>

ያለ ምንም ደም፣ ኢትዮጵያችን ትቅደም! (አሰፋ ሀይሉ)

ያለ ምንም ደም፣ ኢትዮጵያችን ትቅደም!

አሰፋ ሀይሉ
(ሠማዩ ቢጠቁር፣ በሥጋት ቢቀልምም…)

“መንገሥ ከሚያባላስ – መጥገብ ከሚያቃቅር – ማግኘት ከሚያጎድለን፥
ማጣት ውሎ ይግባ – ባርነት ይሰንብት – ድህነት ይግደለን!
ከረፈደ ፀፀት – ደረት እየደቁ – ከእግዜር ቢዋቀሱ፥
ትርጉሙ ምንድነው – ሲኖር ተቃቅሮ – ሲሞቱ ማልቀሱ!”
          (- ከምስጋና ጋር፦ ከወጣት ገጣሚ ሕሊና ጌታቸው)
የአብይ የሕልም መንግስት በዚህ መልኩ ሀገሪቱን መምራት ይሳካልኛል ብሎ ከቀጠለ በመጨረሻ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እስከወዲያኛው መሠናበቱ አይቀሬ ነው። በከፍተኛ ሕዝባዊ ፕሮፖጋንዳና ወታደራዊ ዝግጅት ላይ ተጠምደው የከረሙት የኢትዮጵያ ተረኛ ገዢ ነን ብለው የተነሱት ኦሮሚያ ተብዬዎቹ ምኞታቸው እንደማይሳካ ሲረዱ የቢሊሱማ ሪፈረንደም እናደርጋለን ብለው በአጭር ጊዜ መነሳታቸውም አይቀሬ ነው። በአሁኑ የሀገሪቱ የተበታተነ ወቅታዊ አቋም በወታደራዊ መንግሥት ከሚመራ ወታደራዊ ኃይል ውጪ አሁን ሥልጣኑን የሙጥኝ ብሎ በያዘው የአብይ አህመድ የይስሙላ አስተዳደር ያንን የሪፈረንደም አደጋ ሊገታ የሚችል የተባበረ ኃይል የለም።
በሌላ በኩል የትግራዩ ዘረኛ ቡድን (ወያኔ) የህልውናዬ ምንጭ ነው የሚለውን የጎሳ ሥርዓትና ሕገመንግሥት ከመፍረስ ለመታደግና ራሱንም በቁሙ ከመበላት ለማትረፍ በየስፍራው ያሉ ጀሌዎቹን ሰብስቦ ተኩስ ማስጀመሩም አይቀሬ ነው። ከወያኔ ጋር የሚደረገው አይቀሬ ጦር መማዘዝ ይቅርና በወያኔ ላይ እየተደገሱለት ያሉ የገንዘብ ማሽመድመድ (ፋይናንሺያል) እርምጃዎች በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ከባድ ጦስና መዘዝ ይዘው መምጣታቸው አይቀሬ ነው።
በተላላኪነት ወደር ያልተገኘለት የአማራው የሥልጣን አልቅት ብአዴን ደግሞ ከራሱ ከአማራው ሕዝብ በቅርቡ የሚቀሰቀስበትን አመፅ ሊያስቆም የሚያስችል ቁመናም ሕዝባዊ ድጋፍም የለውም። ያ ከመሆኑ በፊት ሕዝባዊ አብዮት ከክልሉ አስቀድሞ ሳያፈናቅለው ለመክረም ከታደለ ግን የመጨረሻ ወኔውን አሟጦ በቄሮው መንግሥትና በጎረቤት ኃይሎች አይዞህ ባይነት ከወያኔ ጋር ጦር ለመማዘዝ መነሳቱ አይቀሬ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ የማዕከሉን የልብ ትርታ እየተከተሉ በማዕከሉ ወታደራዊ ጥላ ከለላ ሥር ተጠልለው በፅሞናና በፀባይ ከተረኛው ኃይል ጋር እየተራመዱ ያሉት የደኢህዴን ጥገኛ ዘረኛ ኃይሎችም በበኩላቸው የሚከሰትን ማንኛውም ሀገራዊ አጋጣሚ በመጠቀም በየአካባቢያቸው የበላይነትን ለማረጋገጥ ሲሉ እርስ በእርስ ወደ ደም አፋሳሽ ግጭት በሚገቡ ኃይሎች መታመሳቸው አይቀሬ ነው። የተከፋፈለውና የተዳከመው የክልሉ የሥልጣን ኃይል ግጭቶቹን የሚገታበት ጉልበቱም ተሰሚነቱም የለውም።
የሶማሌ ክልል ተብሎ በሚጠራው ሰፊ ምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍልም እንዲሁ በአብይ መንግሥት ጥላ ከለላ ተሰጥቶት ሥልጣን ላይ ያለው አካል ባመረሩና ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቀባይነት ባላቸው የሶማሊ ኃይሎች ተገፍቶ ክልሉን ጥሎ መሸሹ አይቀሬ ነው።
ዓይን ባወጣው የአብይ አህመድ፣ የነታከለ፣ የእነ አበቤና በአጠቃላይ የኦሮሙማው አስከፊ የተረኝነት፣ የክልከላና የዝርፊያ አገዛዝ ተማርሮ ለአመፅ አመቺ አጋጣሚውን እየጠበቀ ያለውን የአዲስ አበባ ሕዝብ (በተለይም በሚሊየን የሚቆጠረውን የአዲስ አበባ ወጣት) እስከመጨረሻው በጠብመንጃ ኃይል ብቻ አስፈራርቶና አፍኖ ማስቀረት አይቻልምና በአንድ ቀውስ መነሻነት ሰበብ ብሶቱ ገንፍሎ መውጣቱና ሕዝባዊ አመፅ መቀስቀሱ አይቀርም። ጉልበት ብቻውን ኃይል አይሆንም። የ97ቱን የአዲሳባ አመፅ አኳኋን ያየ ዳግም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚፈነዳን ሕዝባዊ አመፅ በጠብመንጃ ኃይል ደም በማፍሰስ አቆማለሁ ብሎ የማሰቡን ቅዠትነት ፈፅሞ አያጣውም።
አሁን በኮሮና ሰበብ በአስቸኳይ አገዛዝ ሥር የወደቀችው ኢትዮጵያ ተመልሳ ዓይኑን ባፈጠጠ ቁርጡ የታወቀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥጥር ሥር ተመልሳ መግባቷም አይቀሬ ነው።
የሐይማኖት መነሻ ያላቸው የእርስ በእርስ ግጭቶችም በየስፍራው ተቀባብለው በተቀመጡ አክራሪዎች ቀስቃሽነት መነሳታቸው አይቀሬ ነው።
ዕለት በዕለት ወደ አዘቅት እየገባ ያለውን ኢኮኖሚም ሀገራዊው የገንዘብ ርጭት ሊሸከመው የማይችልበት ደረጃ የሚደርስበት ቀን ሩቅ አይደለም።
እንደ ጎረቤት ሀገር ግብፅ እጅግ ጠንካራ ተሰሚነት ያለው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመሐል ጣልቃ ገብቶ ካላስቆመው በስተቀር በኢትዮጵያ ቢያንስ ለወራት ዕድሜ የሚቆይ ሲቪል ዎር (የእርስ በእርስ ጦርነት) የመቀስቀሱ ዕድል በጣም አሳሳቢና ከፍተኛ፣ ከፍም ሲል ፍፁም አይቀሬ ነው።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከረዳት ከዚህ ሁሉ ሀገራዊ ጦስም በፊት አንድ ሌላ መፍትሄም አለ። የወያኔ ወራሽ ለመሆን በመመኘት ሞቶ ያልተቀበረውንና ሀገሪቱን ወደመበታተን ጫፍ ያደረሳትን ዘረኛ ሥርዓት በተረኝነት አስቀጥላለሁ ብሎ በውጭ ኃይሎች አይዞህ ባይነትና በሕዝቡ ታጋሽነት ተመክቶ የሚውተረተረው ተረኛው መንግሥታዊ ኃይል ሥልጣኑን በጊዜ ለሕዝብ የሚያስረክብበትን ቀን በፍጥነት አሳውቆ ራሱን ከመንበሩ ገለል ቢያደርግ፣ የሀገሪቱ ታዋቂ ሰዎችና ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶችና ዕውቅ የፖለቲካ ተዋናዮች የሚካተቱበት (እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመራ) ጊዜያዊ ባለአደራ መንግሥት ቢያቋቁም፣ እና ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝብ ፍላጎቱን ሊገልፅበት የሚችል ነፃ ሀገራዊ የፖለቲካ ውይይት የሚደረግበትን ሁኔታ ባለው አቅም ሁሉ ቢያመቻች – ራሱንም ሀገሪቱንም ከተደቀነባት አይቀሬ ቀውስ ለማዳን የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል።
አሊያ ግን በዚህ የአብይና ጭፍሮቹ ውሽልሽል የተረኝነት አገዛዝ፣ ከወያኔ በቀጠለ የዘረኝነት አገዛዝ ተረፈምርት፣ በእነዚያው በበሰበሰው ሥርዓት ጥርሳቸውን ነቅለው ባረጁ የዘረኛው ሥርዓት ባለሟሎች፣ እና ከበፊቱም በባሰ ዓይን ያፈጠጠ ተረኛ አምባገነንነት መንፈስ.. ሀገሪቱ በዚሁ ዓይነት ለጥቂት ጊዜ እንኳ ብትቀጥል መጨረሻችን አስከፊ ሀገራዊ ቀውስ እና አይቀሬ የእርስ በርስ ጦርነት ብቻ ነው የሚሆነው።
ፈጣሪ አምላካችንን ከተደቀኑብን አይቀሬ የጭንቅ ድግሶች በመገላገያው አውጣን ማለት ካለብን ማለቻው ጊዜ በእውነቱ አሁን ነው። ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያችንን ይባርክ። ለኢትዮጵያውያን የሚበጀንን ሰፊ ልቦናና የመፍትሄውን መንገድ ቸር ፈጣሪ ያመላክተን።
እናት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!
_______________________
ድኅረ ማስታወሻ፦
እንዳለመታደል ሆኖ ሰሞኑን ክፉ ክፉው ይታየኛል። ሥጋት ሥጋቱ። ሆሆይ! ብዬ ተገረምኩ። ፈጣሪን ግን አላማረርኩትም። ፈላስፋው ስለ “ፔሲሚስቶች” ያለውን እያሰብኩ፦ ፓራሹትን የፈጠሩት ሰዎች እኮ አውሮፕላኑ በዓየር ላይ ድንገት ብልሽት ገጥሞት ይከሰከስ ይሆን? ብለው የሰጉ ሰዎች ናቸው። ስጋት አስቀድሞ ካልታሰበ፣ መትረፍ የሚባል ነገር ላይኖር ነው። እንኳን ሳይታሰብ፣ አንዳንዴ ቀን ሲጠም ሺህ የስጋት ተንታኞች ባሉበትም ሀገር፣ የታሰቡት ሥጋቶች ይደርሳሉ። ሥጋትም ተባለ ትንቢት፣ ወይም “ዎርስት ኬዝ ሴናሪዮ”፣ ወይም ሌላ… ለማንኛውም ሥጋት የህልውና መሠረት ነው፣ ያለ ሥጋት የሚኖር አህያ ብቻ ነው፣ በሚል መሪ ቃል ተነሳስቼ፣ ሐሴት ሐሴቱን ማውራቱን ለሌሎች ትቼ፣ ሰው ሥጋን ተካፍሎ በሚበላበት የዓውዳመት ሰሞን፣ እነሆ ሥጋቶቼን ላካፍል ተነሳሁ! ወድጄ አይደለም። “ለሀገር!”። “ለሀገር ሲባል – የተካፈለ ሥጋት!” ተብሎ ይወሰድልኝ። መልካም ከሥጋት-ነፃ ጊዜ ተመኘሁ። በሥጋት። ቻው።
Filed in: Amharic