>

"ለትህነግ የበጀት ድጎማ አይደረግም!!!" (ኢፕድ)

“ለትህነግ የበጀት ድጎማ አይደረግም!!!”

ኢፕድ

* << በህገወጥ መንገድ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ም/ቤትና ካቢኔ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው የፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ እንደማይደረግለት የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ገለፀ!!!! >>
* የፌደራል መንግስት ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ ተላለፈ…!!!
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባዔ የፌደራል መንግስት ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
ይህ ውሳኔ ሊተላለፍ የቻለው ባለፈው ነሃሴ 30 2012 ዓ.ም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ጉባዔ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ እንዳልተደረገ፣ እንዳልተፈጸመ እና እንደማይጸና ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው፡፡
ውሳኔውን የሚከታተል የህገ መንግስት ጉዳዮች እና የማንነት ጉዳዮች አጣሪ ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን ሲከታተል ቆይቶ ውሳኔው ባለመፈጸሙ ባዛሬው ዕለት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ነው ይህንን ወሳኔ ሊያሳልፍ ያቻለው፡፡
ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል መንግስት ላይ ሶስት ውሳኔዎችን ማሳለፉን ገልጿል፡፡
የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ያካሄደውን ኢ-ህገ መንስታዊ ምርጫ ተከትሎ ከተመሰረቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈጻሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግስት ምንም አይነት ግንኙነት እንደማያደርግ ወስኗል፡፡
ሁለተኛው የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብን የልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ማዕከል በማድረግ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደርን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ህጋዊ ተቋማት ብቻ የስራ ግንኙነት ያደርጋል፡፡
ሶስተኛ የውሳኔውን አፈጻጸም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴ ክትትል መደረግ አለበት።
የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚው አካል/ካቢኔ/ ህገመንግስታዊ ቅቡልነት ስለሌላቸው ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ምንም ዓይነት ህጋዊ ግንኙነት ማድረግ እንደማይችሉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባሄ አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡
ይህም በመሆኑም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ከፍተኛ አስፈፃሚ አካላት ጋር እንደህጋዊ አካላት በመቁጠር ደብዳቤ መፃፃፍ፣ መረጃ መላላክ፣ የፌዴራል ተቋማት ለክልል ተቋማት የሚሰጧቸውን ድጋፎች መስጠት፣ በፌዴራል ደረጃ የሚካሄዱ መድረኮች ላይ ማሳተፍ የመሳሰሉ ጉዳዮችን ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡
በአንጻሩ የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ የልማትና የአገልግሎት ተጠቃሚነቱ  እንዳይስተጓጎል እንደ ቀበሌ ፣ወረዳ ፣ ከተማ ካሉ ህጋዊ  የክልሉ መዋቅር ጋር ብቻ ግንኙነቱ እንደሚደረግና ይህም በሚዋቀር ኮሚቴ ክትትል እንደሚደረግ አቶ አደም ፋራህ በተለይ ለኢቲቪ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ሊደረስ  የቻለው የትግራይ ክልል መንግስትና ገዥው ፓርቲ ህውሃት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ባከበረ መልኩ የስራ ዘመኑ በምክር ቤቱ ውሳኔ የተራዘመውን የክልሉን ምክር ቤት የህግ አስፈፃሚ አካል ወደ ቦታው መመለስ ስላልቻሉ ነው ብለዋል አፈ  ጉባኤው፡፡
ውሳኔው  የትግራይ ህዝብ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ እየተከተለ ባለ ቡድን ምክንያት ከሰላም፣ልማትና መሰረታዊ አገልግሎት አንፃር እንዳይጎዳና የትግራይ ህዝብ እንደሌሎች የአገራችን ህዝቦች መሰረታዊ የልማትና የደህንነት አገልግሎቶች እንዲያገኙ ታስቦ መተላለፉንም አመልክተዋል፡፡
‹‹ይሄ ሊሆን የቻለው ለትግራይ ህዝብ ካለን ክብር ነው›› ያሉት አፈ-ጉባሄው፤‹‹ ህዝብም እንደ ሌሎች የአገራችን ህዝቦች ሊያገኘው የሚገባውን ጥቅም ሊከበርለት ይገባል ከሚል ጽኑ እምነት የመነጨ ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የውሳኔ አፈፃፀምም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥናት ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል፡፡
በህገወጥ መንገድ የተቋቋመው የትግራይ ምክር ቤትና ካቢኔ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለው የፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ እንደማይደረግለትም  ተመልክቷል፡፡
 በቀጣይ በክልሉ ካሉ የከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት በተለይ ህዝቡ ማግኘት የሚገባውን መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኝ በጥናት ተመስርቶ ተፈፃሚ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
Filed in: Amharic