ከቡስካ በስተጀርባ – በኢቫንጋዲው ዳንኪራ…!!!
እየብ ጥላሁን
ሁለት የተለያዩ እግሮች ፣ ሁለት የተለያዩ ልቦች ፣ ሁለት የተለያዩ ሃሳቦች በአንድ ምናብ የተጓዙ ይመስል ከአድማስ ወዲያ ማዶ ከቡስካ ተራራ በስተጀርባ ሳይቀጣጠሩ ተገናኝተዋል፡፡ ቡስካ ምን ጉዳይ ቢኖረው ይሆን ጎሳዬ ተስፋዬን እና ፍቅረማርቆስ ደስታን ጠርቶ ሚስጥሩን ሊያካፍላቸው የወደደው፡፡ ቡስካ ከቀኝ ብብቱ ስር አንድ የዛፍ ፀጉር ነቅሎ ብእር ቀርፆ ቀለም ጨምቆ የሰጣቸው ይመስል ሁለቱም የቡስካ ሚስጥረኞች አንድ ነገር ፃፉ ‹‹ከቡስካ በስተጀርባ›› የሚል ያላለቀ ሀረግ ፤ ግን ደግሞ ያለቀ ዓረፍተ ነገር፡፡ ፍቅረ ማርቆስ ከጎሳዬ ቀድሞ የቡስካን ተራራ ሚስጥር ይዞ ወደ ህዝቡ ቢገባም እንደጎሳዬ ሙዚቃ ግን የተደራሲያንን ልብ አላገኘም ነበር፡፡ ጎሳዬ ከቡስካ ተራራ በስተጀርባ ያለውን ሚስጥር እንዲህ ሲል ይጀምራል፡፡
…………………..
ካድማስ ወዲያ ማዶ ቡስካ በስተጀርባ
እግር ጥሎኝ ባያት ፍቅሯ ልቤ ገባ
በራቁት ደረቷ ተወድሮ ጡቷ
እጅ ወደላይ ብሎ ማረከኝ ውበቷ
……………………..
ይላል ፤ ፍቅረ ማርቆስም ልክ እንደጎሳዬ ያየውን የተማረከበትን ተፈጥሮአዊ የማህበረሰብ አኗኗር ከህሊና ሰሌዳው ላይ እየቀዳ ወደ ተቀረው አለምም እንዲህም አለ ለካ በሚያስብል የድርሰት ስነ-ውበት አፃፃፍና አደራረስ ደርሶ አቅርቦልናል፡፡ፍቅረማርቆስ በድረሰቱ ውስጥ እጅግ ለማመን የሚከብዱ እውነቶችን አስነብቦናል ከነዚህም ውስጥ ተፈጥሮአዊ ውበትን፣ እውነተኛ የፍቅርን ስሜት ፣ ንፁህ ህሊናን፣ ሩህሩህ ልብን ፣ ውሸት ያልሆነ ሽንገላ የሌለበት እውነተኛ ደግነትን ፣ የዋህነትና ቅንነትን በሚሸርጡት የቆዳ ሳዳጎራ ላይ ደርበው የለበሱ ማህበረሰብን አሳይቶናል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ሁለት የብእርና የድምፅ ባለቤቶች አብዝተው የተደነቁበት ማህበረሰብና ቦታ የት ነው ብለን ስንጠይቅ ፍቅረማርቆስና ጎሳዬ ከፊት ሆነው እዬመሩን ከአድማስ ወዲያ ማዶ ከቡስካ ተራራ በስተጀርባ ከከስኬ ወንዝ ባሻገር ከቆንጆና ጀግና መንደር ከሐመሮቹ አምባ ያደርሱናል፡፡
………………
የሐመሯን ወጣት እኔስ የሐመሯን
የጠረፍ ሀገሯን
በጨረቃ ብርሃን አየኋት በማታ
ኢቫንጋዲው ቦታ
…………………..
በሐመር ብሄረሰብ አንድ እጅግ የሚያስደንቅና የሚያስገርም ኢቫንጋዲ የሚባል የጭፈራ ባህል አላቸው፡፡ የኢቫንጋዲ ጭፈራ የሚጨፈረው ሲመሽ ጨረቃ ስትወጣ ሲሆን በዚህ ጭፈራ ላይ የሚሳተፉት ደሞ ያላገቡሴቶችና ወንዶች (ያገቡም ያላገቡም) ናቸው፡፡ ፍቅረ ማርቆስከቡስካ በስተጀርባ በሚለው መፅሃፉ ላይ የኢቫንጋዲ ጭፈራን አጨፋፈር ስልት እንዲህ ሲል አስቀምጦታል ‹‹ በኢቫንጋዲ ከአምስት አይነት በላይ የጭፈራ ስቶች ሲኖሩ ስልቱ በዘፈቀደ ፣መወዛወዝ ሳይሆን አንድ ወጥና ደረጃ በደረጃ የወሲብ ስሜትን ሊቀሰቅስና ሊያጋግል በሚችልበት ዘዴ የተቀነባበረ መሁኑን ካርለት ቀስ በቀስ በሚገባ አጤነች፡፡ መጀመሪያ ወንዶች ብቻ እየዘለሉ ሰውነታቸውን ያሟሙቃሉ ፣ ቀጥሎ ወንዶች አባራሪ ሴቶች አቅጣጫ ቀያሪ እየሆኑ ይሾራሉ ፣ ከዚያ የወንዶች ጭን በሴቶች ጭን ስር ያልፍና ውስጥ ሱሪ አልባ ገላዎች አንዱ ‹‹ጄኔኔተር›› ሌላው ‹‹ኦፕሬተር›› ይሆኑና በሚፈጥረው የኤሌክትሪክ ሞገድ ሲናጡ ሁለቱም ተያይዘው ወደ ጫካ ይሰወራሉ ፡፡ ጭፈራ….ግለት…ጫካ…እርካታ ብቻ አበቃ፡፡›› ይለናል፡፡ ምናለባት ጎሳዬ እዚህ ጭፈራ ላይ ታድሞ ይሆን ….
………………….
በሰማይ ከዋክብት ታጅባና ደምቃ
ድቅድቁን ጨለማ ሲገፈው ጨረቃ
የወግ የልማዱ ጭፈራው ሲደራ
ለፍቅሯ ታዘዝኩኝ እኔስ ለሃመሯ
………………
ብሎ የዘፈነው ? አዎ ሐመር የኢትዮጵያ አንዱ ጌጥ ፣ የኢትዮጵያ አንዱ ውበት ነው፡፡ …በሐመር ብሄረሰብ ሁሉንም ነገር እንደተፈጠረ ሳይበረዝ ፣ ሳየከለስ እናገኘዋለን…ያልተበረዘ ባህል ፣ ያልተበረዘ እምነት ፣ ከጥቅም ጋ ያለተያያዘ ደግነት ፣ ውሸት የማያደፈርሰው መተማመን ፣ ከንፁህ ልብ የሚመነጭ ፍቅር ፣ ጥላቻና ቀናት የሌለበት መተሳሰብ ፍፁም የልጃገረዶች ነፃነት ተፈጥሮ እንደአፈጣጠሯ የምትኖርበት ማህበረሰብ ሐመር፡፡ ፍቅርማርቆስ ደስታ በዚህ ማህበረሰብ አኗኗር ዙሪያ ‹‹ ከቡስካ በስተጀርባ ፣ ኢቫንጋዲ እና የዘረሲዎች ፍቅር ›› የተሰኙ መፅሃፍቶች ሲኖሩት በውስጡ ደግሞ የተለያዩ ገፀ-በሓሪያትን አካቶ የሐመርን ብሄረሰብ አኗኗር ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ጀግንነት ፣ ፍቅርና ኩራትን በደልቲ ገልዲ ፣ ሃያል ፍቅርና ፅናትን በጎይቲ አንተነህ ፣ ትህትናንና ስብእናን በከሎ ሆራ ፣ ፍፁም በማህበረሰብዊ ፍቅር መነደፍን ደሞ በአንተነህ ይመርና በከርለት አልፈርድ አሳይቶናል፡፡ ከቡስካ በስተጀርባ ከወደ ማህል ገፅ ላይ ላይ ቀንጨብ አድርጌ ልውሰድና ላስነብባቹ ‹‹ ደልቲ እቀፈኝ ፤›› አለችው ደልቲ እንደተባለው ሳዳገራውን( ሽርጡን) አውልቆ ተጠጋት እንደተለመደው ጠበቅ አድርጎ አቀፋት፡፡ እሷ ግን ጠራቸው ‹‹ ጠበቅ አድርገህ እቀፈኝ ትንፋሼን ሳትጠብቅ ሳመኝ ፤ ትጨነቃለች ፤ መተንፈስ ያቅታታል ብለህ ብለህ እንዳታስብ እቀፈኝ ፤ ሳመኝ …አካሌ ካንተ ገላ ጋር አንድ እስኪሆን ወዳንተ ለጥፈኝ ፡፡በእቅፍህ ውስጥ
እንደተደሰትኩ በእቅፍህ ውስጥ ነፍሴ ትለፍ›› አለችው ደልቲ እንደተባለው አቀፋት በመካክላቸው አየር እንኳን የሚያልፍበት ቀዳዳ አልተወም ፡፡ሁለመናዋን ከፋፍታ ሰጠችው እሱ ደግሞ ሁለመናዋን ዘጋጋላት ፡፡ በጣም አጥብቆ ዘጋው ፡፡ እሱ የዘጋውን ማንም ሰው ዘላለም ዝግ እንደሆነ እንዲኖር ጎይቲ ተመኘች፡፡›› ስለ እውነተኛ ፍቅር ስናስብ አስቀድሞ በአይምሯችን የሚመጣው ፍቅር-መቃብር የሰብለ ወንጌልና የበዛብህ ታሪክ ነው ፡፡ ነገር ግን ከቡስካ በስተጀርባን ስናነብ ደግሞ ከበዛብህና ከሰብለ ወንጌል ባለተናነሰ በደልቲ ገልዲን እና በጎይቲ አንተነህን ልብ ውስጥ ያለውን ፅኑ ፍቅር እናደንቃለን፡
፡ ውድ አንባብያን ደራሲ ፍቅረማርቆስ ድስታን እና ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬን ከልቤ እያመሰገነኩ ለእናተ ደግሞ መጀመሪያ የጎሰዬን ኢቫንጋዲን ሙዚቃ እንደሰሙት በመቀጠል ደሞ ከቡስካ በስተጀርባን እንድታነቡት ካበዝኳቹ ከዛ………ከዛማ ምን ጥያቄ አለው በመጣችሁበት መንገድ ትጨረሱታላችሁ፡፡
………..
ካድማስ ወዲያ ማዶ ቡስካ በስተጀርባ
እግር ጥሎኝ ባያት ፍቅሯ ልቤ ገባ
በራቁት ደረቷ ተወድሮ ጡቷ
እጅ ወደላይ ብሎ ማረከኝ ውበቷ