀብታሙ አያሌው
ገዳዮች “በአማራ ጠል ፖለቲካቸው” መርጠው ሲገድሉ እና የህዝብ ብሶት ሲገነፍል “ከኔ በላይ ተቆርቋሪ ከየት ይገኛል” ብለው ሆይ ሆይ ሲሉ ከርመው “አሜሪካ ሆኖ ብአዴንን መተቸት አይቻልም” የሚሉት ነገር ይገርመኛል።
ብአዴን 27 ዓመታት በሙሉ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ውጪ የሚያስብ አንድም ግለሰብ ሆነ ድርጅት እንዳይኖር የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሲያስር፣ ሲገድል፣ ሲያሰድድ የኖረ ቡድን መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ከዚያ ጥዩፍ ተግባሩ ቢማር መልካም ነበር። ነገር ግን ያ አልሆነም።
አሁንም ባለፉት ሁለት አመታት የብአዴን ጉዞ የለመደው እሽክርና እያስጎነበሰው ቀና ማለት እንደተቸገረ ነው። ትላንት ህወሓት ለተባለ ቡድን ዛሬ ለኦህዴድ ገብሮ መኖር በመረጠ ስብስብ የአማራን ህዝብ ከጥቃት መታደግ የማይቻል መሆኑ ግልፅ ሆኗል።
በኔ እይታ ልሂቃኑ ከስሜት በራቀ መንገድ የክልሉን ህዝብ ከተጋረጠበት አደጋ የሚታደግ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተገቢውን ሚና የሚጫወት የኢትዮጵያን አንድነትና ከፍታ ለማረጋገጥ ትልቁን ምስል ከማየት የሚጀምር አማራጭ የፖለቲካ ኃይል (ፓርቲ) ማደረጃት ቢያስቀድሙ ይበጃል።
ወቅቱን ያገናዘበ ትግል ማድረግ ወሳኝ ነው። ብአዴን ይሄንኑ ግብር የኦህዴድ ገባሪ ስልጣኑን ለማስቀጠል የማራን ህዝብ ወደ ጎጥ ፖለቲካ አውርዶ እርስ በእርስ እያናቆረ እነሱ ከሌሉ ክልሉ ይፈርሳል የሚል የሞኝ ዘፈን እያዘፈኑ እንዳይቀጥሉ ብርቱ ትግል ማድረግ ወሳኝ ነው።
ብአዴን ከከፍተኛም ሆነ ከመካከለኛ አመራሩ መካከል የተሻሉ ጥሩ አመራሮች እንዳሉ አይዘንጋ። የህዝባቸው ስቃይ የሚያማቸው የገባሪ ፖለቲካን የሚፀየፉትን በሚገባ አክብሮ ማገዝ ፣ የትግል አጋር ማድረግም ያስፈልጋል። በፅናት እየታገሉ ያሉ የአብን አመራሮችን ማበርታት እና ከወሬ በዘለለ ሁለንተናዊ ድጋፍ ማገዝ የትግሉን መንገድ ቀሊል ያደርገዋል።
ትግልን ቦታ እንደማይወስነው በእርቀት እንደማይበየን ለማወቅና በቂ ትምህርት መውሰድ ካስፈለገ ይህንን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሃቀኝነት ፈርጥ ሆና ብቅ ያለችውን የአባይ ሚዲያዋ መዓዛ መሐመድ ያቀረበችውን ትንተና አብነት ማድረግ ብዙ ያተርፋል።
መለስ ብሎ ማስታወስ ቢያስፈልግ በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረውን ኢህአዴግን ለመገርሰስ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ከባታልዮን ጦር በላይh) የሆነ ብዕሩን ሲያሰልፍ አንዳንዶች “ኢህአዴግ ከፈረሰ አገር ይፈርሳል ፣ ተተኪ አልተዘጋጀም ” ሲሉ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም … ተሜ “ሰው በመረጠው ይታገል” ብሎ እሱ ትክክል ባለው መንገድ ትግሉን መቀጠሉ በውጤት ሚዛን እንዲለካ ማድረጉ ማስታወስ በቂ ትምህርት ይሰጣል።