>

ጀግናችንን ሸኘን፤ ቀብሩም ክብራቸውን እና ሥራቸውን በሚመጥን መልኩ ተከወነ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጀግናችንን ሸኘን፤ ቀብሩም ክብራቸውን እና ሥራቸውን በሚመጥን መልኩ ተከወነ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ኖሮ መሞት ምን እንደሆነ በተግባር ያሳዩኝን አባቴን ፕሮፌሰር መስፍንን በአካል ተገኝቼ ለመቅብር በመቻሌ ፈጣሪን አመሰገንኩ። ኖሮ ላለፈ ሰው ሞት ጥሩ እረፍት ነው። ይብላኝ ለኛ ለቀረነው ከእድሜያችን ውስጥ ከኖርንበት ያልኖርንበት ዘመን ሚዛን ለሚደፋው። በፍርሀት ቆፈን ለተያዝነው፣ በንዋይ ፍቅር ለዋልነው፣ ሆዳችን ያባውን ለመተንፈስ ብቅል መቅመስ ግድ ለሚለን፣ አንገታችንን እንደ ሰጎን አሸዋ ውስጥ ቀብረን ለግፍና ለግፈኞች የዝምታ ድጋፍ ለምንቸረው፣ ላለፈ ላገደመው ሹመኛ ሁሉ ጭብጨባና ፉጨት እየለገስን ስልጣን መባለጊያ እንዲሆን ላደረግነው፤ ይብላኝ ለኛ ሰው ሆኖ መኖርን በርቀት እያየን በእድሜ ጠገብ ጉዞ ሳንኖር ለምናልፈው። ፕሮፌሰር እነዚህን ሁሉ አሸንፈው፤ ሰው ሆነው ኖረው ሰው ሆነው ያለፋ ናቸው።
ሰው ሆኖ፣ እንደሰው ተከብሮ፣ ለሰው ክብር ሲል ተገፍቶና ተዋርዶ ከሰውነት ጸጋ ሳይጎድል ሰው እንደሆነ ለማለፍ የወደደ ሁሉ የጋሽ መስፍንን ዱካ ይከተል።
ከሰውነት ከመጉደል ያውጣችሁ! 
የጋሽ መስፍንን ነፍስ በአጸደ ገነት ያኑርልን!
Filed in: Amharic