>
5:28 pm - Tuesday October 10, 8034

ፕሮፌሰርን በሓሳቦቻቸው እናስባቸው !  (ቤላ ዳንኤል)

ፕሮፌሰርን በሓሳቦቻቸው እናስባቸው !

 ቤላ ዳንኤል

 

* “ያስፈራል፤ ግን ኢትዮጵያ አትፈርስም !”
(ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም | 2004 )
” …… ችጋር የአገዛዝ ስርአት ውጤት … ነው….!”
ይቺ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ስንት የመከራ ወንዞችን ተሻግራለች! ገና ስንት ትሻገራለች! ስንት የግፍ ተራራዎችን አቋርጣለች! ገና ስንት ታቋርጣለች! ስንት የበደል ሰይፎችንና ጦሮችን አምክናለች! ገና ስንት ታመክናለች! ስንት የውጭ ኃይሎችን አሳፍራለች! ገና ስንቱን ታሳፍራለች! ስንት አምባገ- ነኖችን እያለቀሰች ቀብራለች! ገና ስንቱን ትቀብራለች!
የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ ግለሰቦችና መንግሥቶች ሞልተዋል፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ ጭንጋፍ ልጆችም አሏት፤ ማኅጸንዋ እየደማ እየረገማቸው ሰላምና እንቅልፍ አጥተው አብጠው ይፈነዳሉ፤ የኢትዮጵያን መፈራረስ የሚመኙ መንግሥቶች ሁሉ ከዚህ በፊት ቀድመው ፈራርሰዋል፤ ወደፊትም ይፈራርሳሉ።
አንዳንዶች ቢጨነግፉም፣ አንዳንዶች ቢክዱም፣ አንዳንዶች ሆዳም ቢሆኑም ፣ አንዳንዶች ቢወላውሉም፣ ኢትዮጵያ ልጆች አሏት፣ አሁንም የሚሞቱላት፣ ያልበሏት፣ የሚሳሱላት፤ ያልሸሿት፤ አፈሯን የሙጢኝ ብለው አፈርሽ እንሁን የሚሏት፣ ደሀነትም ሆነ ጭቆና ካንቺ አይለዩንም የሚሏት፣ ኢትዮጵያ ዛሬም ልጆች አሏት ስትፈርስ ቆመው የማያዩ፣ ሲያማት ነፍሳቸውን ዘልቆ የሚያማቸው፣ ሳልፈርስ አትፈርስም ነው ቃል ኪዳናቸው።
….
ኢትዮጵያ ትወድቅ ይሆናል፤ ግን ያለጥርጥር ትነሣለች፤ በፊትም ወድቃ ተነሥታለችና፤ ኢትዮጵያ ትሰነጠቅ ይሆናል ፤ ግን ያለጥርጥር ትገጥማለች፤ በፊትም ተሰንጥቃ ገጥማለችና፤ ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙላት የአየሉ ቢመስሉም የንስሐ ጊዜ ስትሰጣቸው ነው፤ ኢትዮጵያ ዕብሪተኞችንም ትሕትና ታስተምራቸዋለች፤ ዕብሪተኞች ከነዕብሪታቸው በራሳቸው እሳት ቀልጠው እስቲያልቁ ኢትዮጵያ ትእግስትዋ አያልቅም፤ ኢትዮጵያ ትእግስት ነችና።
በበጎ መንፈስ እስከተመራን ድረስ፣ ፍርሃትንና አለመተማመንን፣ ጥላቻን፣ ጠብንና ድብድብን፣ ሊዘሩብን ከሚፈልጉ ርኩሳን መናፍስት ከራቅን ኢትዮጵያችን አትፈርስም፣ የደፈረሰውም ቶሎ ይጠራል።
 
.*     *      *
” …… ችጋር የአገዛዝ ስርአት ውጤት … ነው….!”
(ከአድማጭ ያጣ ጩኸት – መፅሐፋቸው)
.
.
ችጋር የሰው ልጅ እንደ ማገዶ እንጨት ተለብልቦ የሚያልቅበትና ቀባሪ እንኳን የማያገኝበት የውርደት ሞት ነው ። የሰው ልጅ ውርደት ነው ። የሕብረተሰብ ውርደት ነው ። የአገር ውርደት ነው ። አስቡት ቁራሽ እንጀራ ወይም እፍኝ ቆሎ የሚሰጥ ዘመድ ፣ ወይም ወዳጅ ፣ ወይም ወገን ጠፍቶ ለነፍሱም ይሁን በሰብአዊ ርሕራሄ ተነሳስቶ ፣ የሚረዳ ጠፍቶ  በሺና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየቤታቸው ፣ በየመንገዱና በየገበያው የሚወድቁበት ሁኔታ ነው ።
.
ችጋር የሚመጣው በድርቅ ፣ ወይም በተምችና ሌሎች የተባይ ሰብሎች ወይም በዝናብ ብዛትና በበረዶ ወይም እግዚአብሔር በመቆጣቱ ፣ ወይም በነዚህ ሁሉ ነው ይባላል ። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የሚደረደሩት ሆን ተብሎ ኃላፊነቱ በማንም ላይ እንዳያርፍ ለማድረግ ነው ። ሁሉም ከእውነቱ የራቀ ነው ። እውነቱ ነገር እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ችግሮች ቡብዙ አገሮች ይከሰታሉ ። ሆኖም በዚህ ምክንያት ሰዎች በችጋር አለማለቃቸው ነው ። እውነቱ ችጋር የአገዛዝ ሥርአት ውጤት መሆኑ ነው ። እውነቱ ነገር ችጋር ኅብረተሰብ በአገዛዝ ስርአት ደንዝዞና በራሱ የኑሮ ትግል ተተብትቦ የመተሳሰብና የመረዳዳት መንፈሱ የተሟጠጠ መሆኑ ነው ። እውነቱ ነገር ችጋር የሚጀምረው የድርቅ ወቅት ከመድረሱ በጣም በጣም ቀድሞ መሆኑ ነው ።  ……… “
እግዚአብሔር ነፍሶትን በአፀደ ገነት ያሳርፍ !
Filed in: Amharic