>

ግልጽ ደብዳቤ ላቶ ደመቀ መኮንን (መስፍን አረጋ)

ግልጽ ደብዳቤ ላቶ ደመቀ መኮንን

መስፍን አረጋ

 

ያብይ አህመድ ሒሳብ ኦነጋዊ ቀመር

በተግባር ቀንሶ፣ በወሬ መደመር፡፡


ይህ ግልጽ ደብዳቤ በተመሳሳይ ርዕስ ካንድ ዓመት በፊት የተለጠፈውን ግልጽ ደብዳቤ በትንሹ በመለወጥ በድጋሚ የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡   

ለክብር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የብልጽግና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፡፡  ይህን ግልጽ ደብዳቤ የምጽፍልወ ቁጭ ብለው የሰቀሉት ዐብይ አህመድ ቁመው የማያወርዱት መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡  ዐምባገነኖች እየተጠናከሩና እየተደላደሉ ሲሄዱ በመጀመርያ የሚያስወግዱት ለስልጣን ያበቋቸውን ሰወች ነው፡፡  እነዚህን ሰወች የሚያስወግዱት ደግሞ ምንነታቸውንና ማንነታቸውን ስለሚያውቁባቸው በነሱ ፊት በውሸት ትርክት ራሳቸውን መካብ ስለማይችሉ ነው፡፡       

‹‹ለውጥ›› በሚባለው ክስተት የመጨረሻው ሰዓት ላይ እርስወ አቶ ደመቀ መኮንን ከወያኔ ጉምቱወች ጋር ፊት ለፊት ሲጋፈጡ ዐብይ አህመድ ግን ማጀት ስለተደበቀ፣ እርስወን ባየና ያችን የቁርጥ ቀን ባሰባት ቁጥር ይሸማቀቃል፡፡  እርስወ ማለት ለዐብይ አህመድ ቱሪናፋነቱን በግልጽ የሚያሳዩት መስታወት ማለት ነወት፡፡  በርስወ ፊት ራሱን ማግነን ስለማይችል ጊዜውን ጠብቆ እንደሚሰባብርወት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ያ ጊዜ ደግሞ እየተቃረበ ይመስላል፡፡  የአጥናፉ አባተ ዕጣ ከፊት ለፊትወ ተጋርጧል፡፡   

ከባሕር ዳር ጭፍጨፋ በኋላ ዐብይ አህመድ (ያለምንም ጥርጥር በርስወ እሽታ) ባማራ ሕዝብ ላይ የጫነው የኦሮሙማው ሎሌ ተመስገን ጥሩነህ፣ ባስፈላጊው ጊዜ እርስወን ለማስወገድ ባንገትወ ላይ የተጠመጠመ አሲል እባብ መሆኑን መጠርጠር ብልህነት ነው፡፡   

ራስወን ለከፍተኛ አደጋ በማጋለጥ ዐብይ አህመድን ለስልጣን ያበቁት ጦቢያና የጦቢያ ብሔርተኞች (በተለይም ደግሞ አማሮች) ባማራ ጥላቻ ባበደው በጎጠኛው ወያኔ ከሚደርስባቸው መከራና ስቃይ ለመታደግ ነው ብየ እገምታለሁ፡፡  የዐብይ አህመድ አገዛዝ ግን ለጦቢያ ብሔርተኞች (በተለይም ደግሞ ላማሮች) ትሻልን ሰድጀ ትብስን አመጣሁ የሚያስብል ከእሳት ወደ ረመጥ የሆነ ኦነጋዊ አገዛዝ መሆኑን ለርስወ መንገር አያስፈልግም፡፡ 

ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ አጀንዳውን ማስፈጸም የሚችለው ግን በኦሮሙማ ጥንካሬ ሳይሆን፣  በእርስወ ድርጅት አማካኝነት አማራውን እስካዳከመ ድረስ ብቻ ነው፡፡  ስለዚህም የአማራ ዋነኛ ጠላት ወያኔ ወይም ኦነግ ሳይሆን፣ ተመስገን ጥሩነህን የመሳሰሉ የወያኔና የኦነግ ሎሌወች የተሰገሰጉበት የርስወ ድርጅት ነው፡፡  ወያኔ ለሃያ ሰባት ዓመታት ባማራ ላይ የተዘባነነው፣ ተረኛው ኦነግ ደግሞ ባማራ ላይ የሚጨማለቀው በስሙ ያማራ የሆነው የርስወ ድርጅት በግብሩ ፀራማራ በመሆኑ ብቻና ብቻ ነው፡፡  

ያማራ ስለሆነም የጦቢያ ችግር የአማራን ለምድ የለበሱ ተኩላወች እንጅ ወያኔ ወይም ኦነግ ወይም ሁለቱም አይደሉም፡፡  ሁነውም አያውቁም ወደፊትም አይሆኑም፡፡  ሕብረብሔራዊው አማራ በጠንካራ ድርጅትና በቆራጥ መሪ ከተመራ የነዚህ ጎጠኛ ድርጅቶች እድሜ ከወራት እንደማይዘል እነሱ ራሳቸው በደንብ ያውቁታል፡፡  ዐብይ አህመድን  እንቅልፍ የሚነሳው የኦነግና የወያኔ እስካፍንጫቸው መታጠቅ ሳይሆን፣ ያማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ መሆኑን እሱ ራሱ ባንደበቱ እንዲናገር ያስገደደውም ይህ ግንዛቤው ነው፡፡

ስለዚህም ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ‹‹ለውጡን›› የፈለጉት ያማራን ሕዝብ ለሃያ ሰባት ዓመት የለበለበውን የወያኔ እሳት በኦነግ ረመጥ ለመተካት ሳይሆን ጨርሶ ለማጥፋት ከሆነ፣ እኔ መስፍን አረጋ የምመክርወት ከሩሲያዊው ቦሪስ የልትሲን ትልቅ ትምህርት እንዲቀስሙ ነው፡፡    

ምዕራባውያን በቦሪስ የልትሲን አማካኝነት ሩሲያን አዋረዷትና በሩሲያውያን ላይ ለተወሰኑ ዓመታት ተጨማለቁባቸው፡፡  የልትሲን ግን ሩሲያን ለምዕራባውያን የቀን ጅቦች አሳልፎ ቢሰጣትም፣ በስተመጨረሻ ግን ከቀን ጅቦቹ የሚያስጥላትን ሩሲያዊ አንበሳ በቦታው ተክቶ፣ ላገሩ ትልቅ ውለታ ውሎ፣ የቆሸሸውን ታሪኩን አጽድቶ፣ በክብር አለፈ፡፡  ሩሲያም ባጭር ጊዜ ውስጥ አንሰራራችና፣ ያምሷት፣ ያተራምሷት የነበሩት ምዕራባውያን አመሰችን፣ አተራመሰችን እያሉ ይወቅሷት፣ ይከሷት ጀመር፡፡  የተሳለቁባትን ተሳለቀችባቸው፡፡

ስለዚህም ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ዐብይ አህመድ ምሳ ሳያድርግወት በፊት የጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ ያማሮች) ቦሪስ የልትሲን በመሆን ቁርስ ያድርጉት፡፡  ለጦቢያዊ ፑቲን ቦታወን በመልቀቅ ለኦነግ ጅብ የሰጧትን ጦቢያን ከጅቡ ለማስጣል የበኩልወን ይወጡ፡፡  ለራስወ መሽቶብወት ጦቢያን ሳያስመሹባት በፊት፣ ባንድ ድርጊት ሙሉ ታሪክወን አድሰው በጦቢያውያን ልብ ለዘላለም ይኑሩ፡፡  

 

EMAIL:  mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic