አድማጭ የሌለው ጩኸት!!
ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ማንዱራ ወረዳ ላይ ጥቅምት 02፣2013 ከሌሊቱ በሰባት ስዓት ላይ 21 ሰዎች ድምፅ በሌለው መሳሪያ (በቢላ እና በቀስት) ተገድለዋል፡፡ የስድስት ወር ልጅም እንደታረደ ተሰምቷል፡፡ እነ ማን ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ምክንያቱም ስርዓቱ የአማራን ቁጥር መቀነስ እና የኦሮሞን ቁጥር ለመጨመር ስልታዊ አካሄድ እንደሚሄድ ተነግሮናል፡፡ ለአስረጅነት የሚከተለውን ማየት በቂ ነው፡፡
‘’ቤንሻንጉል ጉምዝ 37 ፐርሰንት አፋን ኦሮሞ የሚናገሩባት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ ሶማሌ ወስጥ አማርኛ እየሞተ በመምጣት ወደታች እየሄደ ነው’’ (ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ከተናገረው የተወሰደ)፡፡
አማራው በእንዲህ አይነት ጥቃት ቁጥሩ እንዲቀንስ እና አካባቢውን እየለቀቀ እንዲሄድ ነው የተፈለገው፡፡ ገበሬው አዝመራውን እየተወ አካባቢውን እየለቀቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ የሚነገራቸውም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ነው፡፡ እንባን የሚያብስ መሪ የሌለው ህዝብ በየጊዜው ይሰደዳል፤ ይገደላል፣ይሸማቀቃል፡፡
ከትናንት ዛሬ ይሻላል ብለን ስርዓቱን ተስፋ ብናደርግም የአሁኑ ስርዓት ከበፊቱ ስርዓት አማራን በማጥቃት የባህሪ ትስስር አለው እንጅ ለአማራው የፈየደው ትርጉም የለም፡፡ የእነዚህን ምስኪን ዜጎች ጩኸት አለመስማት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጌታም ይፈርዳል፡፡ ‘’ የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፣ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትም’’ ምሳሌ 21፣13፡፡