>

የድጋፍ ሰልፍ ብቻ እየፈቀዱ፤ ተቃውሞን እያፈኑ የሚኖርበት ዘመን ያለፈበትና ያከተመ መስሎን ነበር?!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የድጋፍ ሰልፍ ብቻ እየፈቀዱ፤ ተቃውሞን እያፈኑ የሚኖርበት ዘመን ያለፈበትና ያከተመ መስሎን ነበር?!?

ያሬድ ሀይለማርያም

* የሰላም በሮች በተከረቸሙ. ቁጥር የአመጽ በሮች ወለል ብለው እንደሚከፈቱ የዛሬዎቹ አፋኞች የመጡበትን መንገድ ዘወር ብሎ መመልከቱ ብልህነት ይመስለኛል….!!!

አብን የጠራውን የሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ሕገ ወጥም፣ በህገ መንግሥቱ እና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የፈረመቻቸው ስምምነቶች ላይ የተቀመጡትን የዜጎችን የመሰብሰብ እና በአደባባይ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ መብቶች የሚጥሱ ናቸው። አገሪቱ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውስጥ እንዳልሆነች እየታወቀ እና ከቀናቶች በፊት መንግስትን የሚደግፉ ተከታታይ ሰልፎች ያለ ምንም ችግር መካሄዳቸው እየታወቀ ድርጅቱ የጠራውን የሰላማው ሰልፍ እንዳይካሄድ መከልከልም ሆነ ዛሬ ደግሞ አመራሮቹ ከጽ/ቤታቸው እንዳይወጡና ጋዜጣዊ መግለጫም እንዳይሰጡ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መከበባቸው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው የአፈና እርምጃ ነው። መንግስት የኖርንባቸውን እና አገሪቱን ወደ ግጭት የዳረጉ የህውሃት ስህተቶችን እና የአፈና ስልት ባይከተል መልካም ነው። አፈና አመጽን ሊወልድ ይችላል። አመጽ ደግሞ አጥፊ ነው። ወደዛ አቅጣጫ ማህበረሰቡን መግፋት ለአገዛዝ ሥርዓቱም ሆነ ለማንም አይበጅም። የመጣንበትን ክፉ መንገድ ባንመለስበት ጥሩ ነው። የዜጎች ሃሳባቸውን በአደባባይ የመግለጽ፣ መንግስትን የመቃወም እና የመሰባሰብ መብት ሊከበር ይገባል። የድጋፍ ሰልፍ ብቻ እየፈቀዱ፤ ተቃውሞን እያፈኑ የሚኖርበት ዘመን ያለፈና ያከተመ መስሎን ነበር። መሰረታዊ የሆኑ መብቶችን እና ነጻነቶችን አፍኖ ወደ ምርጫስ መሄድ እንዴት ይቻላል?

Filed in: Amharic