>
5:18 pm - Monday June 15, 2922

"ኦነግ ኦነግ ነው ከብልጽግና ጋር የተለየ ግንኙነት የለንም..."  (አቶ አራርሶ ቢቂላ)

“ኦነግ ኦነግ ነው ከብልጽግና ጋር የተለየ ግንኙነት የለንም…”

 አቶ አራርሶ ቢቂላ 


የታገዱት ሊቀ መንበር የሚያቀርቡት ሃሳብ ኦነግን አይመለከተውም
• በዚህ ምርጫ የምንፈልገው፣ የዲሞክራሲ ልምምድ እንዲጀመር ነው

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ተራዝሞ የነበረው 6ኛው አገራዊ  ምርጫ ዘንድሮ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በአመራር ውዝግብ ውስጥ የሚገኘው ኦነግ የታገዱት ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ “የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት” የሚል ቅስቀሳ መጀመራቸው እየተነገረ ሲሆን  የእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የአመራር ቡድን በበኩሉ፤ “ለምርጫው እየተዘጋጀን ነው” ይላል፡፡ የታገዱት ሊቀ መንበር የሚያቀርቡት ሃሳብም ኦነግን አይመለከተውም ብለዋል፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በኦነግ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከአመራሩ ከአቶ ቀጀላ መርዳሳ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡
ኦነግ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ የሚሳተፍበት እድል ተፈጥሯል፡፡ ይህን እድል ለመጠቀም እያደረጋችሁት ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ላይ ተሳትፎ አያውቅም። በ1984 ምርጫ ለመሳተፍ እጩዎች አዘጋጅተን ነበረ፡፡ በመራጮች ምዝገባ ላይ በተፈፀመ ማጭበርበር ምክንያት አቋርጠን ወጣን፡፡ ከህወኃት ጋርም ያጋጨንና ከሽግግር መንግስቱም ተገፍተን የወጣነው በዚያ ምክንያት ነው፡፡ አሁን ሊካሄድ የታሰበው ምርጫ፣ በኮሮና ምክንያት መራዘሙና አሁንም ያን ያህል አመርቂ እንቅስቃሴ ያለው አለመሆኑ፣ በተለያየ አካባቢ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸው፣ ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ በኋላ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ በርካታ ችግሮች መፈጠራቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መታሠራቸው — እነዚህ ሁኔታዎች ፈጥነው የማይስተካከሉ ከሆነ ትንሽ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በዋናነት በኦሮሚያ የምንንቀሳቀስ እንደመሆናችን፣ የክልሉ አለመረጋጋት ለምርጫ የምናደርገው ዝግጅት ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ መንግስት ፀጥታውን ማስጠበቅና በነፃነት እንድንቀሳቀስ የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን አለበት፡፡ መንግስት ፀጥታ ካስከበረና አስተማማኝ ሁኔታ ከተፈጠረ በሙሉ ሃይላችን በምርጫው እንሳተፋለን፡፡
ምርጫው በኮሮና ምክንያት ሲራዘም የኦነግ አቋም ምን ነበር?
መራዘሙ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በ2013 ዓ.ም ግንቦት ወር መካሄድ አለበት ነበር ያልነው፡፡ አሁንም በዚያ አግባብ ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ ስለዚህ እኛ በፈለግነው መንገድ ነው እየሄደ ያለው፡፡
በቅርቡ ከኦነግ ከሊቀ መንበርነታቸው የታገዱት አቶ ዳውድ ኢብሳ ግን “ከመስከረም 25 በኋላ መንግስት የለም፤ የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት” ብለዋል፡፡ ኦነግ አስቀድሞ እንዲህ አይነት አቋም ነበረው?
በጭራሽ አልነበረውም፡፡ እሳቸውም ባሉበት ተሰብስበን የወሰንነው “በችግሩ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነው፤ ነገር ግን ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይካሄድ” በሚል ነው፡፡ አቶ ዳውድ፤ አሁን ከታገዱ በኋላ ያመጡት አዲስ ሃሳብ ነው፡፡ እኚህ የታገዱት ሊቀ መንበር ከህወኃት ጋር እየተናበቡ ነው የሽግግር መንግስት እየጠየቁ ያሉት፡፡ ይሄ ተግባራዊ መሆን የሚችል አይደለም፡፡ እኛ በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረንበት፣ “የሽግግር መንግስት በዚህ ጊዜ ማቋቋም ከባድ ነው፤ የተወሳሰበ ችግር ነው የሚፈጥረው፣ በተጨማሪም ህገመንግስትን መነካካት አያስፈልግም; ብለን ነበር የወሰነው፡፡ ስለዚህ የታገዱት ሊቀ መንበር ያቀረቡት ሃሳብ ኦነግን አይመለከተውም፡፡ እኛ ለምርጫው እየተዘጋጀን ነው፡፡
ለምርጫው ብቁ የሚያደርጋችሁ አደረጃጀት ፈጥራችኋል?
ባለፈው ሁለት አመት በተለያዩ ምክንያቶች ቢሮዎችን ሲዘጉ፣ አባሎቻችንና  አመራሮችን ሲታሠሩ ነበር፡፡ ይሄን ከመንግስት ጋር እየተነጋገርን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ አሁንም በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ላይ ጫናዎች አሉ፡፡ ኦነግን ከትጥቅ ትግል ጋር እያያዙ ሰዎችን የማሠር ነገር አለ፡፡ እኛ ግን ደጋግመን እንደገለጽነው፤ በትጥቅ ትግል እየተሳተፍን አይደለም። በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ ነው ትግል እያደረግን ያለነው፡፡ ነገር ግን እንቅፋቶች እያጋጠመን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ተራምደናል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲከፈት ነው የምንጠይቀው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ኦነግ ስሙ ሲነሳ ብዙዎች “አክራሪ ብሔርተኛ፣ ጨፍጫፊ” አድርገው ነው የሚያስቡት? የዚህ ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?
ኦነግ በዚህ መንገድ እንዲታይ የተደረገው ለፖለቲካ ሲባል በተካሄደበት የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው፡፡ ባለፉት ዘመናት ስሙ ጠቁሮ፣ እንደ ጭራቅ የሚታይ ነበር። ይህ የሆነው ግን … ባደረግነው ነገር ሳይሆን ለፖለቲካ ሲባል በተደረገበት የስም ማጥፋት ዘመቻ ምክንያት ነው፡፡ ይሄን አመለካከት ለመለወጥም ጥረቶች እያደረግን ነው። በማንኛውም ሀገራዊ መድረኮች ላይ እየተሳተፍን፣ የኦነግን ማንነት ለማሳወቅ እየጣርን ነው፡፡ በሚዲያዎችም እየቀረብን  ነው፡፡ አንዳንዶችም “ኦነግ ማለት እንዲህ ያሉ ሰዎች የተሰባሰቡበት ድርጅት መሆኑን አናውቅም ነበር” እያሉ ወዳጆች እየሆንን ነው፡፡ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ኦነግን በመጥፎ ለመሳል ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ገዳይ፣ ጨፍጫፊ እየተባለ ድራማ ነበር የሚሠራው። ለምሣሌ ባሌ ላይ የህወኃት ሠራዊት፣ ሠላማዊ ሰዎች ጨፍጭፎ፣ “የኦነግ ሠራዊት ነው የፈፀመው” ያለበት ጊዜ ነበር! ያ አሁን እውነቱን በሚያውቁ ሰዎች ምስክርነት ተጋልጧል። በወቅቱ ግን የድርጅትን ስም ማጥፋትና በመጥፎ በመሳል ማሸነፍ የሚባል የሴራ ፖለቲካ ነበር፡፡ ኦነግ የዚህ ሴራ ሰለባ ነው፡፡
በአርባጉጉና በበደኖ የተፈፀሙ ጭፍጨፋዎችስ?
እነዚህም ቢሆኑ ኦነግን የሚመለከቱ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ኦነግ በእነዚህም ላይ ተሳትፎ አልነበረውም፡፡
ምንድን ነው ማረጋገጫው? በገለልተኛ አካል ተጣርቷል?
ተጣርቶ ቀርቧል፤ ነገር ግን የኦነግን አስተሳሰብ ማሸነፍ ሳይቻል ሲቀር እንዲህ አይነት ነገር ይለጠፍበታል፡፡ የመላ አማራ ህዝብ ድርጅትም በወቅቱ አጣርቶ ኦነግ እጁ እንደሌለበት መግለጫም አውጥቷል። ኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ናቸው ድርጊቱን የፈፀሙት፤ ይሄ ተጣርቶ ተረጋግጧል፡፡ የበደኖውም እንዲጣራ ጠይቀን ነበር፡፡ ነገር ግን ህወኃት ፈጽሞ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ አልፈለገም። ከተጣራ እውነቱ ስለሚወጣ ለማጣራት አልፈቀድም፡፡ ደጋግመን እንዲጣራ ስንጠይቅ ነበር፤ ነገር ግን የሚሰማን አላገኘንም፡፡
እነዚህን መሰል “ክሶች” ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አያሳድርባችሁም?
ምንም ተጽእኖ አይኖረውም፡፡ ሠላማዊ መሆናችንን በተቻለን መጠን፣ በተለያዩ መድረኮች ለማስረዳት እየሞከርን ነው። የተለያዩ የራሳቸው አላማ ያላቸው ሰዎች ተሽለኩልከው ጥፋት በመፈፀም፤ ወደ ኦነግ ለማላከክ የሚደረግ ካልሆን በስተቀር ጨዋና ስነስርዓት ያለው ድርጅት መሆኑን በተግባር እያረጋገጥን እንሄዳለን፡፡ በህዝቡ ዘንድም ብዙ ድጋፍ አለን፡፡ በስም ማጥፋትና በተለያዩ የተዛቡ አተያዮች የተነሳ ድምጽ እናጣለን የሚል ግምት የለኝም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ምርጫውን ፍትሃዊ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኦነግ በቀጣዩ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊነት ላይ ምን ያህል እምነት አለው? የጠ/ሚኒስትሩ ቃልስ የሚፈፀም ይመስልዎታል?
ጠ/ሚኒስትሩ ያሉት ይፈፀማል ወይ የሚለውን ጊዜው ሲደርስ ነው የምናየው። የምርጫ እንቅስቃሴ የሚጀመርበት የጊዜ ሰሌዳ ከታወጀና ወደ እንቅስቃሴ ከተገባ በኋላ እያየን የምንገመግመው ይሆናል። ነገር ግን አሁን ላይ አስጊ የሆኑ ችግሮች ይታዩናል፡፡ ገዥው ፓርቲ የመንግስት ሃብት፣ ሚዲያዎች በቁጥጥሩ ሥር ናቸው። ምን ያህል ሁሉንም ፓርቲ በፍትሃዊነት ያስተናግዳል? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡
በምርጫው ላይ ያላችሁ እምነትና ተስፋ ምን ያህል ነው?
እንግዲህ ተስፋ አድርገን ነው የምንገባበት፡፡ ነገሮችን በተስፋና በቅንነት ማየቱ ይጠቅማል። መቼም ሁሉም አሸናፊ መሆን አይችልም፡፡ ይሄንንም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች ራሳቸው ምን ያህል የሌላውን ነፃነት ጠብቀው፣ እርስ በእርስ ሳይገፋፉ ይጓዛሉ የሚለው በራሱ ያጠያይቃል፤ ሌላ ግምገማን ይፈልጋል። ምርጫ በባህሪው አስቸጋሪ ነው፡፡  ነገር ግን መስራት የሚያስፈልገው ግጭቶች እንዲወገዱ ማድረግ ላይ ነው፡፡ እኛም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው በሚል አይደለም ወደ ምርጫው የምንገባው፡፡
በምርጫው ልታሳኩት የምትፈልጉት ምንድነው?
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ እኛ ማሳካት የምንፈልገው፣ ምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒነት ያለው መሆን አለበት የሚለውን ነው፡፡ ማንም ያሸንፍ ማን ዋናው ነገር ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ፣ የሂደቱ አካል ሆኖ፣ የራስን ሚና መጫወት ነው አላማችን፡፡ በዚህ ምርጫ ዋናው የምንፈልገው፣ የዲሞክራሲ ልምምድ እንዲጀመር ነው፡፡
ምርጫውን የተሳካ ለማድረግ ኦነግ የሚያቀርበው ምክረ ሃሳብ አለ?
በዋናነት ሠላም መጠበቅና መረጋገጥ አለበት፡፡ በመላ ሀገሪቱ ሠላም ለማስፈን ጠንካራ ስራ ሊሠራ ይገባዋል፡፡ በየአካባቢው ያሉ የፀጥታና የስራ አጥነት ችግሮች ከወዲሁ መስካከል ይኖርባቸዋል፡፡ የፀጥታ ሃይሎች ከህብረተሰቡ መሃል ወጥተው ወደ ድንበርና ካምፕ መመለስ አለባቸው፡፡ ሌላው በምርጫ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከወዲሁ ውይይት መጀመር ይገባቸዋል። ቀደም ሲል የተጀመሩ ውይይቶችም መቀጠል አለባቸው፡፡ ምርጫ ቦርድም እነዚህን ውይይቶች ማበረታታት አለበት። ከውይይት መልካም ነገር ይገኛልና። ይሄ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ኦነግ የአመራር ቀውስ ከገጠመው በኋላ እርስዎ ያሉበትን የአመራር ቡድን እንደ ብልጽግና ተለጣፊ፣ ከሃዲ አድርገው የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ እናንተ በዚህ ላይ ምን ትላላችሁ?
ይሄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የተለመደ የስም ማጥፋት አካሄድ ነው። አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ ስም ማጥፋትና ማጠልሸት የተለመደ ነው፡፡ አንዱ ፍፁም ተወዳዳሪ የሌለው ታጋይ ለመምሰል የሌላውን ስም ማጥፋት አለበት፡፡ ኦነግ ውስጥ ደግሞ ይኼ የተለመደ ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ አካሄድ ተገፍተዋል፡፡
በተለይ ካለፉት 20 አመታት ወዲህ፣ ብዙ ከህዝብ የወገኑ ሃቀኛ ታጋዮች ;ከሃዲ፣ ጠላት; እየተባሉ በአንድ ጀንበር እንዲፈረጁ ተደርገዋል፡፡ ይሄ አይነቱ ፍረጃ ግን ህብረተሰቡ ውስጥ የለም። በሚዲያው ላይ ነው ያለው። ስለዚህ ብዙም ውጤታማ አይሆንም፡፡ እኛ አሁን ህዝቡ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይሄ ፕሮፓጋንዳ የሚሠራ አይደለም። እነሱም ከህወኃት ጋር ተቀናጅተው ነው ይሄን እያደረጉ ያሉት፡፡ ግን አይሳካላቸውም፡፡
አቶ ዳውድ ከህወኃት ጋር  እየተናበቡ ነው የሚሰሩት ብላችሁ ታምናላችሁ?
ኦነግ እሳቸው በመሩት ስብሰባ የወሰነውን ውሣኔ፣ በሁለት ወር ውስጥ ሽረው ነው ዛሬ “የሽግግር መንግስት ይቋቋም” የሚሉት። ይሄ እየተናበቡ እየሠሩ መሆኑን ያሳያል። ግለሰቡ ብቻቸውን ይሄን ማወጃቸው፣ ከማን ጋር እየሠሩ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከህወኃት ብዙ ገንዘብ ይፈስላቸዋል እየተባሉ ሲታሙ ነበር፡፡ እኛ ይሄን ሁሉ መናገር አልፈለግንም ነበር፤ ግን “ከብልጽግና ጋር በጥቅም ተሳስራችኋል” የሚል ዘመቻ ስለተከፈተብን ነው፡፡
ከብልጽግና ጋር በጥቅም ተሳስረዋል ከተባለ፣ በዚህ መጠየቅ ያለባቸው የታገዱት ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እኛ ዛሬም በሚኒባስ ታክሲ ነው የምንሄደው፡፡ እሳቸው መንግስት በመደበላቸው V8 መኪና ጥበቃ ተመድቦላቸው ነው የሚዘዋወሩት። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል፤ ጠልቀን  መግባት አንፈልግም። እውነቱ ግን እኛ ከብልጽግና ጋር ምንም የተለየ ግንኙነት የለንም፡፡ ኦነግ ኦነግ ነው፡፡
ምርጫ ቦርድ የኦነግን የአመራር ውዝግብ በተመለከተ እስካሁን የሰጠው ውሳኔ የለም…?
በቅርቡ ጉዳያችንን ተመልክተው ውሣኔ ያሳልፋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ አኛ በእጃችን ያሉ በርካታ ማስረጃዎችን አቅርበን ነው ውሣኔውን እየተጠባበቅን ያለነው፡፡
የኦነግ የምርጫ መወዳደሪያ “ብሔርተኝነት ነው፤ የተደራጀ ፖሊሲና ፕሮግራም የለውም” ለሚሉ ተቺዎች ምላሽዎ ምንድነው?
ይሄ የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ይፋ እናደርጋለን፡፡ እኛ መወዳደሪያችን ብሔርተኝነት ሳይሆን ፖሊሲያችን ነው። ፖሊሲያችንን እያጠናቀቅን ነው፡፡ ማኒፌስቷችንም ተዘጋጅቷል፡፡

Filed in: Amharic