>

የሀገራችን የድጋፍ ሰልፍ - የዲሞክራሲ ምጸት...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሀገራችን የድጋፍ ሰልፍ – የዲሞክራሲ ምጸት…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ዛሬ በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ዶ/ር አብይ ይምራን፣ መንግስት ይቀጥላል፣ ብልጽግና ያበልጽገን የሚሉ መፈክሮች የተንጸባረቁበት የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል። ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስትን ወይም በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ ደግፎ የሚደረግ ሰልፍ የዲሞክራሲ ወይም በአደባባይ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነት መረጋገጡን ማሳያ ሊሆን አይችልም። የድጋፍ ሰልፎች እንዴት እንደሚዘጋጁ እና እነማን እንደሚሳተፉ ስለምናውቅ።
የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ የሚሆነው በተቃራኒው መንግስትን ወይም በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ በነጻነት እና በአደባባይ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቃወም፣ መንቀፍ እና ቅሬታን መግለጽ ሲቻል ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ አይደለም ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳ መስጠት ከባድ እና የማይቻል ነገር ከሆን ውሎ አድሯል። መንግስትን በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ ተሰብስቦ ለመቃወም መሰናክሉ ብዙ ነው። እዛ ጫፍ ላይ ካልደረስን የድጋፍ ሰልፎች የዲሞክራሲ ምጸቶች ማሳያ ሆነው ይቆያሉ። መንግስትን ወይም ገዢውን ፓርቲ መደገፍ እና ደግፎ ሰልፍ መውጣት መብት የሆነውን ያህል ተቃራኒውም፤ መቃወም እና መንቀፍም መብት ነው። ለመደገፍ ሰዎች ያለፍቃድ አደባባይ ከወጡ ለመቃወምም እንዲሁ መሆን አለበት። በአንካሴም ቢሆን ወደ እውነተኛው የዲሞክራሲ ጎዳና መምጣት ካልቻልን ነገ መደገፍም የማይቻልበት ክፉ ቀን ሊመጣ ይችላል። ለምሳሌ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መቃወም ብቻ ሳይሆን መደገፍም አይቻልም። በሰላማዊ መንገድ መቃወምን የሚያፍን አሰራር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ለማወጅ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን እንደሚጋብዝ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
Filed in: Amharic