የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
ከኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ:-
በኢትዮጵያ ህዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ህዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል፡፡
ከእንግዲህ በአገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ለህዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግስት መሆን ጀምሯል፡፡
በዚህም ምክንያት የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የአገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በአገራችን ተከስቷል፡፡ በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና አገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ስርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፣ ኢዴፓ አገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል፡፡
ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያዬነው አይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም፡፡
በኢዴፓ ዕምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤
1. በአገራችን የህግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው፡፡ በኢዴፓ ዓመራር በአቶ ልደቱ አያሌውና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ አገር ላይ የህግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀምና፤ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡
2. በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች / በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በአገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል፡፡ ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው፡፡
3. አገራችን በዚህ አይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው አገራዊ ምርጫ ድረስ አገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የአገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? አገሪቱ ቋሚ መንግስት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያለየለትን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት / National Dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት፡፡
4. በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ጉዳዩ ከአገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት፡፡
በአጠቃላይ እነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በአገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በአገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የአገሪቱ ባለቤት ህዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው አገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ህጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ