>
5:13 pm - Monday April 18, 1768

ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ! (ከይኄይስ እውነቱ)

ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ!

ከይኄይስ እውነቱ


ዛሬ በኢትዮጵያ የዜጎች የሕይወት፣ የአካልና የንብረት ሰብአዊ መብቶች በዘፈቀደ የሚነጠቁበት፤ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማፈን በዚሁ ምክንያት ዜጎች በፈጠራ ክስ፣ በፈጠራ ምስክር እና በፌዝ ፍርድ ቤት ወኅኒ ቤት የሚንገላቱበት መንግሥት አልባ በሆነ ሽብርተኛ የአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ እንገኛለን፡፡ 

የወያኔ ሕወሓት ወራሽ የሆነውና ለሁለት ዓመት ተኩል ገደማ አገራችንን ምድራዊ ሲዖል ያደረገው የዐቢይ አገዛዝ የሚመራው የጐሣ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ አባል ድርጅቶችና አብዛኛው ግለሰቦች ቀድሞ ‹ፈጣሪያቸውን› በባርነት ሲያገልግሉና የወንጀል ዓይነቶችን በሙሉ ንቅስ አድርገው ሲፈጸሙ የቆዩ፣ ተሐድሶ ያልነካቸው (ይልቁንም ለአገር ያላቸውን የመረረ ጥላቻና ንቀት፣ ለወገን ያላቸውን ጭካኔ በእጥፍ ድርብ ያደሱ)፣ በበደላቸው ያልተጸጸቱ፣ ፍርድ ሳይቀበሉ እስከነ ብልየታቸው የሚገኙ፣ ከወያኔ የተማሩትንና የቀረውን አገር የመበተን፣ ሥር የሰደደ ንቅዘት፣ እስከ የሌለው ዘረኝነት፣ መፈጠርን የሚያስጠላ ግድያ፣ ቅጥ ያጣ የመሬት ወረራና የዜጎች ማፈናቀልን በታሪካችን ተወዳዳሪ በሌለው ሁናቴ በ‹ሕግ›፣ በመዋቅር እና በሽብር ኃይል ደግፈው እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ 

እየተፈጸመ ያለው ግፍና በአገር ህልውና ላይ የደቀነው ሥጋት መጠን ትናንትን ከዛሬ የተሻለ ነው እስኪያስብል የራሳቸውን የጥፋት ሬከርድ ለመስበር እየተሽቀዳደሙ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ዓላማቸው አረመኔያዊና ኋላ ቀር የሆነውን፣ በርካታ ነባር የኢትዮጵያ ነገዶች የጠፉበትን፣ ማንነታቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያጡና ባሪያ እንዲሆኑ የተደረጉበትን ገዳ የተባለ የግድያና የወረራ ‹ሥርዓት› ‹መደመር› በሚል ስም አሽሞንሙነውት ዕለት ዕለት በመደበኛነት እየተገበሩት ይገኛሉ – ኦሕዴድ እስከነ ባሮቹ፣ ኦነግ እስከነ ፍንክትካቹ፣ የበቀለ ገርባ ኦፌኮ እስከነ ጀዋራውያን ግብረ አበሮቹ፡፡ ባጠቃላይ ሌሎች የጐሣ ፖለቲካ ድርጅቶችም በጥፋቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አገራችን ለገባችበት ምስቅልቅል መሠረታዊ ችግሮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የጐሣ ፖለቲካው፣ ‹ክልል› የተባለው ‹ጋጣ› መገለጫው የሆነው የውሸት የጐሣ ፌዴራሊዝም እና ለእነዚህ ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ የሰጠው የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ናቸውና፡፡

በሕዝብ ላይ አገዛዛቸውን ከሚያጸኑ ከእነዚህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለሙ ጭምር ማፈሪያ ከሆኑ ገዢዎች ጋር ባንድነት የቆማችሁ፣ ለጥፋት ተልእኳቸው መሣሪያ የሆናችሁና የምትረዱ በሙሉ የምትሰሙ ከሆነ በሕግ፣ በሞራል እና በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አታመልጡምና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የምታደርጉበት ጊዜ ዘገየ ከሚባል በቀር አሁን ነው፡፡

የአገራችንን ዳር ድንበር ከጠላትና ወራሪ ለመከላከል፣ የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበር፣ የአገርና የሕዝብ ደኅነነት ተግባር ለመፈጸም ጀግኖች አያቶቻችንና አባቶቻቸችን ደማቸውን ያፈሰሱለትን፣ አጥንታቸውን የከሰከሱለትን፣ የሺህ ዘመን የነፃነት ብሔራዊ ምልክታችን በሆነው ሰንደቅ ዓላማ ቃል ኪዳን የገባችሁ የጦር ሠራዊትና የፀጥታ ሠራተኞች በሙሉ  ለአገዛዙ መሣሪያ በመሆን አንዳንዶች ሕዝባችሁን እየፈጃችሁ፣ ሌሎቻችሁ ደግሞ በሽብርተኞች ሲጠቃ እንዳላየ በዝምታ እያለፋችሁ ጐሣን መሠረት ያደረገ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አሳይታችኋልና ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

በአገርና በሕዝብ ሀብት ተምራችሁ ለዕውቀትና ለእውነት በመቆም ለሕዝባችሁ አለኝታ በመሆን ፈንታ ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ በማለት ከጨለማ ኃይሎች ጋራ የአድርባይነት ኅብረት የፈጠራችሁ በስም ‹ምሁራን› የተባላችሁ ወገኖች በሙሉ የአገዛዝን ዕድሜ በማራዘም የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ሆናችኋልና ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

እውነትን በመሸፈን ሐሰት ባገር ላይ እንዲሠለጥን በማድረግና ለተተኪም ትውልድ መጥፎ አርዓያ በመሆን በሕዝብ ላይ በሚፈጸም ግፍና በደል የምትሳለቁ የመንግሥትና የግል ብዙኀን መገናኛዎች እንዲሁም በየትኛውም መንገድ ሐሰተኛ ወሬና መረጃ የምታቀብሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

የፖለቲካ ማኅበርን የገቢ ምንጭና መተዳደሪያ እንዲሁም የትርፍ ጊዜ ሥራ ያደረጋችሁ፤ ተረኛ ግፈኞች ከኢትዮጵያ ሕዝብ በሰረቁት ሀብት ድርጎ (ሹመት፣ ቤት፣ መኪና ወዘተ.) እየተቀበላችሁ በሕዝብ ስም የምትነግዱ የአገዛዙ አጃቢዎች፤ በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅትነት ተመዝግባችሁ የተቃውሞ ፖለቲካን ጠባይና አቋም የማታሳዩ፣ እውነተኛ ተቃዋሚዎችን ለአገዛዙ አሳልፋችሁ የምትሰጡ፣ ለአገዛዙ ምንጣፍ አነጣፊና መጋረጃ ጋራጅ የሆናችሁ፣ ከአገዛዙ ባልተናነሰ ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ እየከተታችሁ ያላችሁ በሙሉ ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

የባህል የእምነት መሠረት ይዞ ለረጅም ዘመናት የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነውን እና በትውፊት፣ በልማድ በአሠራር ተግባራዊ ሆኖ የቈየውን – በሕግ አምላክ – የሚለውን የሕግ የበላይነትና ልዕልና ሃሳብ በመፃረር፣ ፍትሕን የአገዛዞች ደንገጡር፣ ዳኝነትን የፌዝ መድረክ በማድረግ ፍርድ እያጓደላችሁና ሕዝብ በፍርድ ቤቶች እምነት እንዲያጣ እያደረጋችሁ ያላችሁ ‹ዳኞች› ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ አጥቶ ድህነት በሚጫወትበት ሕዝብ ላይ በአባይ (ላልቶ የሚነበብ) ሚዛን የምታታልሉ፣ ከእህልና ምግብ ውጤቶች ጋር ለጤና ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን በመደባለቅ የምትሸጡ፣ ከተገቢው በላይ ትርፍ የምታጋብሱ፣ በሸቀጦች አቅርቦት ላይ ሸፍጥ የምትሠሩ አጭበርባሪ ነጋዴዎች በሙሉ ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

ሆን ብላችሁ በኤሌክትሪክ ኃይልና በውኃ አቅርቦት እንዲሁም ሌሎች ለሕዝብ በሚቀርቡ አገልግሎቶች ሕዝብን የምታማርሩ ግልገል ባለሥልጣናት  እና ተራ ሠራተኞች የሕዝብ እምባ ከንቱ አይቀርምና ወዮላችሁ ወዮታ አለባችሁ እግዚአብሔር ለተገፉት ሊፈርድ ተቃርቧልና ሰልፋችሁን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አድርጉ፤

ሃሳቤን ለመቋጨት በኢትዮጵያ ነገዶች/ጐሣዎች እኩልነት የማያምኑ ተረኞች የኢትዮጵያ ሀገራዊ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ፣ ወገናችሁ በማንነቱና በሚከተለው እምነት ምክንያት የሚደርስበት ጭፍጨፋ÷ መፈናቀልና እንግልት፣ የብሔራዊ ተቋማት÷ ምልክቶችና ቅርሶች በተረኞች ጭፍን ጥላቻ መውደም፣ ቅጥ ያጣው የአገራዊ ሀብት ዘረፋ የሚያሳስበሳችሁ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ የፖለቲካ ማኅበራት፣ በአገዛዙ ያልተጠለፋችሁ የማኅበረሰብ ተቋማት፣ እውነተኛ ምሁራንና እውነተኛ ቀስቃሾች (አክቲቪስቶች) በቅርቡ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተሰባሰቡትን የፖለቲካ ማኅበራት ጅምር እንቅስቃሴ በመቀላቀልና ዓላማውንም ከፍ በማድረግ ሳይውል ሳያድር ሕዝቡን ሁለንተናዊ ለሆነ ሰላማዊ ትግል ለማደራጀት ኅብረት እንድትመሠርቱ ጥሪዬን አደርጋለሁ፡፡ ያልተደራጀ የሕዝብ ዓመፃ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት እንዳስተዋልነው ለጮሌዎች ሲሳይ መሆኑን በመገንዘብ እናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ በዜግነቱ የአገር ባለቤት ባለመብት እንዲሆን የምትታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ትርጕም አልባ ለሆነ ምርጫ አጃቢ ከመሆን ይልቅ ሳይዘገይ በእናንተ ፊታውራሪነት እላይ የጠቀስኋቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማስተባበር ሰላማዊ ትግሉ ባስቸኳይ እንዲጀመር አድርጉ፡፡ የሰላማዊ ትግሎችን ዓይነቶችና አፈጻጸማቸውን ለሕዝቡ አንቁ አስተምሩ፡፡ ከተረኞቹና ግብረ አበሮቻቸው እንዲሁም ከወያኔ በስተቀር ሁላችንም ከጎናችሁ መሆናችንን አትጠራጠሩ፡፡ የሥልጣን ፖለቲካውን የአገር ህልውናና የሕዝብ ደኅንነት ከተረጋገጠ በኋላ ትደርሱበታላችሁ፡፡

አንድ ዘረኛ ቡድን በሕዝብ ሀብት የመከላከያና ፀጥታ ተቋማትን፣ የሕዝብ መገናኛን ብዙኀንን፣ የፍትሕ ተቋማትን፣ ቢሮክራሲውን፣ ኢኮኖሚውን፣ ጥቂት የማይባሉ የማኅበረሰብ ተቋማትን ወዘተ. በተቆጣጠረበት ስለ ምርጫ በተለይም ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ ጨርሶ ማሰብ አይቻልም፡፡ ርግጡን ለመናገር ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁለንተናዊ ቀውስ በምርጫ የሚፈታ አለመሆኑን ተገንዝባችሁ፣ ስትራቴጂካዊ ኅብረት የምታደርጉበት ወሳኝ ጊዜ ላይ የምትገኙ መሆኑን እንደ አንድ የአገሩ ጉዳይ የሚያንገበግበው ዜጋ በማክበር አሳስባችኋለሁ፡፡

ለዚህ በጎ ዓላማ የምትሰባሰቡትን በሙሉ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳችሁ፡፡

Filed in: Amharic