>

"የመተከል በእሳት ቀለበት መግባትና የደመቀ መኮንን እጅግ የዘገዬ አማራጭ!!!" (ጓንጓ ወረዳ ኮሙኒኬሽን)

“የመተከል በእሳት ቀለበት መግባትና የደመቀ መኮንን እጅግ የዘገዬ አማራጭ!!!”

ጓንጓ ወረዳ ኮሙኒኬሽን

*…እጅግ ያሳዝናል፤ ይሰቀጥጣል !!!  የ6 ወር ህፃንን ጨምሮ የ 12 ንፁሃን በግፍ ታርደው አስክሬናቸው ወደ ወረዳችን የመጣ ሲሆን ከነዚህም 7 ቢዝራካኒ ቀበሌ አንድ ቤተሰብ 5 አበባ ቀበሌ ናቸው። 
 
የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጉህዴን)፣ ኦነግ/ሸኔ፣ ህወኃት፣ የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ(ቦዴፓ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብልፅግና ፓርቲ መዋቅራዊ ሰንሰለት የሚሰራጭ የመረጃ አስተኳሽነት መተከል ደኖች ዉስጥ በህወኃት ጀኔራሎች ላለፉት ሁለት አመታት ሲካሄድ የከረመዉ ወታደራዊ ስልጠና፣ ፖለቲካዊ ጠመቃና የሎጅስቲክስ ድጋፍ የተደራጀዉ ጨፍጫፊ ቡድን የመተከልን አኬልዳማነት ቀላል አድርጎታል። መተከል የሞት ማምረቻ ቀጠና ከሆነ ሰነባበተ።
የፍጅት ስኳዱ ከአሶሳ ተነስቶ በደቡብ ሱዳን አድርጎ እስከ ካይሮ በተዘረጋ ጠንካራ የጥፋት ሰንሰለት የተጠላለፈ ነዉ። አሁን ቀጠናዉ ከፊል የትጥቅ ትግል ማስተናገድ ጀምሯል። አጥቅቶ መሸሽ የወቅቱ የትግል ስልት ነዉ። ገድሎ ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት ማዕከላዊ መንግስቱን መፈታተኛ መንገድ ሆኗል። መንግስት እጅግ ከመዘግየቱ ባሻገር በዉስጡ የተሸሸገዉ የጥፋት ሀይል ከዉጭ ካለዉ አደረጃጀት ጋር እየተመጋገበ የቀዉሱን ደረጃ በቀላሉ እንዳይቀለበስ አድርጎታል።
በዚህ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ያመጡት ነዋሪዉን የማስታጠቅ አማራጭ እጅግ የዘገየ አማራጭ ነዉ። አካባቢዉ ላይ የወታደር ማሰልጠኛ ካምፖች ተደራጅተዉ ቤተሰብን በሁለትና በሶስትሺ ብር እያታለሉ በፖለቲካ ያልነቁ የጉምዝ ወጣቶችን የሚያስቆጣ ጠመቃ ሲካሄድ ሰንብቷል። በተደራጀ መንገድ የሰለጠነዉ ታጣቂ በፓትሮል ተጭኖ ብሬል የያዘን መከላከያ ሰራዊት አነጣጥሮ ግንባሩን የሚበትን ብቁ ሆኖ እንዲወጣ ተደርጓል። በከባድ መሳሪያ የተደራጀንና ላለፉት ሁለት አመታት በወታደራዊ ሳይንስ ተግቶ የሰለጠነን ታጣቂ ሀይል ህዝብን በማስታጠቅ አትመልሰዉም። የቀዉሱ ደረጃ ከፍ በማለቱ መፍትሄዉም ማደግ አለበት።
መተከል የአባይ ግድብ መገኛ ከመሆኑ ባሻገር የተለጠጠዉ መልከአምድራዊ አቀማመጡ በመደበኛ የፀጥታ ሀይልና ተበታትኖ የሚኖርን ህዝብ በማስታጠቅ ብቻ ቀዉሱን መቀልበስ አይቻልም። ከዚህ በኋላ ህዝብ ታጠቀም አልታጠቀም አካባቢዉን መቆጣጠር የሚችል ወታደራዊ ሀይል በበቂ መጠን ከሌለ የተደራጀዉ ሀይል የመተከልን ዙሪያ ገባ እየተንቀሳቀሰ የሚያደርሰዉን ጥቃት አድማሱን አስፍቶ መተከልን ዘሎ የአማራ ክልልን ወሰኖች ማጥቃት ይጀምራል።
ከዚህ በኋላ ህወኃትና ግብረአበሮቹ የትጥቅ ትግል ከጀመሩ ያለጥርጥር መጀመሪያ የሚቆጣጠሩት ቀጠና መተከል ነዉ። በአካባቢዉ የሚካሄደዉን እንቅስቃሴ ላለፉት ሁለት አመታት እየተመለከተ አይኔን ግንባር ያድርገዉ በማለት የመተከልን ጉዳይ የረሳዉ የአብይ መንግስት አሁን አካባቢዉ የእግር እሳት ሆኖበታል። ለጊዜዉ የጥቃት ሰለባ የሆነዉ ሰላማዊ ነዋሪዉ መሆኑ ግድ ላይሰጠዉ ይችላል። ጊዜ በሄደ ቁጥር ግን አካባቢዉ ከማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥር ዉጭ የመሆን እድሉ የሰፋ ነዉ። ግድያዉ የሚፈፀመዉ ተበታትኖ በሚኖረዉ ጉምዝ ሳይሆን በተደራጀዉ ተንቀሳቃሽ አማፂ ነዉ። ግድያዉን ፈፅሞ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጨዉ ምስል ለገዳዩ ስኳድ የራሱ ፖለቲካዊ አንድምታ አለዉ። አንድም በአካባቢዉ ያለዉን ሰላማዊ ነዋሪ ማስበርገግ ሁለትም ብልፅግናን አጣብቂኝ ዉስጥ መክተት ሶስትም ለግብፅ መናጆነቱን ማረጋገጥ የታጣቂዉ ቡድን አላማ ነዉ።
እጅግ ያሳዝናል፤ ይሰቀጥጣል !!!  የ6 ወር ህፃንን ጨምሮ የ 12 ንፁሃን በግፍ ታርደው አስክሬናቸው ወደ ወረዳችን የመጣ ሲሆን ከነዚህም 7 ቢዝራካኒ ቀበሌ አንድ ቤተሰብ 5 አበባ ቀበሌ ናቸው። ጓንጓ ወረዳ ኮሙኒኬሽን
በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል በንጹሃን ላይ የሚደርሰው ግድያ ቀጥሏል። መተከል ላይ ለሊቱን ከ 21 በላይ ንፁሀን ዜጎች በግፍ ተገለው ማደራቸው ተሰምቷል።የቤንሻንጉል ባለስልጣናት በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ድኋንዝ ባጉና ቀበሌ ትናንት ከሌሊቱ ፰ ሰዓት አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉን አምነዋል።
ሊቆም ያልቻለውና በተደጋጋሚ የምንሰማው ነገር ቢኖር ንፁሐን ዜጎች፣ በሕይወት የመኖር መብታቸው ተነፍጎ፣ የብሔር ሐረገቸው እየተመዘዘ እንደ እንስሳ በቀስት እየታደኑ ተገደሉ፣  በሰው ልጅ ሊፈፀም የማይገባው ጥቃት ተፈጸመባቸው። የሚለው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ የሚፈጸም ወንጀል ነው። እጅግ ያሳዝናል፤ ይሰቀጥጣል።
ለአከባቢው ሰላምና ለዜጎች ደሕንነትም ፖለቲካዊ መፍትሔና ውሳኔ ግድ ይላል።ባለስልጣናት የተለያዩ መግለጫዎችን ቢሰጡም ሰላምንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው ቢሉንም ከፕሮፓጋንዳ ባለፈ ጥቃትን ለማስቆምና ውድመትን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረትና መፍትሔ ግን እስካሁን አለመታየቱ አነጋጋሪ ነው።
Filed in: Amharic