ሦስቱ ኢትዮጵያዎች❗️
አሳዬ ደርቤ
.
1. ፌደራሊስቷ ኢትዮጵያ❗️
➖የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ ያላት ሳትሆን የመቶ ዓመት እድሜ ያላት ጨቅላ አገር ነች፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች እንጂ ዜጎች የሏትም፡፡ ቀኗን የምትቆጥረው ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ነው፡፡ ወደ ምኒልክ ዘመን…
የእኔ እንጂ የእኛ የሚባል ነገር በውስጧ የለም፡፡ የሚያለያያት ካልሆነ በቀር አንድ የሚያደርጋት ባሕል፣ ቋንቋ፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ባንድራ የላትም፡፡
➖ተንቀሳቅሶ የመሞት እንጂ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብትን አታከብርም፡፡
መፍትሔ ከመፍጠር ይልቅ ችግር መቀመር መገለጫዋ ነው፡፡ ከዋለልኝ መኮነን ውጭ የክልሎቿ እንጂ ሁሉንም የሚያስማማ የራሷ የሆነ ጀግና የላትም፡፡ አዲስ ታሪክ ከመጠንሰስ ይልቅ የቀድሞ ታሪኳን እያስታወሰች ማለቃቀስ ሙያዋ ነው፡፡ ጥያቄዋም ማለቂያ የለውም፡፡
.
➖ፌደራሊስት ልጆቿ በሥም እንጂ በተግባር አሃዳዊያን ናቸው፡፡ ስለዚህም የእነሱ አይነት ማንነትና ሃይማኖት የሌላቸው ዜጎች ላይ በየጊዜው ጥቃት ማድረስ ሙያቸው ነው፡፡ ለስሙ ‹‹ልዩነታችን ውበታችን›› ይላሉ! በተግባር ግን ልዩነታቸው መገዳደያ ምክንያታቸው ነው፡፡ ቢመቻቸው የሁሉም ምኞት አዲስ አሃዳዊ ሥርዓት መመሥረት ነው፡፡
.
2. አሀዳዊቷ ኢትዮጵያ❗️
➖እድሜዋ ከሦስት ሺህ ዘመንም ያልፋል፡፡ ባሁኑ ሰዓት ከባንድራ ውጭ አሀዳዊ የሚያስብል መገለጫ የላትም፡፡ ከብሔር ብሔረሰቦች ይልቅ ለዜጎች ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡
➖በብሔር ጥቃት ለሚፈናቀሉ ልጆቿ ደራሽ ናት፡፡ ዜጎቿ በዲያስፖራ ትረስት ፈንድና በግሎባል አሊያንስ ላይ በመሳተፍ ይታወቃሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ አይታዩም፡፡
.
➖በዜግነቱ የሚያምን ብቃት ያለው መሪ እስከመጣ ድረስ ማንነቱ ግድ አይሰጣትም፡፡ ያስተሳሰሯትን ምሰሶዎች የማይበጣጥስ ለውጥ ለመቀበል ዝግጁ ናት፡፡ ‹‹አይጥፋብኝ›› እንጂ ‹‹አይስፋፋብኝ›› የምትለው ሃይማኖት፣ ባሕልና ቋንቋ የላትም፡፡
➖በክልሎች ውስጥ ያሉት ቅርሶች ሁሉ የእኔ ናቸው ብላ ታምናለች፡፡ ስለሆነም ጥቅሙን ለክልሎች ትታ ሥሙን በመውሰድ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ፋሲል፣ አልነጃሽ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የሶፍኡመር ዋሻ፣ የያዮና የሸካ ጥብቅ ደኖች ሁሉ… የግሏ በማድረግ ትታወቃለች፡፡ ከዚህ ባለፈም የምታወድሳቸው ብዙ አትሌቶች፣ መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጀግኖች አሏት፡፡
.
3. የብልጽግና ኢትዮጵያ❗️
.
➖ገና በመሠራት ላይ ያለች አዲስ አገር ናት፡፡ ሥሟ ‹‹ሸገር›› ትሰኛለች፡፡ አንድ ክልል እና ቀበና የሚባል አንድ ወንዝ አላት፡፡ በውስጧ በርካታ ሰው ሰራሽ ሐይቆች፣ በልምላሜ የተሞሉ ፓርኮች፣ በጣም የሚያማምሩ ቀበሮዎች፣ ይገኛሉ፡፡
➖ነዋሪዎቿ እጅግ ደስተኞችና ሃብታሞች ሲሆኑ ከካድሬነት ባለፈ በዜግነት የሚያምኑ ይሁኑ በማንነት ግልጽ አይደለም፡፡
.
➖እኒህም ካድሬ ልጆቿ አብዛኛውን ጊዜ ኮንዶሚንየም በመሸላለም፣ መሬት በመከፋፈል፣ እጅግ ውድ የእራት ድግሶችን በማሰናዳት፣ ቅንጡ መኪኖችን በመንዳት፣ እንደ ዳርትና ቀስት ያሉ ጨዋታዎችን በመጫወት፣ የውሃ ትርኢቶችን በመመልከት ይታወቃሉ፡፡ ከእራት ግብዣም ሆነ ከፕሮጀክት የሚያገኙትን ገንዘብ በቅንጦት ተግባራት ላይ ሲያውሉ ይታያሉ፡፡
አገሪቷ በጣም ሰላማዊ በመሆኗ ወታደሮቿ ከጦርነትና ከግጭት ይልቅ ትርኢት ላይ የሚሳተፉ ናቸው፡፡
➖ነዋሪዎቿ ስለ ችግርና አደጋ ምንነት የማያዉቁ በመሆናቸው ‹‹ጎርፍ›› ሲባል ትዝ የሚላቸው ‹‹ጎልፍ›› ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በግብርና የሚተዳደር ምንም አይነት ሰው ባለመኖሩ በgrasshopper የሚወድም ሣር እንጂ በአንበጣ (Locust) የሚጠፋ ሰብል የላቸውም፡፡
.
(ከመጽሐፉ ያልተቀነጨበ)