>
5:28 pm - Thursday October 9, 6341

ይድረስ ለሞጋሳ አሞጋሾች! (አቻምየለህ ታምሩ)

ይድረስ ለሞጋሳ አሞጋሾች!

አቻምየለህ ታምሩ


ይህ ጽሑፉ የተጻፈው «የማንነት ጭቆና ደርሶብናል» ሲሉን የነበሩ የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሀያ በላይ የኢትዮጵያ ነገዶችን ማንነት በተሳካ ሁኔታ ያጠፋውን ሞጋሳን «አሞግሱት» እያሉ ዘመቻ በመክፈታቸውና ይህን አዲስ ዘመቻም  ስለ ሞጋሳ ምንነት ከስሩ የማያውቁ የዋሆች በመቀላቀላቸው ነው።  

ሞጋሳ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ሲስፋፉ በጦርነት ያሸነፉትን ኦሮሞ ያልሆነ ሰው በኃይል ማንነቱን በማስቀየር ጎሳ ሰይመው የራሳቸው የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው። ይህ ስርዓት የኦሮሞ አባገዳዎች የቋንቋ፣ የነገድ፣ የማንነትና የባሕል ማጥፋት በተሳካ ሁኔታ ያካሄዱበት ሥርዓት ነው። አንድ ሰው ወዶ የራሱን ማንነት ቀይሮ የሌላ ማንነት ሊጭን አይችልም። ስለሆነም አንድ ሰው በኃይል ሳይገደድ የዘመናት ውጤት የሆነውን የራሱን ማንነትና ቋንቋ በጤና ሊተው አይችልምና ስለ ሞጋሳ ጤነኛነት በከንቱ ልትነግሩን አትሞክሩ።

ከቅርቡ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነን ሲሉን የነበሩ ሰዎች ጭምር ሞጋሳን እያሞገሱ ለማስቀጠል እያሳዩት ያለው ፍላጎት አስገራሚ ደረጃ ላይ ደርሷል። አሁን እንደገባኝ እነዚህ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ሲሉን የነበሩ ሰዎች በኢትዮጵያዊነት ጠበል ቢጠመቁ የጎሰኛነት ሰይጣን እንደሚወጣቸው ነው።

ሞጋሳ የገዳ ስርዓት ምሰሶ ነው። የገዳ ስርዓት በኦነጋውያንና ደቂቆቻቸው እንደሚደሰኮረው እንኳን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊሆን ቀርቶ የፖለቲካ ስርዓትም አልነበረም። የገዳ ስርዓት ወታደራዊ ስርዓት ነበር። አባ ባሕሪ ምስጋና ይግባቸውና የገዳ ስርዓትን ከእድሜ ደረጃ አወጣጥ ጀምሮ እያንዳንዱ የስርዓቱ ደንቦች የተቃኙት ወታደራዊ የበላይነትን ለማስገኘት እንደሆነ አስገንዝበውናል። በገዳ ስርዓት መሪ ሆኖ የሚመረጠው ሰው ከእድሜ አቻዎቹ ብዙ የገደለው ነው። ከመመረጡ በፊት ሰውን አድኖ ገድሎ ለመረጃነት ይዞ ያልተገኘ በገዳ ስርዓት አይመረጥም። በገዳ ስርዓት አንዱ ሉባ ከጓደኞቹ መካከል በልጦ ለመገኘት በተለይ ወንዶችን፣በእናት ማኅጸን ውስጥ ያለ ሕጻንን ጨምሮ ገድሎ እንደ ሽልማት ይዞ መቅረብ የስርዓቱ አንድ አካል ነው። ባጭሩ የገዳ ስርዓት የገዳዮች ስርዓት ነው።

የገዳ ስርዓት ምንም ዓይነት የዲሞክራሲ መልክ እንዳልነበረው የሚያሳየው ሌላው አቋሙ የፖለቲካ ስርዓቱ መሪ (አባ ቦኩ) በቤተሰብ ተወራራሽ ወይም ከልጅ ልጅ የሚያልፍ መሆኑ ነው። እውነተኛው ኦሮሞ ምንም እንኳን በቁጥር ትንሽ ቢሆንም ወታደራዊ የበላይነትን እንዲያገኝ ያደረገው ይህ ለጦርነት የሰላው አደረጃጀቱ ግን ቁጥሩ እንዲበዛ አድርጎታል። አባ ቦኩ (የፖለቲካ ቢሮው) ከልጅ ልጅ የሚተላለፍ በመሆኑ ተቋማዊ ትውፊቱን (institutional memory) ሲያስቀጥል የወታደራዊ ክንፉ የሚሞላው በጉልበትም፣ በእድሜም የመግደል ችሎታቸው ከፍተኛ በሆኑ መሪዎች ነበር። ይህ በሰሜንም ሆነ በሌሎች የደቡብ ማኅበረሰቦች ከነበረው ከቤተሰብ ወደ ቤተሰብ ከሚተላለፈው የስልጣን ሽግግር ሙሉ በሙሉ የተለየ ነበር።

የሞጋሳ ስርዓት የተጀመረው እውነተኛ ኦሮሞ የሆኑት የቦረናና ባሬንቱ ነገዶች መስፋፋት ሲጀምሩ ግዛታቸው እያሰፋ በመሄዱ ቁጥራቸው ሳስቶ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ነበር። በዚህ ጊዜ የተቆጣጠሩትን አካባቢ ሙሉ በሙሉ ከመግደል የማረኩትን ባሪያ፣ ገባርና ገርባ ቢያደጉት የበለጠ ጠቀሜታ እንዳለው ተረድተው የመጀመሪያ ልምዳቸውን ሻሽለውታል።

በዚህ ጊዜ ነበር የጉዲፈቻና ሞጋሳ ስርዓት በስራ ላይ መዋል የጀመሩት። ቦረናና ባሬንቱ ሲስፋፉ በጦርነት የያዙትን ሕዝብ ገድለው ከመጨረስ ይልቅ ባሕሉንና ቋንቋውን በማጥፋት፣ በምንም ዓይነት ማንነቱን ወደ ኋላ እንዳያስታውስ አድርገው የአባቱን ስም ሳይቀር በመቀየር ለጦርነቱ የሚማገድ ኃይል ለማድረግ ነበር ሞጋሳ የተጀመረው። እንዲህም ከተደረገ በኋላ በሞጋሳ የተያዘው ኦሮሞ አልተደረገም ገርባ እንጂ። ገርባ አገልጋይ ብቻ ሳይሆን ኦሮሞው በፈለገ ጊዜ የሚሸጠው ባሪያም ነበር። ይህም ስሪት ከልጅ ልጅ የሚተላለፍ ስርዓት ነበር። በገዳ ስርዓት መሰረት ገርባ ከዚህ የማኅበራዊ ቦታው ወጥቶ መሬትም ሆነ ሌላ ንብረት እንዳያፈራ ይከለክላል። ገርባ የኦሮሞ ንብረት ብቻ ነበር። ባጭሩ ገርባ ምንም እንኳን ኦሮምኛ እንዲናገር ቢገደድም ኦሮሞ ግን ፈጽሞ አልነበረም፤ እንዲሆንም የገዳ ሥርዓትም አይፈቅድለትም።

በ17ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መካከል አብዛኛው የባሪያ አቅራቢዎች ሞቲ የሆኑት አንጋፋዎች እንደነበሩ የተመዘገበ ታሪክ ነው። በዚህም የተነሳ አብዛኛው ባሪያ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነበር። ይህ ማለት ግን ሞቲዎች ለሽያጭ የሚያቀርቡት ኦሮሞዎችን ነበር ማለት አይደለም። በሞቲዎችና አባገዳዎች ለሽያጭ የሚቀርቡት አገልጋይ የነበሩ ገርባዎች ነበሩ። በደቡቡ፣ በምዕራቡና በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል ከአባገዳ መር የዘር ጀኖሳይድ የተረፉት ነገዶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሞቲ ባሪያ ፈንጋዮች ጥቃትን ያስተናግዱ ነበር። ለዚህ የሚከተሉትን እውነታዎች መጥቀስ ይቻላል።

ዳግማዊ አባ ጅፋርን በ1904 ዓ.ም. በሚኖሩበት ጅማ ሄዶ የጎበኛቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም አባ ጅፋር «ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአካባቢውን ሕዝብ በተለይም የሞችን በባርነት ሽጦ እንደጨረሰው» ኦቶባዮግራፊ [የሕይወቴ ታሪክ] በሚል ባዘጋጁት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ አስፍረዋል።

በ1916 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [League of Nations] አባል ለመሆን ባመለከተችበት ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባት ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት የአባልነት ማመልከቻ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት [League of Nations] ለማስገባት ወደ ጀኔቫ የተላከው ቡድን መሪ የነበሩት ራስ ናደው አባ ወሎ በፈረስ ስማቸው «አባ መብረቅ» እንግሊዝ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እንዳትሆን የተቃወመችበትን ምክንያት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፤

«እንግሊዝ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሐን የዘገቡትንና በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኤደንና በግብጽ ባሉት የቅኝ ግዛት መንግሥቱ በኩል የሰበሰበውን ማስረጃ በማያያዝ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለነበረው የባርያ ንግድ ሁኔታ፤ በተለይም የጂማው አባ ጅፋር በከፋ፣ በማጂ፣ በጊሚራና በጉራፈርዳ ሕዝብ ላይ እየካሄዱት ያለው መጠነ ሰፊ የባሪያ ንግድ ለማኅበሩ የፖለቲካ ኮሚሲዮንና ለጠቅላላ ጉባኤ በማቅረብ አባል እንዳንሆን ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብናል» ሲሉ አስረድተዋል።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በአባ ጅፋር አማካኝነት የሚካሄደው የባርያ ንግድ ባጭር ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንዲታገድና የሰው ልጅ መብት በመላው የአገሪቱ ግዛት እንዲከበር የአልጋወራሽ ተፈሪ መንግሥት ለመንግሥታቱ ማኅበር ቃል በመግባት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ከመስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበር 57ኛ አባል ሆና መመዝገቧ በይፋ ታወጀላት።

ባጭሩ በአባ ገዳ የተመራው የኦሮሞ ወረራ ተሳክቶለት ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠር ኖሮ ሁሉም ባህልና ቋንቋ ተጨፍልቆና ተሰልቅጦ ዛሬ ሁሉም አንድ ወጥ ኦሮሞ ብቻ ይሆን ነበር። ለዚህ ማሳያው ቀላል ነው። ኦሮሞ በወረራ የያዛቸው የጥንት ነገዶች ሙሉ በሙሉ ወደ ኦሮሞነት ተቀይረዋል። ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ውስጥ ከኦሮሞ ወረራ በፊት ይኖሩ የነበሩት ጥንታዊ ነገዶች ሁሉ ጸድተዋል። ይህም የሆነው በዋናነት በሞጋሳ ነው። እንድናሞግሰው እየተጠየቅን ያለው ይህንን ጥንታዊ የኢትዮጵያ ነገዶች የጸዱበትን ስርዓት ነው።

ገራሚው ነገር ዛሬ ሞጋሳን ሊያሞግሱ የተነሱት ደረቆች «ተበደልን፣ የዘር ጥቃት ደረሰብን» ብለው ሊያለቃቅሱ የነበሩና በጦረኛ አባገዳዎች ተሸንፈው የተያዙ ገርባ ልጆች መሆናቸው ነው። እነዚህ ገርባዎች ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ተነስተው አባ ላፋዎች [የኦሮሞ የመሬት ከበርቴዎች]፣ ሞቲዎች፣ መልከኞች [የአካባቢ ገዢዎች]፣ አባ ገዳዎች ወዘተ ጠቅልለው ከያዙት መሬት ውስጥ ቀንሰው የሚያርሱት መሬትና የግል ንብረት ባለቤት እስኪያደርጓቸው ድረስ መሬትም ንብረትም እንዳልነበራቸው አያውቁም። ይህን ባለማወቃቸው ዛሬ በኦነጋውያን በየአካባቢው የሚደርሰውን ጥቃትና ተዳፍኖ የቆየው ከሀያ በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች በሞጋሳ የጠፉበት የገዳ ስርዓት የወለደውን ጦረኝነት ክፍል ሁለት ለመምራት ይዳዳቸዋል።

የገዳና የሞጋሳ ስርዓትን ማሞገስ ስድስት ሚልዮን አይሁዶችን ለጥፋት የዳረገውን የናዚ ስርዓት ከማሞገስ ተለይቶ አይታይም። የናዚዎቹን ስኬት ማሞገስ የሚፈልጉ የሉም ማለት አይደለም። በደንብ አሉ። ሆኖም ግን ታሪክ በትክክል በመነገሩ ጨካኝ የናዚ ስርዓት በዓለም ላይ እየተወገዘ እንዲኖርና ተመልሶ እንዳይመጣ ተደርጓል። በአገራችን ግን ታሪካችንን በደምብ ባለማወቃችን፣ የዘር ማጥፋትን የተካሄደበትና ከሀያ በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች የጠፉበትን ሞጋሳን እንደበረከት እንድናሞግስ እየተጠየቅን እንገኛለን። በርግጥ ኦነጋውያን ሰውን ገድሎ አጥፍቶ መኖር አክሳሪ እንዳልሆነ እስካመኑ ድረስ ወደ ቀድሞው የአባ ገዳ ባህላቸው ለመመለስ ማሰባቸው የሚስደንቅም አይደልም።

Filed in: Amharic