>
5:28 pm - Friday October 10, 0724

አክሊሉ ሃብተ ወልድ እ.ኤ.አ. በ1935 ዓ.ም. በተካሄደው በፈረንሳይ ምርጫ የሰሩት ታሪክ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

አክሊሉ ሃብተ ወልድ እ.ኤ.አ. በ1935 ዓ.ም. በተካሄደው በፈረንሳይ ምርጫ የሰሩት ታሪክ…!!!

አቻምየለህ ታም

*  እ.ኤ.አ. በ2020 ዓ.ም. አሜሪካን አገር በሚካሄደው ምርጫ ይህን ታሪክ የሚደግም ኢትዮጵያዊ  ይኖር ይሆን?
የኢትዮጵያ አገልጋዩ ታላቁ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ጸረ ኢትዮጵያ የነበረው የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር የሙሴ ላቫል መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1935 ዓ.ም. በተካሄደው የፈረንሳይ ምርጫ ተዘርሮ እንዲሸነፍና የኢትዮጵያን ነጻነት ይደግፍ የነበሩ የሙሴ ላቫል ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ እንዳደረጉ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ?!
አዎ ታላቁ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ኢትዮጵያ በፋሽስት ወረራ በተደፈረችበት በዚያ የመከረ ወቅት ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን እንዲወርር ያበለጠ ያበረታታ የነበረው የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንስትር የነበረው የሙሴ ላቫል መንግሥት በምርጫ እንዲሸነፍና በምትኩ የኢትዮጵያን ነጻነት የሚደግፉ የፈረንሳይ ተቃዋሚዎች እንዲያሸንፉ አድርገዋል።
ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ይህንን ያደረጉት የሙሴ ላቫል ተቃማዊዎች የምርጫ ቅስቀሳ በየሚያደርጉበት መድረኮች ሁሉ  እየተገኙ ሙሴ ላቫል ፈረንሳይ የፈረመችውን የሊግ ኦፍ ኔሽኑን “Collective Security” በመጣስ ሙሶሎኒን ኢትዮጵያን እንዲወር ከጣሊያን ጋር የተስማማበትን Mussolini-Laval Accord  እና ከእንግሊዝ ጋርም Hoare–Laval Pact  በሚል የተፈራረመውን ተመሳሳይ  ሚስጥራዊ ውል የፈረንሳይ ሕዝብ በዝርዝር እንዲያውቀው በማድረግና በፈረንሳይ በወቅቱ ይታተሙ በነበሩ ታዋቂ ጋዜጦች ላይ ሁሉ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ባሳተሟቸው ጠንካራ ጽሑፎች የፈረንሳይ መንግሥት ኢትዮጵያን አሳልፎ በመስጠት የፈጸመው ግፍ እንዲጋለጥ በማድረግ ነበር።
ይህ የአክሊሉ ሃብተ ወልድ የተሳካ ተጋድሎ ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያን ለሙሶሎኒ የሸጠው ሙሴ ላቫል የኢትዮጵያን ጉዳይ የያዘበት መንግድ  በፈረንሳውያን ዘንድ በመጠላቱና ከሙሶሎኒ ጋር ኢትዮጵያን አሳልፎ ለመስጠት የተፈራረመው የሚስጥር ስምምነት በመጋለጡ በተቃዋሚዎቹ እንዲሸነፍና ኢትዮጵያን የሚደግፍ ተቃዋሚ ፓርቲ መንግሥት እንዲሆን አስችሏል። የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሴ ላቫል የኢትዮጵያ ጉዳይ የያዘበት መንገድ እንዲሸነፍ እንዳደረገው የሙሴ ላቫልን የሕይዎት ታሪክ የጻፈው Hubert Cole እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም.   “Laval: A Biography of One of the Most Controversial Figures of World War II” በሚል ባሳተመው መጽሑፍ  ከገጽ 210–11 ባለው ነግሮናል።
አክሊሉ ሃብተ ወልድም ይንን በፈረንሳይ አገር ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ትግል፤ ኢትዮጵያን ለሚሶሎኒ የሸጠው የሙሴ ላቫል መንግሥት እንዲሸነፍና የኢትዮጵያ ነጻነት ደጋፊ  የሆነ ፓርቲ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ያካሄዱትን ተጋድሎ ፕሮፈሰር መስፍን ወልደ ማርያም በሰብሳቢነ ይመሩት ለነበረው መርማሪ ኮሚሽን ባቀረቡት ያሕይዎት ታሪካቸው ውስጥ ጽፈውታል። አክሊሉ በፈረንሳይ አገር ኢትዮጵያን የሚደግፍ መንግሥት እንዲመረጥ ያደረጉበትን ተጋድሎ ሙሉ ታሪክ ከታች ከታተሙት ገጾች መመልከት ይቻላል። ገጽቹ አክሊሉ ራሳቸው ከጻፉት ማስታወሻ የተወሰዱ ናቸው።
አሁን ጥያቄው በዚያ ዘመን የኖሩት አክሊሉ ሃብተ ወልድ  ኢትዮጵያን  ለሙሶሎኒ የሸጠው በሙሴ ላቫል የሚመራው የፈረንሳይ መንግሥት በምርጫ እንዲቀጣ እንዳዳረጉት  ሁሉ የዚህ ዘመን ሙሴ ላቫል የሆነው ዶናልድ ትራምፕ በኢትዮጵያ ላይ እያራመደው ባለው ድፍረት የተሞላበት እብሪት በምርጫ ዋጋ እንዲከፍል የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ  አለ ወይም የሚል ነው?!
በኔ እምነት የአክሊሉ የአገር ፍቅር ስሜት ያለውና የኢትዮጵያ መደፈር የእግር እሳት የሚሆንበት Ethiopian American ወይም የአሜሪካ ዜግነት ያለው  ትውልድ ኢትዮጵያዊ  እስካላ ድረስ   ልክ እንደ ሙሴ ላቫል በምርጫ ምጣድ ላይ ተጥዶ የሚገኘው ዶናልድ ትራምፕ የሙሴ ላቫይ አይነት ዋጋ እንዲከፍል ማድረግ ይቻላል።

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1928 ዓ.ም. የኮሎኔልነት ማዕረግ ሰጥተው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ አድርገው የሾሙትና   ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፎ ከፋሺስት ኢጣሊያ ጋር የተፋለመው ጥቁር አሜሪካዊው አብራሪ  ጆን ቻርልስ ሮቢንሰን የደሙላትንና መላው ጥቁር ሕዝብ  የነጻነት ተምሳሌት አድርገው የሚቆጥሯትን ኢትዮጵያን ግብጽ በቦንብ እንድታጋያት ፍቃድ ወይም ይሁንታ መስጠቱን በተለይ ጥቁር አሜሪካኖች እንዲያውቁ  በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ የሙሴ ላቫል አይነት አቋም እያራመደ የሚገኘው ዶናልድ ትራምፕ  ዋጋ እንዲከፍል ማድረግ ይቻላል። የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑትን እነ ጀሲ ጃክሰን፣ ጥቁር አሜሪካዊ ዝነኛ የፊልም ተዋናይ የሆኑት እነ ዊል ስሚዝን፣ አቀንቃኝ የሆኑት እነ ሪሐናንና የታዋቂ  ሾው ሆስት የሚያደርጉትን እነ ኦፕራ ዊንፍሬይን በመጠቀም ዶናልድ ትራምፕ ግብጽ ኢትዮጵያን በቦንድ እንድትደበድብ ይሁንታ መስጠቱን ጥቁር አሜሪካውያን እንዲያውቁና በሚመርጡበት ወቅት ለዶናልድ ትራምፕ ድምጽ ባለመስጠት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል።
እንግዲህ! ይህ ወቅት በተለይ የአሜሪካ ዜግነት ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ተነሳሽነቱን በመውሰድ ኢትዮጵያ በቦንብ እንድትደበደብ ይሁንታ የሰጠው ዶናልድ ትራምፕ ዋጋ እንዲከፍል በማድረግ  የማኅበረሰብ አለኝታነታችሁን በተግባር የምታሳዩበት ወቅት ነው። አንዱ አክሊሉ በዚያ ጨለማ ዘመን በጭንቅ ውስጥ ሆነው በፈረንሳይ አገር ማድረግ የቻሉትን በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ  በነጻነት በሚኖርበት አሜሪካን አገር ውስጥ አክሊሉ የተከተሉትን መንገድ ተከትሎ ኢትዮጵያ በቦንድ እንድትደበደብ ይሁንታ የሰጠውን እብድ ሰውየ ዋጋ እንዲከፍል ማድረግ አይሳነውም።
ከቻት የታተሙት ገጾች ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሊ በፈረንሳይ አገር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ በሙሲሎኒ እንድትወረር ያደረገውን የሙሴ ላቫል መንግሥት በምርጫ እንዲሸነፍና የኢትዮጵያን ነጻነት የሚደግፉ የፈረንሳይ ተቃዋሚዎች ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ያደረጉበትን ተጋድሎ የሚያሳዩ ዶሴዎች ናቸው። ገጾቹ የተወሰዱት ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ራሳቸው ከጻፉትና ለመርማሪ ኮሚሽን ካቀረቡት ማስታወሻቸው የተወሰዱ ናቸው።
Filed in: Amharic