>

በዓላት የሚፈሩበት ዘመን...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

በዓላት የሚፈሩበት ዘመን…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

የባዕላት ቀን የደስታ እና የአብሮነት መገለጫ መሆናቸው ተረት እየሆነ ይመስላል። ባዕላት መፈራት ጀምረዋል። የፍርሃቱ ምንጭ ደግሞ አንድም የሕዝብ ቁጣ ሊፈነዳባቸው ይችላል፣ በሥርዓቱ ላይ ያኮረፉና የተበሳጩ ሰዎች አመጽ ሊያስነሱ እና በዓሉን ለተቃውሞ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይችላሉ ከሚል የመንግሥት ጥልቅ ስጋት የመነጨ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ባዕላትን ለሽብር አደራጎት አመቺ እድል አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ የሚያሳዩ የተደራጁ የፖለቲካ ጏይሎች መኖራቸው ነው። ከስንት አመታት በኋላ አዲስ አመት፣ መስቀል እና ኢሬቻን አዲስ አበባ ሆኜ ሲከበሩ ለማየት ችያለው። መሬት ላይ ያለው ድባብ ባዕላቱ መጡልን የሚል የደስታ ስሜት ሳይሆን መጡብን የሚል የሽብር ስሜት ነው ያየሁት።
ዱሮ የባዕላት ድምቀት ከዋዜማ በፊት ነበር የሚጀምረው። አሁን ደግሞ በጊዜ ግቡ፣ ከቤት አትውጡ፣ እረብሻ ሊነሳ ይችላል፣ የሽብር ጥቃት ይኖራል የሚሉ ወሬዎች ከእንኳን አደረሳችው በፊት ቀድመው ይሰማሉ። ይሄ በሕዝቡ መካከል ያለ ስሜት ብቻ ሳይሆን የአገዛዝ ሥርዓቱ ሚድያዎች እና ሹማምንቱም በቴሌቭዥን መስኮትና በራዲዬን ብቅ እያሉ ይሄንኑ ሽብር ሲነዙ ነው የሚውሉት። ከባዕላት ቀናት ቀደም ብላችሁ የአገሪቱን መገናኛ ብዙሃን ብትመለከቱ እነገሌ ባዕሉን ሊያደፈርሱ፣ አደጋ ሊያደርሱ፣ ሕዝብ ሊጨርሱ አሲረዋል፣ ታጥቀዋል፣ ተደራጅተዋል ተጠንቀቁ የሚል ማስፈራሪያ አዘል የሽብር ዜናዎች ነው የምትሰሙት። እንዳንዴ የምትለብሱትና የምትይዙት የበዓል ማድመቂያ ነገርም በመንግስት ይመረጥላችዋል። ወደ በዓሉ ሥፍራ የምትመጡ ሰዎች ይሄን መልበስ ወይም እንዲህ ያለ ባንዲራ መያዝ አትችሉም ትባላላችው።
ባዕላትን ከሽብር ስሜት ነጻ ህኖ በደስታና በፌሽታ ማክበር ድሮ የቀረ ይመስላል። ዛሬ በባዕላት ዋዜማ ሰዎች እየተደዋወሉ እረ በግዜ ግቡ፣ ከቤት አትውጡ ሲባባል ነው የምትሰሙት። በማህበረሰቡ ውስጥ የሽብር ስሜት ተንሰራፍቷል። ቅዳሜና እሁድ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል ትላንት አርብ የአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች ገና በጊዜ ጭር ብለው ነበር። ሕዝቡ ከምሳ ሰዓት በኋላ ስራውን ጥሎ፣ ንግድ ቤቱን ዘግቶ ወደ ቤቱ እግሬ አውጪኝ ብሏል። ብዙዎችን ለማናገር ሞክሬ ነበር መንግስት ሽብርተኞችን ይዣለው ማለቱን ተከትሎ ነዋሪው ስጋት ውጥ መውደቁን ተረድቻለሁ።
ሕዝብ ልጆቹን ይዞ አደባባይ በመውጣት በመደሰቻው ቀን አደጋ ይደርስብኛል፣ አመጽ ይነሳል፣ ቤተሰቤ አደጋ ላይ ይወድቃል ብሎ በስጋት ከራደና ሽብር ውስጥ ከወደቀ በመንግስትና በጸጥታ ጏይሉ ላይ እምነት አጥቷል ማለት ነው። እነዛ ሰሞኑን ድንጋይ በጭንቅላታቸው እየፈጩ  እና በአየር እየተገለባበጡ ወታደራዊ ትዕይንት እያሳዩ በነበሩ ፖሊሶችም ላይ እምነት አላሳደረም ማለት ነው። ይሄ ለአንድ አገር ትልቅ ውድቀት ነው።
እንደ ዱሮው ባዕላቶቻችንን ያለምንም የሽብር ስጋት በየአደባባዩ በነጻነት የምናከብርበትን ጊዜ ያምጣል!!
Filed in: Amharic