>

ምነው ጫጫታው በረከተ?  መጽሐፍ ቅዱስም አትጥቀሱ ነው...??? (አባይ ነህ ካሴ)

ምነው ጫጫታው በረከተ?  መጽሐፍ ቅዱስም አትጥቀሱ ነው…???

አባይ ነህ ካሴ 

+ ታጠቁ ብሎ ያስተማረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! በመቀጠልም የእርሱ ፍጡራን እና ደቀ መዛሙርቱ ትምህርቱን እስተምረውታል! ቃሉ ካስፈለገ እነሆ፡-
* ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፡፡ ሉቃ ፲፪፥፴፭።
 
* እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፡፡ ኤፌ ፮፥፲፭።
* ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኖራችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ። ፩ጴጥ ፩፥፲፫።
ከዚህ ቀደም “እመን እንጅ አትፍራ” የሚል ጥቅስ በልብሳችሁ ላይ አትጻፉ የሚል ክልከላ በተደጋጋሚ ይደረግብን ነበር፡፡ አንዲት ሃይማኖት የሚለውንም እንደዚሁ፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይኹን የሚለውን ቃል ጠቅሰው ቅዱስነታቸው መልእክት ቢያስተላልፉ የዛሩ መንፈስ ያደረበት ሁላ መንጫጫት ጀመረ፡፡
ሁሉን እንተርጉም ባዮች ቅዱስ ፓትርያርኩ ታጠቁ ብለው ዐወጁ እያሉ እንደ ወስከንቢያ ይራወጣሉ፡፡ ዐዋጅ ከኾነባችሁ አልሰማችሁ እንደሁ እንጅ  ከታወጀ ፪ ሺህ (2000) ዓመታት አለፉት፡፡ ጣታችሁን የምትቀስሩት ምላሳችሁን የምታውለበልቡት ቅዱስ አባታችን ላይ ሳይኾን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደኾነ እናስታውሳችሁ፡፡
ክርስቶስን እናምናለን እያላችሁ ቃሉን ግን የማትቀበሉ ከኾናችሁ በምን ቃል እንጥራችሁ? ትርጉሙም ተዘልላችሁ አትቀመጡ፣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ የሚል ነው፡፡ አትዘጋጁ የሚል የሃይማኖት መምህር ቤተ ክርስቲያን ኖሯት አያውቅም፡፡ አትዘጋጁ የሚል ባንዳ ብቻ ነው፡፡
ዝግጅቱ ወይም መታጠቁ ደግሞ ሞት በየትኛው ሠዓት ወር እና ዓመት እንደሚመጣ ስለማናውቅ ንስሐ ገብተን ሥጋ ወደሙን ተቀብለን ሥጋና ነፍሳችንን ቀድሰን ሳንዘናጋ እንድንኖር ነው፡፡ መታጠቅ ለሱሪም ለቀበቶም ለሰይፍም እንደሚጠቀሰው ሁሉ ለንቃትም ይጠቀሳል፡፡ “የወገቡ መታጠቂያ ጽድቅ፥ የጎኑም መቀነት ታማኝነት ይኾናል።” ሲልም ቅድስና ንጽሕና እንደ ትጥቅ ተነግሯል፡፡ ኢሳ ፲፩፥፭። ኃይል መንፈሳዊ ነውና፡፡
ስለ ትሕትናም ደግሞ “ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል ቀርቦም ያገለግላቸዋል።” ይላል፡፡ ሉቃ ፲፪፥፴፯። አገልጋይ የሚኾነው ጌታው ሲኾን ባሪያዎቹ ደግሞ ተገልጋይ ሲኾኑ ጌታው ስለሚያደርገው የትሕትና ሥራ ወገቡን መታጠቁን ያመለክታል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅዱሳን ሐዋርያቱን እግር ሲያጥብ ወገቡን ታጠቀ መባሉ ለዚህ ነው፡፡ “ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ” እንዲል፡፡  ዮሐ ፲፫፥፬-፭።
አንዳንዶች ግን ከሰይፍ በቀር መታጠቅ አያውቁም፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ፓትርያርኩን ንግግር በመሰላቸው እየዘነጣጠሉ ሲያመነዥኩት ይታያሉ፡፡ በተለይም ተከፋይ አክቲቪስቶች ሥራዬ ብለው ይዘውታል፡፡
v ሲገድሉን መታገሳችን እውነት ነው፣
v ስንሞት አይዟችሁ ባይ እንደሌለንም ዐውቀናል፣
v ሞት እያለ ብንዘናጋ ግን ጥፋቱ የእኛ ነው፡፡
ከጭካኔ በላይ ሞትን ከልዩ ልዩ ስቃይ ጋር ለ፴ ዓመታት ተሸክመነው ኖረናል፡፡ ለእናንተ ድንቁርና ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ ከመጥቀስ መቼም ቢኾን አንቆጠብም፡፡ ወይም እናንተ ስላልገባችሁ ተብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ኤዲት አይደረግም፡፡ ሲያምራችሁ ይቅር! በዚህ የሚሸማቀቅ አንድም ኦርቶዶክሳዊ አታገኙም፡፡ መንፈሳዊም ተፈጥሯዊም መብታችን ከኾነው ራሳችንን ከመከላከል አትቆረቁቡንም (አትመልሱንም)፡፡
Filed in: Amharic