>
5:28 pm - Friday October 10, 1721

የኢትዮጵያ ባንዲራ ከየት መጣ?  (ጸጋው ማሞ)

የኢትዮጵያ ባንዲራ ከየት መጣ? 

ጸጋው ማሞ

 

  *  ባንዲራችን ለኩሽም ፣ ለሴምም ፣ለያፌትም የተሰጠ ነው !
           በመጽሐፍ ቅዱስ በኦሪት ዘፍ. ምዕራፍ 9፡12-17 ላይ እንደወረደ እንዲህ ይላል
 ” በእኔና በእናንተ መካከል…ለዘላለም ትውልድ የማደርገው  የቃል ኪዳኔ ምልክት ይህ ነው፣ ቀስቴን በደመና ላይ አኖራለሁ፣ የቃል ኪዳኔ ምልክት  በእኔና በምድር መካከል ይሆናል ፣በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁ ጊዜ ቀስቴ በደመና ትታያለች ፣በእኔና በእናንተ መካከል  ያለውን ቃል ኪዳኔን አስባለሁ— ቀስቴም በደመና ትሆናለች… ሥጋ ባለው ሁሉ  መካከል ያጸናሁት የቃል ኪዳን ምልክት ይህ ነው “
በማለት ለኖህና ለልጅ ልጆቹ   ምንም እንኳን ኃጢአት ቢሰሩ  ዳግመኛ በንፍር ውሃ  እንደማያጠፋቸው  የዘላለም  ኪዳን በቀስተ ዳመናው አማካኝነት እንደሰጣቸው በማያሻማ  መልኩ በማይታበል ቃሉ  ተናግሯል ።ዳሩ ግን የሰው ልጆች ሁሉ  ኪዳኑን ከነመኖሩም ቢረሱትም፤  ሃገራችን ኢትዮጵያ ግን  በሦሥቱም ኪዳናት ጸንታ የኖረች የዓለም ብቸኛዋ ሃገር በመሆኗ  የኪዳኑን ምልክት(ባንዲራውን) የማንነቷ መታወቂያ አድርጋ ሺ ዘመናትን እየተሻገረች የፈጣሪን የኪዳኑን  ምልክት  ዛሬም ድረስ በፈተና መካከል ይዛ ቆማለች ።

ባንዲራችን

 “”ሰንደቅ ዓላማችን የአምላክ ስራ በቅድስቲቷ ልጆች በኢትዮጵያ ዘንድ መታወቂያ የእግዚአብሔር ዙፋን ነው “”    “የኩሽ ሀያሉ ስርወ መንግስት ጀግኖች” ገጽ 66
——
   ኢትዮጵያን ልዩ  የሚያደርጋት  እንደ ምዕራባውያን ክርስትናን ከጣኦት አምልኪነት በቀጥታ አለመቀበሏ ነው ። ከአዳም የሚመዘዘውን ህገ ልቦናን ፣ ህገ ኦሪትን አልፋ ነው አዲሱን ኪዳን የተቀበለችው። የባንዲራችን አመጣጥ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጻፋ በፊት ጀምሮ የነበረ  የህገ ልቦና  የአምልኮ አንዱ ክፍል ነው።
——
   አለቃ አያሌው ታምሩ  “የኢትዮጵያ እምነት  በሦሥቱ ህግጋት ” ገጽ 48 ላይ ” ኖህና  ልጆቹ  መጀመሪያ ከውሃ ጥፋት ፣ሁለተኛ ለአጋንንት ከመገዛት ያዳነ ልዑል እግዚአብሔርን ብቻ  ስታመልክ ፣ለኖህም የሰጠውን ቃል ኪዳን በማስታወስ  አረንጓዴ ፣ቢጫ ፣ቀይ  መልክ ያለው  ሰንደቅ አላማ በፊቱ አድርጋ በህገ ልቦና ብቻ ስትገዛ ኖራለች”  በማለት በህገ ልቦና በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ካሉት ኪዳናት አንዱ ባንዲራው እንደሆነና  ለፈጣሪ የመገዛት  ምልክትም እንደሆነ ይናገራሉ ። ባንዲራው  የአዲሱ ኪዳን ውርሳችን ሳይሆን ከኖህ ያመጣነው  ይበልጡንም ኩሻዊ ማንነታችን ነው ።
 ——-
    ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ “ኢትዮጵያ የአለሙ መፋረጃ” በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ 64 ላይ ስለ ባንዲራችን ጨመቅ አድርገው እንዲህ ይላሉ” ቀስተ ደመናው የደህንነት መተማመኛችን ዘላለማዊ ዋስትናችንና አማናዊ ምስክራችን ነው ” በማለት ኢትዮጵያ ከአምላኳ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ኪዳን ይመሠክራሉ ።
—–
  መሪ ራስ አማን በላይ  ደግሞ “በመጽሐፈ ብሩክ ዣን ሸዋ ቀዳማዊ ገጽ 259 ላይ ስለ ባንዲራችን እንዲህ በማለት ይገልጻሉ” በሰማይና በምድር መካከል በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል እግዚአብሔር ያደረገውን ቃል ኪዳን ያስታውሱት ዘንድ የእግዚአብሔር መላእክ ሱርያኤል  በደመናውና በፀሐዩ መካከል ይታይ ዘንድ የቃል ኪዳኑ መታሰቢያ ምልክት የሆነውን በእንቁዮጵ ላይ ጽፎ ከህይወት ምንጭ ውሀ ራስ አጠገብ አትሞ አስቀምጦታል ” በማለት  ለሰው ልጆች በሚታይ መልኩ እንደተሰጠ ይናገራሉ ። ይሁንና ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክቡር ኪዳን ስለያዝን አይኑ የሚቀላ ማነው?   ሌላ ሌላውን ትተን   ኢትዮጵያኖች ከየት  አመጡት?  እንዴት  የቀስተ ዳመናውን ምልክት ሊጠቀሙ ቻሉ ?ብለን መጠየቅ እንዴት  ተሳነን?   ይህ ባንዲራ  የኩሽ ፣የሴምና የያፌታውያን የጋራ ምልክታቸው ስለሆነ ዓለም ሁሉ ሊጠቀምበት ይገባል።
Filed in: Amharic