>
5:28 pm - Friday October 10, 7355

It is my WiFi  (በእውቀቱ ስዩም)

It is my WiFi

 (በእውቀቱ ስዩም)

 ጎረቤቴ  ቺስታ ግብፃዊ ነው፤   ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከገነባች እንግዲህ ተስፋ የለንም ብሎ አሜሪካ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ በመኖር ላይ ይገኛል !  እኔ ከወራት በፊት “ግድቡ ተሽጡዋል” እሚለውን  ዜና አምኜ  ጥገኝነት መጠየቄን የሰማ አይመስለኝም  !
   ኑሮየ ለክፉ እሚሰጥ አይደለም!  ኡበር እነዳለሁ! ዩቲውብ ደሞ በወር  አምሳ ዶላር ይልክልኛል !  ግብጡ ግን ችግረኛ ነው! ስላሳዘነኝ  እኔ በወር ሰማንያ ዶላር እምከፍልበትን  ዋይፋይ  እንዲጠቀም ፓስወርዱን ሰጠሁት !   አንባቢ ሆይ! ለዚህ ደግነቴ ያገኘሁት ምላሽ ምን ይመስልሃል?  ባለፈው መንገድ ላይ አግኝቶኝ  እሳት ጎርሶ  እሳት ለብሶ   “ኢንቲ አዩኒ” ብሎ ባረቀብኝ !  አረብኛ ለማታውቁ  ልተርጉምላችሁ: “  ፊልም ላይ ተጥደህ እየዋልክ  ኔትዎርኩን ስሎው እያደረግህብኝ  ነው! “ ማለቱ ነው ! እረ ገለስ! it is my wifi ብየ ቀወጥኩት!
  (በነገራችን ላይ ግብፆች “ ጀ“ የሚል ቃል የላቸውም፤ ገማል ይላሉ እንጂ ጀማል አይሉም! ለዛ ነው” ጀለስ “ ማለት ሲገባኝ “ገለስ “ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩኝ ! ለምሳሌ፤ ባህር ዳርቻ አሸዋ ላይ  በጀርባህ ተኝተህ፤ ፀሃይ በመሞቅ ላይ እያለህ፤  አንዲት ግብፃዊ “ገላህ  ያምራል ካለችህ” ሙገሳ አይደለም! ሃራስመንት ነው!
  ባለፈው ያዲሳበባ ሰው ከቤቱ በረንዳ ተገጥግጦ  “ግድቡ የኔ ነው” እያለ ሲቀውጠው   በዩቲውብ አየሁ  !   የህዝቡ  አቀዋወጥ ፤ ግብፅ በሌሊት ግድቡን  ባቆማዳ ጠቅልላ፤ በግመል አሸክማ ስትሄድ የደረሰባት ነው እሚመስለው  !
   በነገራችን ላይ ፤ ግድቡን ትተን ስለባልቦላው ማውራት የምንጀምርበትን ጊዜ  አልናፈቃችሁም?!   እንደኔ እንደኔ፤ ግድቡ ስራ ሲጀምር   ለአንድ አመት ያህል ህዝቡ ለመብራት መክፈል የለበትም! እንዲያውም በጊዜ  መብራት አጥፍቶ የተኛ ሰው   በወንጀል ቢጠየቅ  ደስ ይለኛል !
   የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ግድቡ ተርባይኑን ማንቀሳቀስ ቢያቀተው ወይም ተርባይኑን  ለጥቂት ቢስተውስ ? ወይ ደግሞ የግልገል ጊቤን አርአያ ተከትሎ ቢገግምስ?   እኔ ጣጣ ያለው አይመስለኝም  ! ሌላው ቢቀር  አሳ እናረባበታለን! አሳ የበላ ትውልድ ጭንቅላቱ ይሰራል !  ጭንቅላቱ ከሰራ ይመራመራል!  ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ኒውክልየር ይፈጥራል !
 በነገራችን ላይ አባይ  በተነሳ ቁጥር  “ አባይ ማደርያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል “ የሚለው እጅ እጅ እሚል  ተረት መጠቀሱ  የማይቀር ነው !  የሆነው ሆኖ ፤ከግድቡ  ሙሌት  በሁዋላ ግንዱ ለማን ደረሰ? ዶክተር አቢይ;-ሶስት ቦታ ተቆርጦ እንደ ቅርጫ እንካፈለው እንደማይል ተስፋ አለኝ!    እዛው  ግብፅ ፈልጣ ሩዝ ትቀቅልበት!
 ከአበዛሁት አትፍረዱብኝ !  የአገር ፍቅር ሲበዛ ካቲካላ ነው!  አናት  ላይ ይወጣል!
(ጀዋ ካህሊል🙏)
Filed in: Amharic