>

ምርጫ ወይም ሞት...!!! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ምርጫ ወይም ሞት…!!!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የዘንድሮውን ምርጫ ማሸነፍ የሞት እና ሽረት ጉዳይ ነው። አሁን ያለው የአሜሪካ መንግስት ባለበት የሚቀጥል ከሆነ፤ አክራሪ ነጮችንና የሃብታም ሃብታሞችን መጥቀሙ አይቀርም። በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ መንግስታዊ አስተዳደር ባለበት መልኩ መቀጠሉ፤ የወደፊቷን አሜሪካ ብቻ ሳይሆን፤ የወደፊቱን አለም እና ህዝቦቿን ታሪክ ሊቀይረው ይችላል። በዛሬው ጽሁፋችን… ማ ማንን መምረጥ አለበት በሚል ጊዜ ማጥፋት አያስፈልገንም። ምክንያቱም ህዝብ የሚጠቅመውን ያውቃል፤ የኛ ትንታኔም አያስፈልገውም። ነገር ግን ይህን አጋጣሚ ምክንያት በማድረግ ስለ ምርጫው እና የምርጫው አቆጣጠር አንዳንድ ታሪካዊ እውነቶችን እናጋራችኋለን…!!!
 
የአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ በየአራት አመቱ ይከናወናል። ሁሌም ግን አዲስ የሚሆን ነገር አለ። እንኳንስ ለውጭው ሰው ቀርቶ፤ አሜሪካ ላሉትም Electoral Vote የሚባለው የምርጫ ሂደት ግራ ያጋባዋል። ይሄ Electoral Vote ደግሞ ጥቅም ላይ የሚውለው ፕሬዘዳንቶች ሲመረጡ ነው። በሌላ ጊዜ… የኮንግረስ እና የሴኔት ወይም የሌላ ሃላፊነት ቦታዎች በአብላጭ የድምጽ ይወሰናሉ፤ የአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ግን በ Electoral Vote እና Electoral College የሚወሰን ነው። ለመሆኑ ይሄ በምርጫ ሰሞን ደጋግመን የምንሰማው Electoral College ወይም Electoral Vote ምንድነው? እንዴትስ ነው የሚሰራው? (ትንሽ አብራችሁን በመቆየት ብዙ እውቀት አግኙ)
“ነገርን በምሳሌ…” እንደሚባለው አንዳንድ ሁነቶችን በማንሳት እንጨዋወታለን። ለምሳሌ ባለፈው የምርጫ ሂደት፤ ፕሬዘዳንት ትራምፕ “ይሄ Electoral Vote የሚባለው አሰራር ትክክል አይደለም።” ሲሉ ተቃውሟቸውን አቀረቡ። እንደፕሬዘዳንቱ አባባል፤ “ምርጫውን ማሸነፍ የሚገባው ከፍተኛ ድምጽ ያገኘ ነው።” በማለት አንገራገሩ። እናም በህዝብ ድምጽ ብልጫ አሸንፈው፤ በ Electoral Vote ቢሸነፉ፤ የተቀናቃኛቸውን ሂላሪ ክሊንተን ፕሬዘዳንትነት ላይቀበሉት እንደሚችሉ አሳወቁ።
በመጨረሻው በድምጽ ቆጠራ ወቅት፤ ሂላሪ ክሊንተን በጠቅላላ ድምጽ አሸነፉ፤ ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ Electoral Vote አሸነፉ። እናም በህጉ መሰረት ዶናልድ ትራምፕ አሸናፊነታቸው በኦፊሴል ሲተዋወቅ፤ ሂላሪ ክሊንተን በህዝብ ድምጽ ብልጫ ቢያሸንፉም በ Electoral Vote ስለተሸነፉ፤ በአሜሪካ ህግ መሰረት ተሸናፊ ሆኑ። እንዲህ ያለው በህዝብ ድምጽ አሸንፎ ፕሬዘዳንት አለመሆን ደግሞ በ 1824, 1876, 1888 እና 2000 ምርጫ ወቅት ተከስቷል። እና ይሄ Electoral Vote እንዴት ነው የሚሰራው?
ስለ Electoral Vote የመጨረሻውን ሚስማር ከመምታታችን በፊት፤ ታሪካዊ አመጣጡን እንንገራቹሁ። ነገሩ የሆነው አሜሪካ የመጀመሪያ ፕሬዘዳንቷን በመረጠችበት ወቅት ነው። በዚያን ዘመን… (ከ200 አመት በፊት መሆኑ ነው) በ1760ዎቹ ዘመን ተቋቁሞ ለአሜሪካ ነጻነት ይሰራ የነበረው ኮንግረስ፤ ለአገሪቱ ፕሬዘዳንት ሊኖረው እንደሚገባ አመነበት። ነገር ግን ምርጫውን ለማድረግ፤ ህዝቡን ማሰባሰብ ቅስቀሳ ማድረግ፤ የድምጽ ኮሮጆውን መዝጋት እና መክፈት፤ የህዝቡን ድምጽ መቁጠር እና ማጥቆር… ጊዜ የሚወስዱ፤ ለአሰራርም የማይመቹ ሆኖ አገኛቸው። ይህን ችግር ለማቃለል ኮንግረሱ ስብሰባ አደረገ።
በመጨረሻ በዘመኑ የነበረውና ተቀማጭነቱን ፊላዴልፊያ ያደረገው ኮንግረስ፤ በወቅቱ ለአሜሪካ ነጻነት እውቅና የሰጡ ክፍለ ግዛቶች (States)፤ የህዝቡን ድምጽ የሚያሳውቁ ተወካዮቻቸውን እስከ ጃኑዋሪ 7፣ 1789 ድረስ እንዲያሳቁ ለሁሉም ስቴት ገዢዎች በደብዳቤ ተገለጸላቸው። በዚህ መሰረት… ምርጫ ይደረግና፤ እነዚህ የህዝብ ተወካይ መራጮች (Electors) ደግሞ፤ የስቴቱ ገዢ (Governor) ፊርማ ያለበትን የምስክር ወረቀት ይዘው አስመራጮች ወደ ኮንግረስ ቀርበው የወከላቸውን ህዝብ ድምጽ እንዲያሳውቁ ተደረገ። የነዚህ ተመራጮች ስብስብ ደግሞ Electoral College ተባለ። ኮሌጅ የሚለውን ቃል በቀጥታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ብለን መተርጎም ስህተት ይሆናል። Electoral College ወይም የመራጮች ኮሌጅ – የምርጫው ሂደት እና ይህን የሚያከናውነው ጊዜያዊ ተቋም ማለት ነው።
አሁን ነገሮችን ወደራሳችን መልሰን፤ ምሳሌውን በራሳችን አድርገን እንጨዋወት። ባለፈው ሳምንት Early Vote ለማድረግ ከቤተሰቤ እና ጓደኞቼ ጋር ሆነን ወደ ምርጫ ጣቢያ ሄድን። ፕሬዘዳንት እና ምክትላቸውን መርጠን፤ ለሌሎቹም ድምጽ ሰጥተን ወጣን። እንግዲህ ለሌሎቹ የሰጠነው ድምጽ በድምጽ ብልጫ የሚወሰን ሲሆን፤ ለፕሬዘዳንቱ የሰጠነው ምርጫ ግን በተዘዋዋሪ መንገድ ለ Electoral College ወይም ለጆርጂያ ስቴት 16 ተወካዮች ነበር የሰጠነው። እናም በምርጫው ቀን መጨረሻ ላይ ቆጠራ ተደርጎ ሲያልቅ፤ በድምጽ ብልጫ ያሸነፈው ፕሬዘዳንት… ለጆርጂያ የተመደበውን 16 ድምጽ ይወስደዋል… ማለት ነው።
ሆኖም ከጆርጂያ የበለጠ እንደህዝብ ብዛታቸው መጠን፤ በዛ ያለ የድምጽ ቁጥር ያላቸው ስቴቶች አሉ። ለምሳሌ ካሊፎርኒያ 58 ኤሌክቶራል ድምጽ፤ ቴክሳስ 38፣ ኒው ዮርክ እና ፍሎሪዳ እያንዳንዳቸው 29 ድምጽ አላቸው… ሌሎቹም ስቴቶች የተለያየ ቁጥር አላቸው።
በአጠቃላይ 100 ድምጽ ለሴኔት ተወካዮች፤ 435 ለኮንግረስ ተወካዮች፤ ሶስቱ ድምጽ ለዋሺንግተን ዲሲ ይከፋፈላል። የዚህ ድምር ውጤት 538 ነው። እናም ፕሬዘዳንት የሚሆነው የእነዚህን ኤሌክቶራል ቮት ከግማሽ በላይ ወይም ከ270 በላይ ድምጽ ያገኘ ያሸንፋል። ሆኖ አያውቅም እንጂ፤ እኩል 270 ድምጽ ካገኙ… ኮንግረሱ በድምጽ ብልጫ ፕሬዘዳንቱን ይመርጣል።
ይህን ሁሉ ትንታኔ አድርገን መልሰው “Electoral Vote ምንድነው? አልገባንም” ካሉን፤ ችግሩ ከርስዎ ሳይሆን፤ ከኛ ሊሆን ይችላል። ምንም ይሁን ምን ግን… የድምጻችን ብዛት ተደምሮ ፕሬዘዳንት ባይመርጥም፤ የአሜሪካ መስራች አባቶች ያበጁትን፤  ኤሌክቶራል ድምጽ አሰጣጥ በማክበር… በመረጥናቸው ተመራጮች፤ ምርጫችንን በምርጫ መርጠን፤ የመረጥነው ተመራጭ… የመጨረሻው ምርጫ እንዲሆን፤ ዘንድሮ “Vote ወይም ሞት” ብለናል።
Filed in: Amharic