>

ዛሬ አቶ ልደቱ VS  የፍርድ ቤት ዳኞች ! (በተስፋለም ወልደየስ)

ዛሬ አቶ ልደቱ VS  የፍርድ ቤት ዳኞች !

በተስፋለም ወልደየስ


ማስረጃውን ይዞ እንዲቀርብ የታዘዘው ፖሊስ  በማን አለብኝነት በችሎቱ ሳይገኝ ቀረ። ታዋቂው ፖለቲከኛ ለችሎቱ የሚፈፀመውን አድልኦ እና ግፍ የፍትህ ሥርዓቱን አደጋ ላይ መውደቅ በቅሬታ መልክ አቀረቡ።

የአቶ ልደቱ አቤቱታ በችሎት

“እኔም ፖሊስም በህጉ ላይ እኩል መብት ነው ያለን። ፖሊስን ይህን ያህል በታገሳችሁት ልክ፤ እኔን አንድ ተራ ዜጋውን ይህን ያህል ትታገሱኛላችሁ ወይ? በዚህ አይነት እንዴት አድርጌ ነው ከፍትህ ስርዓቱ ውጤት አገኛለሁ የምለው?”

 

ህግ ማስከበር የተሳናቸው ዳኞች የሰጡት ምላሽ 

“እኛ እንግዲህ ጦር አናዘምትም። ያለን አቅም ህጉን መተርጎም ነው። ፖሊሶቹ ራሳቸው ናቸው ሊያፍሩ የሚገባው፣ ተቋሙ ራሱ ነው ሊያፍር የሚገባው። ህገ መንግስቱን ነው እየጣሱ ያሉት”

ወይ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ  እንዲህ ማፈሪያ የሆነ ከህወሓት ዘመን የባሰ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት አድርገውት ቁጭ ይበሉ ?

ዝርዝር ዘገባውን ያንብቡ :-

የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ አቶ ልደቱ አያሌው በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ እንዲያደርግ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ በዛሬው የችሎት ውሎው የኦሮሚያ ክልል ዐቃቤ ህግ በአቶ ልደቱ ላይ የቆጠራቸውን ሶስት ምስክሮች ቃልም አድምጧል።

አቶ ልደቱ የተከሰሱበትን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ የመገኘት ወንጀል የሚመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 5፤ 2013 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ሁለት ጉዳዮችን ለመመልከት ነበር። የመጀመሪያው ባለፈው የችሎት ቀጠሮ ሳይቀርቡ የቀሩትን የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ አቶ ልደቱ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ፣ የታሰሩበት የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ ለምን ሊያስፈጽም እንዳልቻል እንዲያስረዳ ነበር። በዚህም መሰረት የዐቃቤ ህግ ሶስት ምስክሮች በችሎት ቀርበው ቃላቸውን መስጠታቸውን፤ የዛሬውን የችሎት ውሎ በአዳማ ከተማ በሚገኘው ፍርድ ቤት በመገኘት የተከታተሉት፤ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ተናግረዋል።

ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በነበረው የችሎት ውሎ፤ የአሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ይዟቸው እንዲቀርብ ትዕዛዝ የተሰጠባቸው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ፤ ዛሬ ባለመቅረባቸው ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ሌላ ትዕዛዝ መስጠቱን አቶ አዳነ አመልክተዋል። የፖሊስ መምሪያ ኃላፊው በችሎት ያልተገኙት ከኃላፊነታቸው በመነሳታቸው እንደሆነ አቶ ልደቱን አጅበው የመጡ ፖሊስ ለችሎቱ መግለጻቸውንም አክለዋል።

ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ተቀብሎ በችሎት አለመገኘቱን በተመለከተ፤ አቶ ልደቱ ለፍርድ ቤቱ ቅሬታቸውን በግልጽ ማቅረባቸውን የፓርቲያቸው ፕሬዝዳንት አስረድተዋል። “እኔም ፖሊስም በህጉ ላይ እኩል መብት ነው ያለን። ፖሊስን ይህን ያህል በታገሳችሁት ልክ፤ እኔን አንድ ተራ ዜጋውን ይህን ያህል ትታገሱኛላችሁ ወይ? በዚህ አይነት እንዴት አድርጌ ነው ከፍትህ ስርዓቱ ውጤት አገኛለሁ የምለው?” ሲሉ ችሎቱን መጠየቃቸውን አቶ አዳነ ተናግረዋል።

የዕውቁን ፖለቲከኛ ቅሬታ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ “እኛ እንግዲህ ጦር አናዘምትም። ያለን አቅም ህጉን መተርጎም ነው። ፖሊሶቹ ራሳቸው ናቸው ሊያፍሩ የሚገባው፣ ተቋሙ ራሱ ነው ሊያፍር የሚገባው። ህገ መንግስቱን ነው እየጣሱ ያሉት” ሲል ምላሽ መስጠቱን የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ጠቅሰዋል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ለአፍታ ጊዜ በመውሰድ በሚሰጠው ትዕዛዝ ላይ መምከሩንም ጠቁመዋል።

በስተመጨረሻም ችሎቱ፤ አቶ ልደቱ በፍርድ ቤት ከዚህ በፊት የተፈቀደላቸው የ100 ሺህ ብር ዋስትናን ተጠብቆ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ እና ይህንንም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ራሱ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ መስጠቱን አቶ አዳነ ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ለኮሚሽኑ ይህንን ትዕዛዝ ያስተላለፈው ተከሳሹ ታስረው የሚገኙበት የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ እንዲፈቷቸው እንዲያስደርግ ከዚህ ቀደም የሰጠውን ትዕዛዝ ማስፈጸም ባለመቻሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው የችሎት ውሎው ለቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያም ትዕዛዝ መስጠቱን አቶ አዳነ ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ የቢሾፍቱ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እና የወንጀል መከላከል መምሪያ ኃላፊ በችሎት ፊት ቀርበው፤ አቶ ልደቱን ለምን እንዳለቀቁ እንዲያስረዱ ማዘዙን ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ይህን ትዕዛዙን አቶ ልደቱን አጅቦ በመጣ ፖሊስ አማካኝነት እንዲደርሳቸው እና መልስ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ማስተላለፉንም አብራርተዋል።

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ኃላፊዎች ምላሽ ለማድመጥ እና የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመጪው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 9፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)     

Filed in: Amharic