>

መንግስት የአማራን ችግሮች ለመፍታት ፍላጎትና ዝግጁነት እንደሌለው ተረድተን ተስፋ መቁረጥ አለብን...!!! (ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ)

መንግስት የአማራን ችግሮች ለመፍታት ፍላጎትና ዝግጁነት እንደሌለው ተረድተን ተስፋ መቁረጥ አለብን…!!!

ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

*… መጠበቅ፣ መለመንና ማማረር ቀንሰን በየአካባቢያችን ለሚገጥሙን ችግሮች በራሱ በማህበረሰቡ መፍትሄ እየፈለግን፣ ስለአማራ ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ በአግባቡ ማሰብና መወያየት መጀመር ያለብን ጊዜ አሁን ነው!
 
የአማራ ህዝብ ትልቁ ውስጣዊ ድክመት ለመንግስታዊ ተቋማት ያለው አመኔታና መንግስት መፍትሄ ይሰጠኛል የሚል ቀቢፀ ተስፋው ነው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ህዝባችን ማንቃት አለብን። ማሳያዎችን እየጠቀስን ማስረዳትና ማስተማር አለብን። መንግስት ተብየው ስብስብ ለህዝባችን መፍትሄ እንደማያመጣለትና መጠበቅም እንደሌለበት ከተገነዘበ ህዝቡ ለራሱ ጉዳዮች የራሱን መፍትሄ ከመፈለግ አያንስም።
ለህዝባችን አንድም አለሁልህ የሚለው አካል ስለሌለ ማማረሩንና ማለቃቀሱን ትንሽ ቀነስ አድርገን በየአካባቢያችን እየተደራጀን ችግሮችን ወደመጋፈጥ መግባት አለብን።
እያንዳንዱ አማራ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ችግሮች በራሱ መፍትሄ የማስቀመጥ፣ የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ፣ አካባቢውን የመጠበቅ ስራ መስራት አለበት።
የአማራ ህዝብ ባለፉት አመታት የገጠሙትን ዋና ዋና ችግሮች መንግስት ተብየው አካል ከቁብ አይቆጥራቸውም። ይልቁንም ለማደንቆርና አማራው ምን ያመጣል በሚል አይነት መንፈስ መንግስታዊ ስላቅ ይሰጠዋል።
ለምሳሌ፦ መንግስት ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች የተሰጠውን መልስና መፍትሄ እስኪ እናስብ
1) ለጣና እንቦጭ ወረራ መንግስት የሰራው ስራና የሰጠው መልስ
2) ለላሊበላ እንዲሁም ለአፄ ፋሲል አብያተ መንግስታት የቅርሶች ጉዳት መንግስት የሰራው ስራና የሰጠው መልስ
3) ከየዩኒቨርሲቲዎች በአስር ሺህዎች የሚደርሱ የአማራ ተማሪዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት ትምህርታቸውን  እንዲያቋርጡ፣ አንዳንዶችም ያለአግባብ ከትምህርት ገበታቸው እንዲባረሩ
4) በኦሮሞ ክልል የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ 17 የአማራ ተማሪዎች መታገት የሰጠው መልስ
5) አማራው በኦሮሞ ክልልና በመተከል በማንነቱ ምክንያት የደረሰበት ተከታታይና ማባሪያ የሌለው ጥቃት፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ የሀብትና የንብረት ውድመት እንዲቆም ለጠየቀው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ
6) በደምቢያና ፎገራ በጎርፍ ለተጥለቀለቁና ለተጎዱ ወገኖች የተሰጠው ምላሽ
7) በወሎና በሸዋ ለተከሰተው አውዳሚ የአንበጣ መንጋ ወረራ የተሰጠው ምላሽ
8) ፍትኃዊ የሆነ የመሰረተ ልማት ተጠቃሚነት (መብራት፣ መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወዘተ…) ተጠቃሚ እንዲሆን ለሚያነሳው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ
9) ፍትህና ርትዕ እንዲሰፍንለት፣ በአማራነቱ ብቻ የፍትህ ማጣት፣ ያለአግባብ በጅምላ ያለመታሰር ለጠየቀው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ
10) ፍትሀዊ የበጀት ድልድልና ድጎማ፣ ፍትሃዊ የንግድ ዕድልና የታክስ ጫና ላይ ያለውን ነገር ሁሉ እንይ።
ምንግስት ለነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ለአማራ የሰጠው ምላሽ አለ? በፕሮፓጋንዳና በማስቀየሻ የተሞላ ማምታታት ካልሆነ ምንም የተሰጠው የተግባር ምላሽ የለም።
ስለዚህ መጠበቅ፣ መለመንና ማማረር ቀንሰን በየአካባቢያችን ለሚገጥሙን ችግሮች በራሱ በማህበረሰቡ መፍትሄ እየፈለግን፣ ስለአማራ ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ በአግባቡ ማሰብና መወያየት መጀመር ያለብን ጊዜ አሁን ነው!
Filed in: Amharic