>

አዲስ አበባ - ለሆድ ቁርጠት መነጽር ታዘዘላት ! (ሀብታሙ አያሌው)

አዲስ አበባ – ለሆድ ቁርጠት መነጽር ታዘዘላት !

ሀብታሙ አያሌው

“ኮድ 2 እና ኮድ 3  የግል ኦቶሞቢሎች በስራ መውጫ እና መግቢያ ሰዓት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ትዕዛዝ ሰጥተናል”
             አቶ ጅሬኛ ሄርጳ (ዋና ዳይሬክተር)
* የተሽከርካሪ መጋራቱ ነገር ፌክ ኒውስ መስሎኝ ትቼው ነበረ? እውነት ከሆነ በጣም አስቂኝ የሆነ የለየለት መሳቂያ መሳለቂያ የሆነ እቅድ ነው። የአንድ ንብረት ባለቤት የማያውቃቸውን እንግዳ ሰዎች በስራ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ በገዛ ንብረቱ የሚገደድበት ግዴታ ከየት የመነጨ ነው? በሀሳብ የመከኑ ሰዎች ይህን መንግስት ከበውት ይታየኛል።
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሥተዳደር እንኳን ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ አገር አንድ ትንሽ መንደር ማስተዳደር የማይችል በብሔር የተሰባሰበ ደካማ ቡድን መሆኑን ለመረዳት የትራንስፖርት ፍሰትን ለማስተካከል ምን አይነት ሌላ ውስብስብ  ችግር እና ቀውስ ሊሚፈጥር የሚችል አጀንዳ ይዞ እንደመጣ ተመልከት።
የግል መኪኖች የትንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንፈቅዳለን ቢሉ  እሰየው።  እነሱ እያሉ ያሉት በግል መኪና በግድ ሰው ካልጫናችሁ መኪናችሁን ማንቀሳቀስ (መንዳት) አትችሉም ነው።
የከተማዋ ዋና ችግር የትራንስፖርት እጥረትና  የትራፊክ ፍሰቱን በሚገባ የሚያስተናግድ መንገድም ሆነ የትራፊክ መብራቶች፣ ምልክቶች፣ ስርአቱን የሚቆጣጠር የትራፊክ መቆጣጠሪያ ካሜራም ሆነ ፖሊስ አለመኖር ነው።
መንገዶች እንዳይዘጋጉ የመንገድ አጠቃቀም ስርዓቱን ስለማዘመን፣  አዲስ አበባ እድገቷን፣  የህዝቡንና የትራንስፖርቱን ብዛት የሚመጥን በቂ መንገድ መገንባት፣ የትራንስፖርት መኪኖች የታክስ ስርዓት ላይ ማበረታቻ አድርጎ  የግሉን ክፍለ ኢኮነሚ ማነቃቃት፣ የግል መኪና (የቤት ኦቶሞቢል) በስራ መውጫና መግቢያ ሰዓት የትራንስፖርት ስራ እንዲሰሩ መፍቀድ ማበረታታት ሲገባ መንግስት ነኝ የሚለው አካል ሌላ ችግር እየወለደ ይገኛል።
የትራንስፓርት መስኩ ላይ አብይ አህመድ የመደባቸው ዳይሬክተር አቶ ጅሬኛ ሄርጳ  ይህው ቀልዳቸውን ቀጥለዋል። ለሆድ ቁርጠት መነጽር የሚያዙ ባለሞያዎች እነ ጅሬኛ የሚቀልዱብሽ አዲስ አበባ ሆይ ፅናቱን ይስጥሽ።
PS
—-
የትራፊክ ፍሰቱ የሚታይበት ፎቶ አዲስ አበባ 22 ማዞሪያ አካባቢ ዘሪሁን ህንፃ  ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጎዳና አካባቢ ምሽት 1 :30 አካባቢ የተነሳ ፎቶ ነው።
Filed in: Amharic