>

የመንግሥታዊ ጥቃት መገለጫ - ዝቋላ...!!! አትገቡም....!!! (አባይነህ ካሳ)

የመንግሥታዊ ጥቃት መገለጫ – ዝቋላ…!!! አትገቡም….!!!
አባይነህ ካሳ


 

“ወደ ዝቋላ ገዳም ተጉዋዦችን ያስቀረነዉ ከገዳሙ በተፃፈልን ደብዳቤ መሠረት ነው”
የልዩ ሀይል ፖሊስ
 
 “ምንም የፃፍነው ደብዳቤ የለም በፖሊስ ድርጊት አፍረናል ተከፍተናልም”
  የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ገብረህይወት
ለሕዝቡ ግድ ከማይሰጠው መንግሥት የሚጠበቀው ሁሉ እየደረሰብን ይገኛል፡፡ ኦርቶዶክስ ስትኾን ወደ ገዳምህ ለመሔድ ትከለከላለህ፡፡ በሺህ ኪሎ ሜትሮች ሳይቀር አቆራርጦ የመጣ ምእመንን ድንገት ወታደር እና ፖሊስን አስተባብሮ ተመለስ ማለት ምን ማለት ነው?
የኮሮና ቫይረስ አጀንዳ የሚገንነው ኦርቶዶክሰውያን ሲሰበሰቡ የኾነበት ልዩ ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ኢሬቻ ለማክበር ኮሮና የለም፡፡ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ድጋፍ ሰልፍ ለመውጣት አዲስ አበባ ይሁን ኦሮሚያ ወይም ሐረር ኮሮና ከምድረ ገጽ ይጠፋል፡፡ በደብረ ዘይት የኾነውን ዐይተናል፡፡ ደመራ ለማክበር ግን ውሥን ቁጥርም አይፈቀድም፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሲሰባሰብ ግን ጋኔኑ ይጮኻል፡፡ የሚሰማውም የእርሱ ድምፅ ኾኗል፡፡
ጥቅምት ፭ ዓመታዊ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ክብረ በዓል መኾኑ ይታወቃል፡፡ በየዓመቱ በደብረ ዝቋላ (ዝ ቆላ) ክብረ በዓሉ በልዩ ድባብ ይከበራል፡፡ ጻድቁ ለ፳፻፷ (260) ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈጸሙት ገድል ብዙውን የተጋደሉበት ቦታ ነው፡፡ ምእመናን ከዐራቱም ማዕዝን በዓሉን ለማክበር ይጓዛሉ፡፡ ዛሬ በዋዜማው ቆራጭ ፈላጩ ኦርቶዶክስ ጠሉ የኦሮሚያ አስተዳደር ድንገት ብድግ ብሎ ተጓዦቹን አግቷል፡፡
ጻድቁ ከትውልድ ሀገራቸው ይልቅ ተሽላቸው በፍስሐ በብሩኅ ገጽ የተቀበለቻቸው ስንት ተጋድሎ የፈጸሙባት ሀገር እንዲህ ኾና ሲያዩአት ምን ይሉ? ከልዕልና ማማዋ ወርዳ እስከዚህ ድረስ ሲያዘቅጧት ምን ይሉ አባታችን? ያኔ የተቀበለቻቸው ኢትዮጵያ ዛሬ የገዛ ልጆቿን አልቀበልም የሚሉ ሰርዶዎች በቅለውባት ሲያዩ ምን ይሉ?
በዓሉን በውሡን ሰው የማክበር ፍላጎት ቢኖረው እንኳ ከሀገረ ስብከቱ ጋር ተመካክሮ ቁጥር በመወሠን ደግሞም ቀድሞ በማሳወቅ ሊፈጽመው ይገባ ነበር፡፡ በግዴለሽነት ገንዘብ ቋጥሮ ዓመት ሙሉ ተዘጋጅቶ ስንቅ ሰንቆ የመጣን ተሳላሚ ተመለስ ማለት አንጀት ይቆርጣል፡፡ እናም ከደብረ ዘይት ጀምሮ ያለውን የ፲፭ ኪሎ ሜትር ርቀት በእግር ጉዞ የተጓዙ እናዳሉ ሁሉ የተመለሱት ይበዛሉ፡፡ በረከታቸውን እንደኾን ተቀብላችኋል፡፡ በልብ እንጅ በእግር መሔድ አይደለም ቁም ነገሩ፡፡
ትናንት ወደ ዝቋላ ገዳም ለንግስ ሲጓዙ የነበሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ከቢሾፍቱ እንዳለፉ በፖሊስ መሄድ አትችሉም ተብለው መከልከላቸውን ታውቋል። በርካታ መኪኖችም መንገድ ላይ ለማደር ተገደዋል።
ዛሬ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ “ወደ ዝቋላ ገዳም ተጉዋዦችን ያስቀረነዉ ከገዳሙ በተፃፈልን ደብዳቤ መሠረት ነው” ሲሉ የገዳሙ አስተዳዳሪ አባ ገብረህይወት ደግሞ “ምንም የፃፍነው ደብዳቤ የለም በፖሊስ ድርጊት አፍረናል ተከፍተናልም” ሲሉ ተናግረዋል።
ሰሚ ያጣች ቤተ ክርስቲያን እያደረጓት ስለኾነ አዎ ራስን የመከላከል አስፈላጊነት ከዐይናችን ሥር ነው፡፡
የላሃ የሃይማኖት እስረኞችን እርዳታ አትርሱ!
Filed in: Amharic