የጌታቸው ረዳ መወራጨት ምን ይነግረናል?
ሙሉአለም ገብረመድህን
ትሕነግ በታሪኩ (ሁለተኛ) ተተኪ ትውልድ አፈራ የሚባልለት ብቸኛ ሰው ቢኖር አቶ ጌታቸው ረዳ ነው፡፡ ከደደቢት እስከ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት፤ ከምኒልክ ቤተ መንግሥት እስከ መቀሌ ድረስ በጥቅሉ አርባ ስድስት ዓመት ባስቆጠረው የድርጅቱ ታሪክ ውስጥ ከፊት መስመር ተሰላፊዎቹ በረኸኞቹ ናቸው፡፡ ጌቾ የድኀረ መለሱ የትሕነግ ፖለቲካ ነድቶ ወደፊት ያመጣው ሰው ነው። አሁን ላይ የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ እና በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአማራና የፌዴራል ባለሥልጣናትን ተሳዳቢ የሚል “ማዕረግ” አለው። እነሱ በፖለቲካ ቋንቋ “ቃል አቀባይ” ይሉታል። በግብር ሌላ ቢሆንም!
***
ስድብ አድራሽና ጉዳይ ገዳዩ ሰውየ ይህችን ጽሁፍ ከመጻፌ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ቃለ መጠይቅ የሰጠው ቅዳሜ ምሽት በትግራይ ቲቪ ላይ ነበር። ቃለ መጠይቁ ተጨምቆ ከ 7 ደቂቃ የማይበልጥ ቢሆንም አንዴ የተናገረውን አስር ጊዜ እየደገመ 55 ደቂቃ ያህል አውርቷል።
አገሪቱ ኢትዮጵያ ሆና ነው እንጅ፣ በምዕራቡ ዓለም የአንድ ሰው ወቅታዊ ስነ ልቦና በአነጋገሩ፣ በአካል እንቅስቃሴውና መሰል ጉዳዮች ትንታኔ ተሰርቶበት ሊታወቅ ይችል ነበር። በእኛ ሀገር ግልፅ የሆኑ ስሜቶች የሚነበቡበትን ካልሆነ በስተቀር ሌላው ላይ አይተኮርም። (በዚህ ጉዳይ ላይ Getachew Shiferaw ተመሳሳይ አስተያየት ፅፎበት ያውቃል። የሞክሸህን ጉዳይ ግፋበት)
የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ፖለቲካዊ ዐቅመ ቢስነታቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑ ነው። የጌታቸው ረዳን ቃለ መጠይቅ ሙሉውን የተመለከተ ሰው ይህን መረዳት ይችላል፡፡ ብዙ ከደጋገመው ቃላት ይልቅ በቃለ መጠይቁ የታዩ ተጓዳኝ ነገሮች የትህነግን ወቅታዊ አቋም ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ ደክሟቸዋል! ፈርተዋል!!
ጌታቸው ረዳ ከጉዳይ ገዳይነት ሚናው የተነሳ ተሳዳቢ ‘’ፖለቲከኛ’’ ነው። ተሳዳቢነት ደግሞ ምንም ያለማድረግ የተሸናፊነት ምልክት ነው። በዚህኛው ቃለ መጠይቅ ግን ደጅ የሚጠና ሰው መስሎ ቀርቧል። ጌታቸው ተሳዳቢ ቢሆንም ከአሁን ቀደም በሚያደርጋቸው ቃለ መጠይቆች ከስድብ ባሻገር ማስፈራሪያና ጉራ አይለየውም ነበር። ዛሬ ያች ድንፋታ እንደ ጉም በናለች። ምንም ማድረግ ያልቻለው ወይንም የከበደው ነገር እንዳለ ከአቅመ ቢስ ተልመጥማጭ ንግግሩና እንቅስቃሴው መረዳት ይቻላል።
በቃለ መጠይቁ ስሜቱን ለመግፅ እንኳ ያልቻለባቸው ጊዜያት አሉ። የሰውነቱ ሁኔታ፣ የአንደበቱ መርበትበት፣ የቃላት ድግግሞሹ፣… አፉን ከፍቶ ከስድስት ሰከንድ በላይ መቆየቱ፣… ጮክ ባለ ሁኔታ ስለ ትሕነግ ‘መብረጅረጅ’ ያሳብቃል። ለወትሮው “አውቃለሁ” ባይ ነበር። ዛሬ ግን ያችን አስመሳይነቱን እንኳ አልቻለባትም፡፡
ምንም እንኳ ሚዲያው በቀጥታ በትህነግ የሚመራ፣ የድርጅቱ የግራ ጥፍሩ (አማራንና የፌዴራል መንግስቱን መቧጠጫ) ቢሆንም ጋዜጠኛዋን ለማዘዝ አልተሳካለትም። ተጽፎ የተሰጣትን ትጠይቀዋለች፤ ቃላት እየደረተ ከመስመር ይወጣል። ሚዲያዎች ላይ ቀርቦ ያደርገው ከነበረው ከእስካሁኖቹ ቃለመጠይቆቹ እጅግ የተለየ አቅም ያጣበት ነበር። እርግጠኛ ሆኖ መናገር አልቻለም። ፊቱ ላይ ፍርሃት ጮክ ብሎ ይነበባል! መሀሉን ለለመደ የዳር አገር ፖለቲካ እንዲህ ነው የሚያብረጀርጀው!
***
የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሊያገኝ የሚገባውን የ100% ጥቅም ዛሬ በነሱ ስግብግብነት ቁልቁል ከተውታል። የዝህች አገር ድርሻው 6% ሆኖ እንዲገደብ አድርገውታል። ይህን የኪሣራ ውጤት “ትግል” ሲሉ ይጠሩታል። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ተጠቅልሎ ተይዞ የኖረው ሥልጣን ዛሬ ላይ ከእጅ ሲወጣ ትግራይን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ አደገኛ ቀመር ሆኖ ተገንቷል፡፡ ዛሬ የትሕነግ አባላትም ሆኑ ደጋፊዎቹ ዳር ይዘው ‹‹ፖለቲካ ብዙ በወለደ አይደለም›› በሚል ቢፎክሩ፤ ቢራገሙ ከሁሉ በፊት ወቀሴታው መቅደም ያለበት በታሪክ ፊት ተሸናፊ ለሆነው ለራሳቸው ድርጅት ነው። ወደፊት መመለሱ አይቀርምና የተዘረፉ መሬቶችን ሳይጨምር “የትግራይ ክልል” እየተባለ በሚጠራው የጠበበ ምድር ላይ ተወስነው እንዲቀሩ ራሳቸው ናቸው ታሪካዊ ስህተት የፈፀሙት።
***
የጌታቸውን አለቆች በተመለከተ ሁለት ነገር ብቻ ልበል፡፡ አሁን ገጥሟቸው ያለው ሽንፈት በታሪክ ፊት የመዋረድ ያህል ነው፡፡ አለን ይሉት የነበረውን ሞገስ ነው የተነጠቁት! ያ ሞገስ ዛሬ ተገፏል፡፡ ሲገፈፍ ደግሞ የግለሰብ ተክለ-ስብዕና ብቻ ሳይሆን የድርጅት ታሪክንም ይጨምራል፡፡ አመራሩ ተጭኖት የኖረው የቁስ ሰቀቀን አወዳደቁን አክፍቶታል፡፡ አይጣል በታሪክ ፊት ተሸናፊነት ‘ቁርበት አንጥፉልኝ’ ለማለት እንኳ ዕድል አይሰጥም። ፕላኔት ሆቴል እየተኙ በእንቅልፍ ልብ ማዕከላዊ ማሳለፍ ከውርደትም በላይ ነው፡፡ የ20 ዓመት ልጃገረድ አቅፎ እያደሩ በቅዥት ውስጥ የ27 ዓመት የክስ ቻርጅ ሲሸሹ ማደር ጥልቅ ተሸናፊነት ነው፡፡እንደ ትላንቱ ሁሉ ለዝሙት ተግባር ዱባይና ሩቅ ምስራቅ አገራት ድረስ ቪያግራ ተሸክሞ መዝመት ቢቀር፣ ዛሬ ለህክምና ከአገር መውጣት ብርቅ ሆኖ ባቸዋል ፤ አሁን ከዚህ ኑሮ ሞት አይሻልም !?
ግፍና እብሪት መጨረሻው ይሄው ነው። ከሞት የከፋ ጥፋት ያደረሱባት ኢትዮጵያ አንቅራ ተፍታቸዋለች!