>
5:28 pm - Thursday October 10, 5680

የአኖሌ እጅና ጡት ቆረጣ ትርክት፡- ተረቱና እውነቱ...!!! (እውነት ሚድያ አገልግሎት)

የአኖሌ እጅና ጡት ቆረጣ ትርክት፡- ተረቱና እውነቱ…!!!

እውነት ሚድያ አገልግሎት

✍️ በአኖሌ ጉዳይ የታሪክ ምሁራንን ጭምር የማያስማማው ቁልፍ ነጥብ የታሪኩ ምንጭ ጉዳይ ነው፤ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› መጽሐፍ ልበወለድ በመሆኑ እና ኤርትራዊው የመጽሐፉ ጸሐፊ ተስፋየ ገብረ አብም ኦሮሞንና አማራን የማናከስ ተልእኮ ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደቆየ ታውቋልና! የአርሲው ተወላጅና አክራሪው ሙስሊም አባስ ሐጂም ታሪክን ከመመዝገብ ይልቅ ወደ መንደሩና ሃይማኖቱ ባደላ መልኩ ያልነበሩ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ምሁራዊ አስመስሏል!
✍️ ክስተቱ የተፈጸመው ዐጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ወቅት፣ በእርሳቸው እውቅናና ይሁንታ (ፈቃድ ሰጪነት) ነበር፤ ምኒልክ በዐጼው ሥር የሸዋ ንጉሥ ብቻ ነበሩና!
✍️ የአካል ክፍሎችን በመቁረጥ መቅጣት በዐጼ ቴዎድሮስና በዐጼ ዮሐንስ ዘመናትም የተለመደ ስለነበር ዐጼ  ምኒልክ የእነርሱን ‹‹የመቁረጥ ሌጋሲ አስቀጥለዋል›› ካልተባለ በቀር ‹‹ጀማሪው እርሳቸው ናቸው›› የሚያስብል የታሪክ መሠረት የለም!
✍️ አኖሌን ጨምሮ የቀደሙት ግጭቶች መንሥኤ ፈጽሞ አንዱ ብሔር ሌላውን ለመጉዳትም ያደረገው፣ ይልቁንም ‹‹አማራ ኦሮሞን ያጠቃበት›› የሚባል አይደለም፤ የጥንቱን በአሁኑ የአስተሳሰብና የፖለቲካ ቅኝት እየመዘኑ ትውልድን ማሳሳትም ትክክል አይደለም!
✍️ በአዙሌ እንጂ በአኖሌ የተካሄደ ጦርነት አልነበረም፤ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ አንድ ዓመት በኋላም አዘናግቶና ‹‹እንታረቅ›› ብሎ ጠርቶ ማጥቃት፣ ይልቁንም ሴትንና ቄስን ማጥቃት ከነባሩ የኢትዮጵያውያን ጦረኞች ባህል ጋር አይገጣጠምም!
✍️ ለተቆረጠው አካል ሁሉ፣ በተቆረጠበት ቦታ ሁሉ ሐውልት እንሥራ ብንል ምድሪቱ ራሱ ላትበቃ ትችላለች፤ ያልተቆረጠ አካል፣ ያልፈረጠ ዓይንና ያልተፈለጠ አጥንት አልነበረምና፡፡ ለተከሰቱት ግፎች ሁሉ ሐውልት አንተክልም ማለት ግን እውቅና ሰጥተናል፣ ግፉን ደግፈናል ማለት አይደለም!
✍️ እንኳንስ በዚያን ወቅት ቀርቶ ‹‹ሰልጥነናል፣ ዘምነናል›› ብለን በምንኩራራበት በዛሬው ዘመናችን እንኳን ከነገሥታቱ ጭካኔ የባሱ አሳፋሪ ድርጊቶችን እየፈጸምን ስለሆነ ነገሥታቱ ‹‹ብልት ቆርጠዋል›› ብለን የምንወቅስበት የሞራል ልዕልና የለንም!
✍️ እናም ወደኋላ እየቆዘምን ‹‹የቆረጣና ቆራጣ ታሪክ›› አንፈልግ፤ ዛሬም ትውልዱ የባሰውን ግፍ በክርስቲያኖች ደም ቀለምነት፣ በኦሮምያ ምድር ወረቀትነት አኖሌን በተግባር እየተረከልን ነውና!!!
“““`
በአዲሱ ፖለቲካዊ ታሪክ ትርክት መሠረት የኦሮሞ ሕዝብ ምኒልክ በሚመራው የአማራ ጦር አማካይነት እጅና ጡቱን ተቆርጧል፡፡ ይህንን ትርክት በተለይ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲካ አራማጆችና በምርምራዊ ጥናት ስም በርካታ ጽሑፎችን በመጻፍ እያሳተሙ የዓለሙን ማሕቀፈ እሳቤ የቀየሩት ‹‹ምሁራን›› ይገኙበታል፡፡ እናም የተለያዩ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥ ስለ አኖሌ ሐውልት ተጨባጭ እውነታዎችን እንፈትሽ፡-
1. የምንጭ ጉዳይ
——————–
ሁሉንም ዜጎች ከማያስማሙ ያለፉት የኢትዮጵያ ታሪኮች፣ ይልቁንም  ‹‹ተከስተዋል›› ተብለው በጥቂት ቡድኖች ከሚታመኑ ነገር ግን ትክክለኛ የታሪክ ምንጫቸው ከሚያከራክር ትርክቶች ውስጥ የአኖሌ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲካን ተከትለው ከሚነጉዱት ጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ የታሪክ ምሁራን በአኖሌ ተፈጽሟል ተብሎ ስለሚወራው የእጅና ጡት ቆረጣ ትርክት አይስማሙም፤ ማስረጃ ይምጣልን ብለውም ይሞግታሉ፡፡
በእርግጥ ሦስት መሠረታዊ እውነቶችን ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ፡- አንድ ኃላፊ ክስተት በታሪክ ድርሳናት ላይ ‹‹አልተጻፈም›› ማለት ‹‹ፈጽሞ አልተፈጸመም›› ማለት አለመሆኑን፤ ሁለተኛ፡- ባሳለፍናቸው የሀገራችን ሕዝቦችና አስተዳደራዊ ሥርዓት ሂደት እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ያሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች ታሪክ በጥራትም ሆነ በብዛት ተጽፈው አለመቀመጣቸው፤ ሦስተኛ፡- ይጻፉ የነበሩ ታሪኮችም በአብዛኛው በነገሥታቱ ተጽዕኖ ሥር ባሉት ጸሐፌ ትእዛዛት አማካይነት በመሆናቸው መሪዎቹን የሚያስነቅፉ ተግባራት ነጥረው የሚወጡባቸው ሁኔታዎች አናሳ መሆናቸው፡፡ እናም የአኖሌው ጉዳይም ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ ደርሶት ባለመጻፉ ላልተገባ ክርክርና ተቃውሞ ተዳርጎ እንዳይሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማየቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ያልነበረን ክስተት አጋንኖ በመጻፍ ለዘውግ ፖለቲካ ማራገቢያ መጠቀም፣ ሕዝብንም ከሕዝብ ማጋጨት ጸያፍ ነው፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ ስለ አኖሌ ታሪክ በምንጭነት የሚጠቀሱት ድርሳናት ሁለት ናቸው፡- የተስፋዬ ገ/አብ ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› ልብወለድ እና የአባስ ሐጂ ቃላዊ መጣጥፎች፡፡
1.1. ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› 
—————————
የዚህን ምንጭ ምንነት በአግባቡ ለመፈተሽ ሁለት መሠረታዊ እውነታዎችን መፈተሽ ይኖርብናል፡- የጸሐፊውን ተስፋዬ ገ/አብ ማንነት እና የመጽሐፉን ምንነት፡፡
ተስፋዬ ገብረ አብ በትውልድ ኤርትራዊ ነው፡፡ በፖለቲካ አሰላለፍ ደግሞ ሲታይ ሻዕቢያና ሕወሓት ተመሳሳይ አቋም ላይ በነበሩበት ወቅት እነዚህ ሁለቱ ሌሎች ሕዝቦችን በምን መልኩ በዘር ከፋፍለው መግዛት እንደሚችሉ የሚያመላክቱ ስልታዊ አካሄዶች ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ በዋናነትም ሁለቱን ታላላቅ የኢትዮጵያ ሕዝቦች (ኦሮሞንና አማራን) በማናከስ ሂደት ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የነበረ ግለሰብ ነው፡፡ ከታች የምንመለከተው ‹‹የቡርቃ ዝምታ›› መጽሐፍም የዚሁ ፕሮፖጋንዳ አካል ነበር፡፡ ለእነ ሕወሓት የነበረውን ግልጽ ድጋፍ ደግሞ ‹‹ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ›› በተባለው መጽሐፉ በይፋ ማወጁ ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ በነበሩ ልብ ወለዶቹም ዘር-ተኮር የጥላቻ ፖለቲካዎችን ከመዝራት ሌት ተቀን ተግቶ የሚሠራ ከመሆኑም በላይ ይኸና መሰል ዋዣቂ አካሄዶቹ ሲነቁበት ከሀገር ወጥቶ በስደት ሀገር ኑሮውን ለመግፋት የተገደደ ግለሰብ ነው፡፡
‹‹የቡርቃ ዝምታ›› መጽሐፍ ደግሞ ለታሪክ ጉዳዮች በምንጭነት የማይጠቀስ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ልቦለድ መሆኑ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ‹‹ልበ ወለድ›› የተባለበት ዋናው ምክንያትም እውነታነት የሌለው፣ በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጥ የማይችል ስለሆነ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱ ያሰበውንና እንዲሆን የሚፈልገውን ነገር ከልቡ አንቅቶ እየጻፈ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ለማስቀመጥ የሚያደርገው ጥረት እስከሆነ ድረስ ተስፋዬ ገብረ አብም መጽሐፉን ተጠቅሞ ያደረገው ይኸንኑ ነው፤ ምንም እንኳን እውነትን በልቦለድ ቀብሮ ለማስቀረት ባይቻልም ለጊዜው የተሳካለትም ይመስላል፡፡
ከአኖሌው ትርክት ጋር በተገናኘ ተስፋዬ ገ/አብ ‹‹ቡርቃ›› በሚላት ወንዝ አጠገብ የተከሰተ እውነተኛ ግጭት በታሪክ ውስጥ የለም፤ በአርሲው ዘመቻም የተዋጉት ‹‹አማራና ኦሮሞ›› የሚባሉ ሕዝቦች ሣይሆኑ ዘውዳዊው አስገባሪ ኃይልና ገባሪ የአስተዳደር ሥርዓቶች ናቸው፡፡ የደራሲው ዓላማ ግን ፖለቲካዊ ሤራ ነውና ግጭቱን ‹‹የብሔር›› መልክ ሰጥቶ ለማራገብ ሞከረ፡፡ ሌላው እውነታ ደግሞ አኖሌ የጦርነቱ ቦታ አልነበረም፤ ጠርዘኛ ፖለቲከኞቹ እንኳን አኖሌ ‹‹እጅና ጡት የተቆረጠበት ቦታ ናት›› ይበሉ እንጂ በአኖሌ አንዳች ጦርነት እንዳልተካሄደ አልካዱም፡፡ ግጭት የተካሄደባቸው ቦታዎች አርባ ጉጉ፣ በደኖ እና ከፍተኛውና የማገባደጃው ውጊያ የተካሄደባት አዙሌ የመሳሰሉት ነበሩ፡፡
1.2. የዘመናችን ፖለቲካ ተደጋጋሚ ተረኮች 
———————————————
በተለይ ከዘመነ ሕወሓት ጀምሮ ያለው የሀገራችን ፖለቲካ ብሔር-ተኮር (ሕዝቦችን በመከፋፈል ላይ የተመሠረተ) መሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚያሳዝነው ሌሎችም ቢሆኑ ይህንን የከፋፍለህ ግዛ ስትራቴጂና መሰል ልቦለዶችን እንደወረደ ተቀብለው ከማስተጋባት ያለፈ የታሪክ ማስረጃ ላይ መመርኮዝ አለመፈለጋቸው ነው፡፡ በዚሁ የ2012 ዓ.ም እንኳን ጀዋር መሐመድ ‹‹ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የምኒልክን ቤተ መንግሥት የሚያሳድስ ከሆነ የአኖሌ ሀውልትም ቤተ መንግሥቱ ውስጥ መቆም አለበት›› ብሎ መከራከሩ አይረሳም፡፡
 
1.3. የአባስ ሐጂ ገነሞ ጽሑፎች
———————————————
እስካሁን ድረስ ‹‹ተደርጓል›› የሚለውን ድምዳሜ እንደ እምነት ወስደው ብቻ ከሚያቀነቅኑት ባሻገር አንዳች ታሪካዊ ማስረጃ አገኘሁ ካሉት ውስጥ በቅርቡ አባስ ሐጂ ገነሞ በአንድ ሚዲያ ላይ ሲናገሩ፡- ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ የጻፍኩት እኔ ስሆን መረጃውን ያገኘሁትም ከአከባቢው ሽማግሌዎች ነው›› ብለው ነበር፡፡ አባስ ሐጂ ገነሞ The History of Arsi (1880-1935) በሚል የመጀመርያ ዲግሪ ማሟያ ወረቀት ጽፈው (እ.ኤ.አ. 1982) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንደተመረቁበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፤ በኋላም ይህንኑ ይዘትና ርእስ ‹‹ዓለም አቀፋዊ›› ጆርናሎች ላይ Les Oromo-Arsi, pp. 154–191. አሳትመው የትርክቱን አድማስ ከእውነታው ይልቅ አስፋፉት፡፡ በኋላ ደግሞ Abbas H. Gnamo, Conquest and Resistance in the Ethiopian Empire, 1880-1974 – The Case of the Arsi Oromo በሚል ርእስ (እ.ኤ.አ 2014) መጽሐፍ ጽፈው አሳተሙ፡፡ በእነዚህ ድርሳናት ሁሉ ‹‹የአርሲ ኦሮሞ ጭፍጨፋ›› ለሚለው ጩኸታቸው ‹‹ከአከባቢው ሽማግሌዎች የሰማሁት›› ከማለት ያለፈ አንዳችም ምሁራዊ ምንጭና የታሪክ ድርሳን አልጠቀሱም፤ በዚሁ መልኩ ከሰፈራቸው ሰው የተሰማው ወሬ በፕሮፌሴር ማዕረግ ታዝሎ ለዓለም አቀፍ መድረክ ሊበቃ ቻለ፡፡ ጊዜና  ፖለቲካም ተመቸውና እንደ ክረምት ሙጃ ከመጠን በላይ ተንዥርግጎ ዓለም አቀፋዊ መነጋገርያ፣ የሕዝቡም መነካከሻ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ እነሆ አንድ ሰው ብድግ ብሎ በጻፈው የቃላዊ ምንጭ ትርክት ምክንያት ሀገር ስትታወክ ትኖራለች፡፡
ከመጽሐፋቸው ርእስ ጀምሮ ክስ የሚስተዋልበትና የራሳቸውን ሚዛናዊ ምልከታ ለመጠቆም በማሰብ ‹‹የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች›› በሚል ርእስ ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ያበረከቱልን ታቦር ዋሚ (2006፡488-489) እንኳን ስለ አኖሌው እጅና ጡት ቆረጣ ትርክት አስመልክቶ በዋና ምንጭነት የተጠቀሙት ይኸንኑ የአባስ ሐጂን ድርሰት ነው፡፡ አባስ ሐጂ በወቅቱ ካልነበሩት አንድ ሽማግሌ ተረት ሰምቶ ‹‹ምሁራዊ መጽሐፍ›› ከማድረጋቸው በፊት በየትኞቹ የታሪክ ምሁራን ተጽፎ እንደነበር ግን አንዳችም አልተነፈሱልንም!
አባስ ሐጂስ ለምን ይህንን ትርክት ማቀንቀን ፈለጉ? ከተባለ ደግሞ ‹‹የጸሐፊው ማንነት በታሪክ ሚዛናዊነት ላይ ያለው ተጽዕኖ›› በሚለው የታሪክ አጠናን ማንጸርያችን (Historiography) መርሕ መሠረት ሃይማኖቱን ለመመርመር እንገደዳለን፡፡ አባስ ሐጂ የአርሲ ሙስሊም ናቸው፤ የሚታወቁትም በስማቸው ብቻ ሣይሆን የእስልምናውን የበላይነት የሚያቀነቅኑ ‹‹የጥናት›› ወረቀቶችን በዓለም አቀፋዊ ጆርናሎች ላይ በማሳተም ጭምር ነው፡፡
የአኖሌው እጅና ጡት ቆረጣ ትርክት ደግሞ በአርሲ (ሙስሊም በዝ በሆነ አከባቢ) የተካሄደ ጭፍጨፋ ተደርጎ ስለሚነገር የትውልድ ቦታውም፣ ሃይማኖቱም ‹‹ይመለከተኛል›› ባይ ናቸው፡፡ ጭፍጨፋውን ያካሄደውም ምኒልክ (አማራና ኦርቶዶክሳዊ) ነው ተብሎ መታመኑ ደግሞ የሕወሓት መሪዎችን፣ እንደ ተስፋዬ ገ/አብ ያሉ የፖለቲካ ምልምሎችን፣ ሙስሊሞቹንና የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ያስተሳሰረ የጋራ ጥቅም ሆነ፤ እናም ተባብረው ለዓለም አስተጋቡት፡፡ ይልቁንም ሁለቱ አካላት ለአማራ ገዢዎች ካላቸው ጥላቻ ጋር ተዳምሮ የጋራ ቃልኪዳን ቀለበት እንዲያስሩ ያበቃቸው ይኸው ትርክት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
በአጠቃላይ የዚህ ትርክት ትክክለኛ ምንጭ እስካሁንም ድረስ የታሪክ ምሁራኑን እንዳጨቃጨቀ ነው፡- ‹‹በእውነትም ተደርጓል›› እና ‹‹ፍጹም ተረት ነው›› በሚሉ ሁለት ተቃራኒ ጎራዎች፡፡ ምንም እንኳን ሁለቱም አካላት ‹‹ምንጭ አምጣ›› መባባላቸው የተለመደ ቢሆንም በተፈጥሯዊው አካሄድ ግን ምንጩን ማምጣት ያለበት ‹‹ተደርጓል›› ባዩ እንጂ ታሪካዊ ምንጭ በመጥፋቱ ምክንያት ‹‹ተረት ነው›› ያለው አይደለም፤ አልነበረም፣ አልተደረገም የሚል ቡድን ምንጭ ሊጠየቅ አይገደድምና!
2. የዘመቻው ኩነት በማን ዘመን፣ በእነማን ተፈጸመ?
—————————————————-
በርካቶች ስለ አኖሌ ትርክት በሰሙና ባነበቡ ቁጥር ትዝ የሚላቸው የዐጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ቢሆንም እውነታው ግን እንደርሱ አይደለም፡፡ ክስተቱ የተፈጸመው ዐጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ወቅት፣ በእርሳቸው እውቅናና ይሁንታ (ፈቃድ ሰጪነት) መሆኑ መታወቅ አለበት፤ ምኒልክ በዐጼው ሥር የሸዋ ንጉሥ ብቻ ነበሩና (ተክለ ኢየሱስ፤ 2008፡263)፡፡
የዐጼ ምኒልክ ትኩረትም ቢሆን በዐጼ ቴዎድሮስ የተደከመበትን፣ በዐጼ ዮሐንስ የተጣረበትን የኢትዮጵያ አንድነት የማጠናከር ዓላማ በቀር ሌላ ዓላማ አልነበረውም (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1983፡18)፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ጥሩም፣ መጥፎች ገጠመኞች መኖራቸው አይቀሬ ነው፡፡ አንድ የማድረግ ሂደቱ ወደ ግጭት እስካመራ ድረስ (አስገባሪና ገባሪ በስምምነት ካልፈጸሙት በቀር) የኃይል ሚዛኑ ከፍ ባለው አካል ጥቃት መፈጸሙም የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ ድርጊቶቹ መገምገም ያለባቸው በሌላ ዐውድ፣ በወቅታዊ የፖለቲካ አንድምታና ትንታኔ ተመዝነው ሣይሆን በወቅቱ በነበረው መክብብ ብቻ ነው፡፡
መረሳት የሌለበት ሌላው ነጥብ ወደ ዛሬዎቹ የኦሮምያና ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተደረጉት መስፋፋቶች (ማስገበሮች) የተሠማራው ምኒልክ ብቻ ሣይሆን የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጭምርም ነበሩ፡- ‹‹የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የጦር አርበኛ ጀግና ጠቦ ደረሶን፣ ንጉሥ ምኒልክ ጎበና ዳጨን መርጠው ኦሮሞ ቤት ሰደዱ፡፡›› በተባለው መሠረት (ተክለ ኢየሱስ፤ 2008፡263) በተለይ ሙሉ ወለጋን፣ ጅማን፣ ኢሉንና ምዕራቡን የሸዋ ክፍል (ባኮ፣ ትቤንና ጨሊያን ጨምሮ) ያስገበረው ተክለ ሃይማኖት ነበር፡፡ በወቅቱ ታዲያ በእነዚህ አከባቢዎችም ጥቃት አልደረሰም ነበር ብሎ ለመደምደም ይከብዳል፤ በዚህ ልክ ግን ተጋንኖ ሲነገር አልተሰማም፡፡
3. እጅና ጡት ቆረጣ የጀመሩት ዐጼ  ምኒልክ ናቸውን? 
—————————————————————-
አብዛኛው ሰው የአኖሌን እጅና ጡት ቆረጣ ታሪክ ሲሰማ ዐጼ ምኒልክ አንድም ይህንን ለመፈጸማቸው ተጨባጭ ምንጭ አይጠይቅም (በመረጃ ሊስተካከል የሚችል ታሪክ አድረጎ ከመረዳት ይልቅ እንደ እምነት ወስዶታልና)፣ አንድም ደግሞ ንጉሡ የዚህ ዓይነት መቀጣጫ ፈር ቀዳጅ (ጀማሪ) ሊመስለው ይችላል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡- ዐጼ  ምኒልክ ይህንን የጥቃት ቅርስ የወረሱት ከዐጼ  ቴዎድሮስ እንደሆነ በግልጽ የጻፉ አሉ፡- የኦሮሞ ታሪክና ፖለቲካ ነክ ጉዳዮች ጸሐፊው መኩሪያ ቡልቻ ጭምር ‹‹Contours of the Emergent and Ancient Oromo Nation›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ The Mass Mutilation of Anole-the legacy of Tewodros-II በሚል ዘግበዋል፡፡
ቢያንስ አንድ እውነት ይታወቃል፤ ዐጼ  ቴዎድሮስና ዐጼ ዮሐንስ ከዐጼ  ምኒልክ እንደሚቀድሙ፡፡ ዐጼ  ቴዎድሮስና ዐጼ ዮሐንስ ደግሞ አካል መቁረጥ ዋና የመቅጫ ስልታቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ለምሳሌ፡-
✍️ ዐጼ ቴዎድሮስ እጅና እግር መቁረጥ ብቻም ሣይሆን ከቆረጡ በኋላም የፊጥኝ እያሰሩ ወደ ገደል ይጨምሩ ነበር (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1983፡24-25፤ ገብረ ሥላሴ፣ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፣ 2008፡42፤ ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣ 2006፡382፣ 413)፡፡
✍️ ዐጼ ዮሐንስ እጅ፣ እግርና ከንፈር ቆርጠዋል (ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡196 ላይ ከእንግሊዛዊው ጀኔራል ጎርዶን [General Gordon’s Journal, P.216]  የተጠቀሰ፤ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንነት፣ 1982፡200-201፤ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡262)፡፡
እናም ዐጼ  ምኒልክ የእነርሱን ‹‹የመቁረጥ ሌጋሲ አስቀጥለዋል›› ካልተባለ በቀር ‹‹ጀማሪው እርሳቸው ናቸው›› ወደሚል ድምዳሜ አያደርስም፡፡
በጥቅሉ ታሪካችን መልካም ነገሮች እንደነበሩት ሁሉ አሉታዊ ገጽታዎችንም አስተናግዶ አልፏል፡፡ በተለይ የመቁረጥና መቆራረጥ ታሪካችንን ስንዘክር ያልቆረጠም ሆነ ያልተቆረጠ ብሔር የለም፤ ያልተቆረጠና ያልፈረጠም አካል የለም ብሎ ለመደምደም ይቻላል፡፡ የተለያዩ ነገሥታትም የየራሳቸውን የቅጣት ዓይነት ሲጠቀሙ ነበር፡- እነ ዐጼ ዘርዓ ያዕቆብ ቋንጃና ምላስ ቆርጠዋል፤ እነ ዐጼ ሱስንዮስ ጭንቅላት ቆርጠዋል፤ እነ ዐጼ  ቴዎድሮስ እጅና እግር ቆርጠዋል፤ የኦሮሞ ተዋጊዎችም ቢሆኑ የማረኳቸው ወታደሮች በገዳው ሥርዓት መሠረት ሊገቡ ካልፈቀዱ ብልታቸውን መቁረጥ ዋና ቅጣታቸው ነበር፡፡ ይህንን ብቻ ይዘን ታዲያ ‹‹የቆረጣና ቆራጣ ታሪክ›› መጻፍ፣ በዚህች ክስተት ብቻ ስንናቆር መኖር ግን አሁንም የአካል መጎዳደሉን ታሪክ ይደግመው እንደሁ እንጂ ሊያክመን አይችልም፡፡
4. ጥቃቱስ ‹‹ብሔር-ተኮር›› ነበርን?
——————————————-
‹‹ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በተለየ ሁኔታ በኦሮሞ ላይ ተፈጽሟል›› የሚል ክስ ከዘመናችን ጠርዘኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚነሳ ሌላኛው ነጥብ ነው፡፡ በአገራችን የነበሩት ትግሎች በአብዛኛው ሀብትና ሥልጣንን መሠረት ያደረጉ እንጂ አሁን እንዳለው ግንዛቤ የዘር ጉዳይ አልነበረም! ለምሳሌ፡- ጎንደሬው ዐፄ ቴዎድሮስ የጎንደሬዎቹን እጃቸውን ቆርጠዋል፣ በአንድ ቤት ውስጥ አስገብተው አቃጥለዋቸዋል፤ በጎጃም (ሞጣ አካባቢ) ብዙ ሕዝብ ጨፍጭፈዋል፡፡ ዛሬ ‹‹አማራ ክልል›› በተባለው የሸዋ ክፍል ወርደውም ብዙ እጆች ቆርጠዋል፡- ‹‹ዐፄ ቴዎድሮስ እጅግ ተዋረዱ፤ የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነሥተው ሄዱ›› ብላ ያለቀሰችውም ባሏን በዚህ ቅጣት ያጣች ሴት ነበረች (ተክለ ኢየሱስ፤ 2008፡221)፡፡
እናም እነዚህን ሁሉ ክስተቶች ታዲያ ዛሬ ላይ ሆነን አማራውን ከመጨቆንና ከማጥፋት አንጻር ካየነው፣ ቅኝ ግዛት አድርገን ከተመለከትነው ትልቅ ስሕተት ይሆናል፤ አማራ የአማራን ዘር ሊያጠፋም፣ ቅኝ ሊገዛም አይችልምና!
በሌላ መልኩ ደግሞ የሕዝቦች አሰፋፈርና የመልክዓ ምድሮች አከላለል እንደዛሬው ስላልነበር፣  የዛሬው ዓይነት ክልላዊ አደረጃጀትና ዘውጋዊ ፖለቲካም ስላልነበር ሁለቱን በግልጽ ለይቶ ‹‹አማራ›› እና ‹‹ኦሮሞ›› በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው የተፋለሙበት አድርገን መቁጠር የለብንም፡፡ ለምሳሌ፡- በሰገሌው ጦርነት ላይ ወሎ (ራስ ሚካኤል) እና ሸዋ (ተፈሪ መኮንን) ተዋግተዋል፤ በወሎና በሸዋ ውስጥ ግን ዛሬም ድረስ ኦሮሞንና አማራን በግልጽ ድንበር መለየት አይቻልም፡፡ በምኒልክና በተክለ ሃይማኖት ምክንያት እምባቦ ላይ ሸዋና ጎጃም ተጫርሷል፤ ምንም እንኳን በምኒልክ ወታደሮች ውስጥ የሸዋ ኦሮሞዎች ቢበዙም አማራዎችም ነበሩ፣ እንዲሁም ሁለቱ ነገሥታት በአማራነት ከተፈረጁ ዘንዳ ‹‹የአማራና ኦሮሞ ጦርነት›› የሚያስብል አንዳች አሳማኝ ነጥብ አይኖርም፡፡
የአኖሌውን ግጭት ‹‹አማራ በኦሮሞ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ›› አድርጎ ማራገብ አግባብ የማይሆንበት ሌላም እውነታ አለ፤ የሠራዊት ስብጥር፡፡ በእውነቱ የዐጼ ምኒልክ ጦር የተገነባው በአብዛኛው በኦሮሞ ፈረሰኞች ሲሆን ታየ ቦጋለ ‹‹9/10ኛው በኦሮሞ፣ 1/10ኛው በአማራ የተገነባ ጦር›› እንደነበር ያስቀምጣሉ (ታየ ቦጋለ፤ መራራ እውነት፤ 2011፡246)፡፡ የኦሮሞ ታሪክ ጸሐፍት ራሳቸው ለዐጼ ምኒልክ ማሸነፍ ዋነኛ ምክንያቶች ብለው ከሚጠቅሷቸው ነጥቦች መካከል አንደኛው ‹‹ታዋቂ የኦሮሞ ሰዎችን በመሣርያነት መጠቀማቸው›› ከመሆኑም በላይ በግልጽም ‹‹የኦሮሞን ግዛት ያሸነፉት ምኒልክ ሣይሆኑ ራስ ጎበና ነበሩ›› እስከማለት ደርሰዋል (ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006 ዓ.ም፤ ገጽ 501 እና 503)፡፡ ይኸ ከሆነ ደግሞ ኦሮሞ በገዛ ወገኑ ላይ የታቀደ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሊያደርግ እንደማይችል ግልጽ ማሳያ ነው፡፡
በጥቅሉ የቀደሙቱ ግጭቶች ምክንያት ፈጽሞ የብሔር ጉዳይ፣ አንዱ ብሔር ሌላውን ለመጉዳትም ያደረገው አልነበረም፤ የጥንቱን በአሁኑ የአስተሳሰብና የፖለቲካ ቅኝትም እየመዘኑ ትውልድን ማሳሳትም ትክክል አይደለም!
 
5. የድርጊቱ አፈጻጸም በኢትዮጵያውያን ልማድ ሲገመገምስ?
—————————————————–
ስለ አኖሌ ትርክት ልብ ልንለው የሚገባው ሌላኛው ነጥብ (ምናልባትም በአብዛኞቹ ጸሐፍት የማይጠቆመው) የድርጊቱ አፈጻጸም ሂደት ነው፡፡ ‹‹እውነተኛ ታሪክ›› አድርገው የሚነግሩን ሁሉ የጻፉት ንጉሥ ምኒልክ የእጅና ጡት ቆረጣውን ያካሄዱት በይፋዊ ጦርነቱ ወቅት አልነበረም፡፡ አርሲን የማስገበር ድሉም የተጠናቀቀው በአኖሌ ሣይሆን ከስድስት ተደጋጋሚ የመያዝ ሙከራዎች፣ ምናልባትም አራት ተከታታይ ዓመታትን ከፈጀ ጥረት በኋላ ራስ ዳርጌ ሣህለ ሥላሴ (የምኒልክ አጎት) በመሩት የመጨረሻው ዘመቻ አዙሌ በተባለው ቦታ ነበር (ታቦር ዋሚ፤ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፤ 2006፡488-489)፡፡
እናም ቆረጣው ተፈጸመ የተባለው ይልቁንም አርሲን በቁጥጥራቸው ውስጥ ካስገቡና የራሳቸውን ሰው ለአከባቢው ገዥ አድርገው ከሾሙ (ጦርነቱ ከተጠናቀቀ) አንድ ዓመት በኋላ ‹‹ኑና እንታረቅ›› በሚል ማታለያ ወደ አኖሌ ሰብስበው ነው (Abas Haji, 1995:15-16፤ ታቦር ዋሚ፤ 2006፡489)፡፡ በውኑ ይኸ ዓይነት አታልሎ ማጥቃት ስልት በኢትዮጵያውያን ታሪክ ውስጥ ነበር ወይ? ብለን ደግሞ እንጠይቅ፡፡
‹‹ውረድ እንውረድ›› ብሎ ለትግሉ ቀድሞ የሚቀጣጠር፣ ይዋጣልን! ብሎ የሚፎክር ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን የሸፍጥ ስልት (ያውም ባሸነፉት ሕዝብ ላይ፣ ደግሞም አንድ ሙሉ ዓመት ዘግይቶና አዘናግቶ) ይፈጽማል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ መምህር ብርሃኑ አድማስ በአንድ ወቅት ለዚህ ዓይነቱ ባህል የፊታውራሪ ገበየሁን ‹‹ፈሪ ይመስል ጠላቴን ከኋላ አልወጋም!›› አገላለጽ ጠቅሶ ተርጉሟል፤ ‹‹ለጠላት እንኳን ግልጽነት (fairness) ማሳየት ይገባልና›› በሚል፡፡ በሀገሪቱ የታሪክ ድርሳናትም ውስጥ ‹‹እየመጣሁ ነኝና በዚህ ቀን፣ እዚህ ቦታ ላይ እንገናኝ፤ ተዘጋጅተህ ጠብቀኝ›› የሚል ቅድመ ማስጠንቀቅያዎች ሲሰጡ እንጂ ድንገት ደርሶ (አድብቶ) ማጥቃት የተለመደ አልነበረም፤ ጀግና የሚያሰኘው ቅሉ ይህ ነውና! በዚህ አንድምታ መሠረት ታዲያ የዐጼ ምኒልክ አመራር ከዚህ እሴት ተቃራኒ በሆነ መልኩ የአርሲን ሕዝብ አዘናግቶና ‹‹እንታረቅ›› በሚል አታልሎ ይህንን ጥቃት ፈጽሞ ከሆነ በታሪክም ሆነ በሰማይ ተጠያቂ ከመሆኑም በላይ ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ ሊያስብለው አይችልም!
በእውን የሴት ልጅ ጡት መቁረጥስ በኢትዮጵያውያን ታሪክና እሴት ውስጥ ይታወቅ ነበር ወይ? የሚለውንም ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ጦርነት ሲታሰብ ‹‹ወንድ ከሆንክ ግጠመኝ›› እየተባለ ከወንድነት ጋር ከመያያዙም በላይ ሴት ልጅ ትማረካለች እንጂ እንኳንስ ጡቷ ሊቆረጥ ቀርቶ በጦር ስትወጋ፣ በጥይት ስትደበደብ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ እጅና እግራቸው እየተቆረጠ፣ ዓይናቸው እየፈረጠ፣ ብልታቸው እየተሰለበ ይገደሉ የነበሩትም ወንዶች ብቻ ናቸው፤ በባህሉም ‹‹ጀግና›› ያሰኝ የነበረው ወንድን በመግደል እንጂ ሴትን አልነበረምና፡፡ ዛሬም ድረስ በአብዛኞቹ የሀገራችን ክፍሎች ሴትና ቄስን መግደል (ማጥቃት) የወንድነት መለኪያ አይደለም፡፡ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ ጾታቸው ወንድ በመሆኑ ብቻ የማይገደሉ (እንደ ሴት ተንቀው የሚታለፉ) እንደነበሩም አይካድም፤ ከአራዊት መካከል አንበሳን፣ ነብርን፣ ጎሽንና ዝሆንን የገደለ ከፍተኛ ክብር እንደነበረው ሁሉ በጦር ሜዳም ታዋቂ ጀግና ካልገደሉ ዝም ብሎ መፎከር አልነበረምና፡፡ ነባሩ ባህል እንዲህ እንደነበር ለመረዳትም፡- ‹‹የትግሬንም ንጉሥ የሸዋንም ንጉሥ ሲንቁ  ሲንቁ፣ ወንድ አለራስዎ ገድለውም አያውቁ፤ በመቅደላ በኩል ጩኸት በረከተ፣ የሴቱን አናወቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ›› ተብለው ለዐጼ ቴዎድሮስ  የተገጠሙላቸውን ስንኞች ልብ ይሏል (ተክለ ጸድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1981፡439፤ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፣ 2008፡242)፡፡ እናም ሴትን ልጅ ገድሎና አካሏን አጉድሎ መፎከር በውኑ የቀደምት ኢትዮጵያውን ባህል ካልነበረ ትርክቱ እንዴት ሚዛን ሊደፋ እንደሚችል መጠየቁ አይከፋም፡፡
ዲ.ሳልቫይች የተባለ አፍቃሬ ኦሮሞ ፈረንሳዊ እንኳን በእነ አባስ ሐጂ አካሄድ ከአከባቢው ሽማግሌዎች ሰማሁ በሚል The Oromo, an Ancient people, Great African Nation በሚል መጽሐፉ ውስጥ 400 ያህል ወንዶች እጃቸውን መቆረጣቸውን እንደነገሩት ጠቅሶ የሴቶችን ጡት ጉዳይ ግን አልጠቀሰም፤ በቃል እንኳን ሲነገር ያልሰማው፣ ደግሞም ያልጻፈው ባይኖር ነው ያስብላል፡፡
6. ለተቆረጠው አካል ሁሉ፣ በተቆረጠበት ቦታ ሁሉ ሐውልት እናቁም?
——————————————————-
ይህ የአኖሌ ትርክት በወቅቱ በነበረው የሥልጣን የበላይነት የተነሣ  እውነት ተደርጎ ቢሆን እንኳን ኦሮሞ የበላይ ቢሆን ኖሮ ይህንኑ፣ የባሰም ሊያደርግ እንደማይችልም ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ እንዲያውም ኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የብሔረሰቡ ጦረኞች ተዋግተው ለማረኩት ጠላት ሁለት አማራጮችን ይሰጡ ነበር፡- እሺ ብሎ ከተገዛ ‹‹ኢልማ ቦጂ›› (የምርኮ ልጅ) በማለት በሰላማዊ ኑሮ ይቀበሉታል፤ አሻፈረኝ ለማለት የሚፈልግ ከሆነ ግን የወንድነት ብልቱን ቆርጠው አፉ ውስጥ እስከመክተት፣ በግዳይነትም ለአለቆቻቸው ያቀርቡ እንደነበር በሕዝቡ ታሪክ ውስጥ ጭምር የተዘገበ፣ በጉልኅ የሚታወቅም ነው (Richard Pankhurst, The Ethiopian Borderlands, P.284፤ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ከአሜን ባሻገር፣ 2008፡ 198):: ታዲያ አንድ ወቅት፣ በሆነች ቦታ እጅና ጡት ተቆርጧል ተብሎ እነዚህኑ አካላት የሚመስል ሐውልት የሚቆም ከሆነ ጦርነት ያልተካሄደበት፣ የወንድ ብልትም ያልተቆረጠበት ቦታ ስለማይኖር በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ለተቆረጡት ብልቶች ሁሉ ሐውልት ስንሰራ ልንኖር ነው፡፡
የዐጼ ዘርዓ ያዕቆብን ቅጣት ለመዘከር ብለን በደብረ ብርሃን የቋንጃና ምላስ ሐውልት አልተከልንም፡፡ ለዐጼ ሱስንዮስ ግፍ አጸፋ ካቶሊኮችን እንደ ጭራቅ የሚስል ትርክትና ሐውልት አልቀረጽንም፡፡ ዐጼ ቴዎድሮስ በሸዋ የበርካቶችን ሰዎች እጅ ለቆረጡበት የእጅ ሐውልት እስካሁን አልቆመም፤ በወርቂቱ ወታደሮች ላይ ያደረጓቸው ግፎችን ለመዘከርም በወሎ ድንጋይ ለመቆለል አልደከምንም፡፡ ሚካኤል ስሁል በአሰቃቂ ሁኔታ ዓይን በወስፌ ጎልጉለው ላሳወሩበት ጥቁር ታሪካችን የዓይን ሐውልት አልተሠራም፡፡ ዐጼ ዮሐንስ በወሎ ምላስ እንዳስቆረጡ፣ አፍንጫ እንዳስፎነኑ ቢነገርም ወሎ ውስጥ ግን የምላስም፣ የአፍንጫም ሐውልት እስካሁን አልተከልንም፡፡
ከኦሮሞዎች በኩል ከተሰነዘሩት ጥቃቶችም ጥቂቶችን እንመልከት፡- አስቀድሞ እንደተገለጸው የኦሮሞ ወታደሮች (በግራኝ ወረራ ጊዜ) የምርኮኛ ወንዶችን ብልት ሰልበዋል፤ በሌላ ጊዜም አባዱላ ጉጂ የላስታን ባላባት የባላንባራስ ወልደ ተክሌን ጣቶቹ አስቆርጧል፣ የህንጣሎ (ትግራይ) ሰዎችን ዓይን በወስፌ አስጎልጉሏል (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› መጽሐፉ ገጽ.195 ላይ ‹‹The Life and the Adventures of Natnael Pearce, P.75›› ከሚለው፣ ጉጂን በአካል ከሚያውቀው የዓይን ምስክር ናትናኤል ፒርስ ጠቅሶ  እንዳሰፈረው)፡፡ በእነዚህ ግፎች ምክንያት የወንድ ብልትና የዓይን ምልክት ያለባቸው ሐውልቶችን አቁሞ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ያካሄደ ሕዝብ ግን እስካሁን አላየሁም፣ አልሳማሁምም፡፡ በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን የነበረው የጎማው ኦሮሞ ባላባት ይፈጽማቸው በነበሩ ሰቅጣጭ የጭካኔ ድርጊቶች (እጅ፣ አፍንጫና ጆሮ መቁረጥ፤ ዓይን ማፍረጥና ድንጋይ በአንገት አስሮ ወደ ወንዝ ማስመጥ) ሁሉ (Harris, Ethiopian highlands በተባለው መጽሐፉ ቅጽ ሦስት፣ ገጽ.160) ወቅት ለተቆረጠው አካል ሁሉ ሐውልት ይቁም ቢባል ሀገሪቱ በቂም ሐውልቶች ብቻ ትጥለቀለቅ ነበር፡፡ በእምባቦ ጦርነት ምክንያት የሸዋ ኦሮሞዎች በጎጃም ላይ አቂመው ዓባይ በረሃ ውስጥ እየጠበቁ የጎጃሞችን ብልት ሲሰልቡ፣ በስልቻም እየጫኑ ግዳይ ይጥሉ ነበር (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡267)፤ ይህንን ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች በትዝታ መልክ ከማውራት በዘለለ ለዚህ ተብሎ አማራ ክልል ውስጥ የቆመ አልያም ሊሠራ የታሰበ የቆለጥ ሐውልት እስካሁንም የለም፡፡
ከእነዚያ በፊትም ሆነ በኋላ (በቅርቦቹ መሪዎች ጭምር) መሰል የጭካኔ ሥራ ላለመሠራቱ ምንም ዋስትና የለም፡፡ ቢያንስ በዘመናችን እንኳን የቀድሞው ኢህአዴግ መንግሥት ራሱ በታራሚዎች ብልት ላይ ሃይላንድ ያንጠለጥልና ጥፍር ሲነቅል፣ ከአውሬዎችም ጋር ያስር እንደነበር በይፋ አምኗል፡፡ ለነዚህ ግፎች ግን ይቅርታ ከመጠየቅ፣ ለወደፊቱ እንዳይደገም ቃል ገብቶ ወደፊት ከመንቀሳቀስ በቀር የብልትም፣ የጥፍርም ሆነ የአውሬ ሐውልት አልሠራልንም፤ ትርፉ ‹‹እህህ ብቻ›› ነውና! በታሪክ ውስጥ ለተከሰቱት ግፎች ሁሉ ሐውልት አንተክልም ማለት ግን እውቅና ሰጥተናል፣ ደግፈናል ማለት አይደለም፤ ያለፈውን ጥፋት ረስተን መጻዒውን ሰላምና ልማት አርቆ ማሰብን እንደመረጥን ያሳያል እንጂ፡፡
ሌላው ቀርቶ ከወጪ አንጻር እንኳን ብንመለከት፡- ለአኖሌ ሰማዕታት ሐውልት ከ20 ሚልዮን ብር በላይ፣ ለጨለንቆው መታሰቢያ ሐውልት ደግሞ 34 ሚልዮን ብር በኦሮምያ መንግሥት ወጪ መደረጉ ታውቋል፡፡ የዕለት ጉርሷን እንኳን ለማረጋገጥ በምትቸገር ሀገር ይህንን ያህል ወጪ አውጥቶ የጥላቻና ቂም በቀል ሐውልት መገንባት ምን ማለት እንደሆነ ለመገመት አይከብድም፡፡ የእነዚህ ሐውልቶች ጥቅም ‹‹ለትውልድ መማርያ፤ መሰል ጥፋት መችም እንዳይደገም ለማሳሰብ›› ቢባል እንኳን ለትውልድ የሚተላለፈው ፍጹም ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ፣ ‹‹መችም ቢሆን ቂምህን እንዳትረሳው›› የሚል እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በእርግጥ ታሪኩ  በትክክል ለመፈጸሙ በቂ ማረጋገጫ እስከቀረበ ድረስና ‹‹የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ጠብ›› ተድርጎ እስካልተተረጎመ ድረስ ግን የመታሰቢያ ሐውልቱ መቆሙ ችግር አይኖረውም፤ በወቅቱ የነበረው ሥርዓትና የአማራ ሕዝብ ፈጽመው የተለያዩ ናቸውና፡፡
ስንቋጨው፡- ጥንት ለተፈጸሙ እንከኖች ሁሉ የበደል ሐውልት እያቆምን በሄድን ቁጥር ጥላቻን ከመርሳት ይልቅ ለትውልድ ቂምን እያስተላለፍን፣ እኛ ከሞትን በኋላ እንኳን እርሱ ‹‹ደም መላሽ›› ሆኖ እንዲያድግ የቤት ሥራ እየሰጠነው እንቀጥላለን፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህል ሀገር እንደሚገነባ ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ሬነ የተባለ የፈረንሳይ ሊቅ፣ ‹‹ሀገር ምንድን ናት›› በተባለ ስመ ጥር ስብከቱ፡- ‹‹ሰዎች ሀገር ለመገንባት ከፈለጉ በታሪክ ውስጥ የተፈጸሙ አንዳንድ ግፎችን ለመርሳት ዝግጁ መሆን አለባቸው›› ብሎ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ፈረንሳዮች ‹‹የቅዱስ በርተሎሚዎስ ጭፍጨፋ›› እየተባለ የሚታወቀውን (የፈረንሳይ ካቶሊኮች በፕሮቴስታንቶች ላይ የፈጸሙትን) መርሳት ነበረባቸው (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡1943)፡፡
እውነትም በጥንቱ ቁርሾ ሁሌ ወደኋላ እየቆዘሙ ወደፊት መጓዝ፣ በሰላምም አብሮ ሀገር መገንባት ይከብዳል፡፡ እናም በአንድ በኩል በታሪክ ውስጥ ተፈጽመዋል ተብለው የሚነገሩ ትርክቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል አላግባብ ተጋንነው እንዳይነገሩ በትክክለኛ ማስረጃ መሞገትና ማስተባበል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለመፈጸማቸው እርግጠኛ የሆንባቸውንም ግፎች ቢሆን በይቅርታ የክስ መዝገቡን ዘግተን የሚቀጥለውን የፍቅር ታሪክ በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ሲባል ግን ያለፈን ታሪክ ሙሉ በሙሉ አናንሳ ማለት አይደለም፤ George Santayana የተባለ የስፔን ፈላስፋ፡- ‹‹ታሪካቸውን ያልተረዱ ሰዎች ያንኑ [የጥፋት] ታሪካቸውን ለመድገም የተፈረደባቸው ናቸው›› ያለው እንዳይከሰት የጥፋት ታሪኮችንም አውቀን ከመሰል ጥፋቶች እንጠበቅ ዘንድ ያስፈልጋልና:: እናም በታሪክ ሂደት እርስ በርሳችን ከመናቆራችን የተነሣ የቋጠርነው ቂም እንኳን ቢኖር በተሻለ የአብሮነትና መተሳሰብ ታሪክ ዝማኔአችንን በተግባር ማስመስከር ይኖርብናል እንጂ ዘወትር አካል ተቆረጠ፣ ዓይን ፈረጠ፣ አጥንት ተፈለጠ ብለን እያላዘንን ከብልታችን በላይ በተሰለበ ሥነ ልቡና ውስጥ መኖር አይጠበቅብንም!
7. እኛስ በዘመናችን ከነገሥታቱ ጭካኔ የሚበልጥ አላደረግንምን?
———————————————
ቀደምት ነገሥታት ይመሩ የነበሩት በወቅቱ በነበረው የግንዛቤ ደረጃና ጥንታዊ የሕዝብ አስተዳደር ሕግ እንጂ እኛ ባለንበት ‹‹የሥልጣኔ›› ዘመን አይደለም፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥበቃ›› በሚለው የ21ኛው መ/ክ/ዘመን አንጽም ሊዳኙ አይችሉም፡፡ በእነርሱ ዘንድ መቁረጥና መፍለጥ የዘመናቸው ወንጀል መቅጫ ደንብና የጀግንነታቸውም ማሳያ ከነበረ ያንን ክስተት በዛሬው ሕጋችን ዳኝተን ‹‹ወንጀል ብቻ›› ልናደርገው አንችልም፤ የታሪክን ክስተት ከጊዜ፣ ከቦታና ከኩነት ለይተን መገንዘብ ሚዛናዊ አያደርግምና፤ የሙያው ሥነ-ምግባርም አይፈቅድምና፡፡
ምናልባትም እኛም ብንሆን በእነርሱ ዘመን ኖረን ቢሆን ኖሮ ያንኑ የማናደርግበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም ነበር፡፡ እነርሱስ ትምህርት ስለሌላቸው፣ ከዚያ የተሻለ መፍትሔ ማምጣት ተስኖአቸው ሊሆን ይችላል፤ የእኛ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ተምሮ በባሰ ግፍ ውስጥ መጨመላለቅ ግን ምንኛ ይደንቅ! እንኳንስ በዚያን ወቅት ቀርቶ ‹‹ሰልጥነናል፣ ዘምነናል›› ብለን በምንኩራራበት በዛሬው ዘመናችን እንኳን ከነገሥታቱ ጭካኔ የባሱ አሳፋሪ ድርጊቶችን እየፈጸምን መሆናችን መዘንጋት የለበትም፡-
✍️ ከበርካቶች መገደልና መሞት  በላይ እጅግ የሚያሳዝነውና ልብ የሚሰብረው ‹‹አሟሟቱ›› ሆኗል፤ ለማንም የማይቀረውን ሞት በተፈጥሯዊ መንገድ መቅመስ የሚያስናፍቅ፣ ‹‹አሟሟቴን አሳምርልኝ›› የሚባለው ጸሎትም በተግባር የታየበት የጭካኔ ትውልዶች ሆነናል!!
✍️ አካል ከመቁረጥና ከማረድም አልፈን ሰውን ዘቅዝቀን ሰቅለናል! ((በ2011 እና 2012 ዓ.ም፣ በምዕራብ አርሲ ውስጥ ብቻ ሁለት የዘቅዝቆ መስቀል ግፎችን በዓይናችን አይተናል))
✍️ አስገድዶ መደፈርም ሆነ በመሣርያ መገደል ያለ ነገር ነው፤ በእኛ ዘመን ግን እንስሳት እንኳን በማይፈጽሙት አካሄድ ሕጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶችና የጃጁ አሮጊቶች ከመገደላቸው በፊት [ሞትም ላይቀርላቸው] በልጅ ልጆቻቸው ተደፍረዋል!
✍️ እንኳንስ የራስ ብልትና ደም ቀርቶ የተፋነው ምራቃችንን መልሰን ለመዋጥ እንኳን እንጸየፍ የነበርን ኢትዮጵያውያን በዘመናችን ግን የሰዎች ብልትና ጡት መቆረጡ ሳያንስ የተቆረጠ አካላቸውን በአፋቸው እንዲጎርሱ ያስገደድን ግፈኞች ሆነናል!
✍️ በነባሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ባህል መሠረት እንኳንስ ቤተሰብ ቀርቶ የቅርብ ዘመድም ሲሞት ሟቹ ‹‹አፈር እስኪቀምስ›› (እስኪቀበር) ድረስ እህል ውኃ እንኳን በአፋችን የማይገባ የነበርን ሰዎች ዛሬ ላይ ግን የክርስቶስን ደም የሚሰዋ ካህንን በቤተ መቅደሱ ፊት ማረዳችን ሳያንስ የካህኑ ልጅ የአባቷን ደም እንድትጠጣ ያስገደድን ጉዶች ነን! ((የበሻሻ ግፍ እንደማሳያ))
✍️ ለአክራሪዎች መግደል፣ ለክርስቲያኖች ደግሞ  መሞት የጽድቅ መንገድ ነው፤ ስቃይን በሚያበዛ መልኩ የሰውነት ክፍሎቻቸውን ተራ በተራ እየተቆራረጡ፣ ከአንዱ ሞት በፊት በርካታ የሞት ስቃዮችን እያከናወኑ፣ በሰዎች የሰቆቃ ድምጽ እየተደሰቱ መግደል ግን በእኛ ትውልድ የታየ ጉድ ነው! ((በጥይት የተመቱ ሰዎች እንኳን ‹‹ጨርሰኝ›› ብለው ባልንጀሮቻቸውን ጭምር የሚማጸኑት ወደው ሣይሆን መሞት ላይቀር እንዳይሰቃዩ ነው፤ ‹‹የርኅራኄ ግድያ›› (Mercy Killing) የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ወደ ዓለም የመጣውም ከዚህ የተነሣ ነበር))
✍️ በየትኛውም የአገዳደል ሁኔታ ሰው መግደልስ ያለ ነው፤ ‹‹ምድራችንን ያረክሳልና መሬታችን ላይ አይቀበሩም!›› ብሎ የገደሏቸውን ክርስቲያኖችን አስከሬን ማጉላላት፣ እንዳይቀበርም አድርጎ ማቃጠል ግን ትውልዳችን በምድረ ኢትዮጵያ የፈጸመው የግፍ ግፍ ነው! ((በምሥራቅ ሐረርጌ ቦረዳ ከተማ ይህ ተደርጓልና))
✍️ ሕግና የሕግ አካላት በሌሉበት ቦታ በወንጀለኞች እጅ መገደልስ ያለ ነው፤ ይከላከልልኛል ብለው ከሸሹበት ፖሊስ ጣቢያ አስወጥተው የመንግሥት ቢሮ ውስጥ መግደልን የመሰለ፣ ‹‹ከነብር ጥፍር አምልጦ በአንበሳ ጥርስ የመግባት›› ድርጊት ግን ከኢትዮጵያ ውጭ በየት ሀገር ተፈጽሞ ይሆን?!
✍️ መንግሥት በመዋቅር ደረጃ የማይደግፋቸውን ወንጀሎች በአስፈጻሚነት ደረጃ ላይ ያሉት ግለሰቦች በሚያደርጓቸው የወንጀል ሰንሰለቶች ግፍ ይፈጸም ይሆናል፤ በመንግሥት መመሪያ ደረጃ፣ ያውም በክልል ምክር ቤት ደረጃ ተመክሮ በጸደቀ ‹‹ሕጋዊ ወንጀለኝነት›› ጅምላ ጭፍጨፋ የሚካሄድባት ሀገር ከኢትዮጵያ በቀር ከወዴት ትገኛለች!? ((በዘመናችን፣ በወርኃ ሐምሌ መጨረሻ 2010 ዓ.ም፣ በሱማሌ ክልል፣ ጅግጅጋ ይኸ በገሃድ ተፈጽሟልና))
✍️ በተጠቁበት ደዌ፣ ሕክምናም በማይገኝበት አከባቢ ለሞት መዳረግስ ያለ ነው፤ ሐኪም ቤት ለሕክምና ከገቡ በኋላ ያክመኛል ያሉት ሲገድል፣ ይፈውሰኛል ብለው የዋጡት መድኃኒት መርዝ ሆኖ እስከወዲያኛው ሲያሰናብት ግን ከፈጣሪ በቀር ለማን አቤት ይባላል?! ‹‹ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ፣ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ!›› እንዲሉ የሕክምና ተቋማትን ለሽብር ያዋለ ትውልድ ከእኛ ውጭ በዓለም ላይ የት ይገኛል?
እናማ በምን አእምሮአዊና ሥነ ልቦናዊ ልዕልና የቀደምት ነገሥታትን ስህተት ልንወቅስ፣ ‹‹ብልት ቆርጠዋል›› ብለን ልንከስስ ይቻለናል?! ትውልዱ አንድም ስለ አኖሌ ግፍ ትክክለኛነት ሳይስማማ፣ አንድም ከአኖሌ የባሰ ግፍ ራሱ እየፈጸመ ከመቶ ዓመታት ቀድሞ በተፈጸመ ጉዳይ መነታረክ ጥቅም አይኖረውም፤ የአኖሌው እጅና ጡት ቆረጣ በመጽሐፍ ባይጻፍ እንኳን ራሱ በክርስቲያኖች ደም ቀለምነት፣ በኦሮምያ ምድር ወረቀትነት አኖሌን በተግባር እየተረከልን ነውና!
Filed in: Amharic