>

ብልፅግና ወንጌል !! (በዘማሪ ዶ/ር  ደረጀ ከበደ) 

ብልፅግና ወንጌል !!

በዘማሪ ዶ/ር  ደረጀ ከበደ 
ከቤተመቅደስ እስከ ቤተመንግስት

መንግስታት በቀንደ መለክትና በአዋጅ ሊያግዱት ሲገባ ቸል በማለታቸው በአመታት መካከል አድጎና መንድጎ፣ ብዙሃኑን አራቁቶ፣ ጥቂቶችን ሚሊኒየርነት ማማ ላይ የሰቀለ አስተምሮ ምን እንደሆን የሚገምት ሰው አለ? ታመው የሚማቅቁን ተፈውሳችሁዋል፣ የደህዩትን ባለጠጋዎች ናችሁ፣ አንድ ብር ስጡና እግዚአብሄር 10 ብር አድርጎ ይሰጣችሁዋል የሚለውንስ የተወላገደ ትምህርት ታውቁት ይሆን??? አማኝ የሚታመመውና የሚደሀየው ጠንካራ እምነት ሲያጣ ነው፣ አለበለዛ ክርስትያኖች አይደሀዩም አይታመመሙም  የሚለውን ትምህርትስ ደርሳችሁበት ይሆን? የእግዚአብሄርን በረከት በግል ስጋዊ ጥቅም፣ በብርና በምድራዊ ቁሳቁስ ብዛት ብቻ የሚገለጥ፣ በካፒታሊስት ዋና መዲናዋ በአሜሪካ ተወልዶ በአፍሪካ ያደገውን የነ “ወንጌል ተጡዋሪዎች፣ ስራ ጠላቱዎች” ትምህርትስ ለይታችሁ አውቃችሁት ይሆን??ትክክል ገምታችሁዋል። የብልፅግና ወንጌል ይሉታል። እኔ ግን “የብልፅግና ወንጀል” እለዋለሁ።
ስለብልፅግና ወንጌልና እስተምሮ በዚህ ጊዜ መፃፍ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ይህ የወንጀለኞች ዶክትሪን የፕሮቴስታንት ክርዝማቲክ አማኞችን በየአጥቢያ ቤተክርስትያኖቻቸው ከማራቆት አልፎ ዛሬ አገራችንን ለመምራት ቤተመንግስት የተኮፈሱ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድንና ጥቂት ፔንጤቆስጤ የስራ አስፈፃሚዎቻቸውን፣ ይሀው አደገኛ ዶክትሪን፣ ተብትቦ እንደያዛቸው ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ህዝቡ ሃገራችን የገባችበትን አሌ የማይባል እጥፍ ድርብ ሰቆቃ እንዲረዳ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። ስለመሪዎቻችን በተለይም ስለ ጠ/ሚኒስትሩ እንግዳ የሆነ፣ በአለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ የአመራር ክፍተት፣ ፍዘትና፣ ንዝህላልነት ላለፉት ሁለት አመት ከመንፈቅ ፀጉራችንን ስንነጭና ጥርሳችንን ስናፋጭ የቆየን በብዙ ሚሊዮን የምንቆጠር ዜጋዎች፣ መልስ ላጣንበት የአስተዳደር ውድቀታቸው፣ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ይህንን የምናብ እምነት properity Gospel ተንትኖ መረዳትና ማስረዳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን።
አያችሁ ብልፅግና ወንጌልን የሚያምን ወይም የሚከተል ሰው በሃዘን፣ በደህነት፣ በበሽታ፣ በተፈጥሮአዊ መቅሰፍት ሰፈር መገኘት አይፈልግም። ያ ማለት፣ ምርት በአንበጣ ተወሮ ገበሬ ሲያለቅስ ብልፅግና ወንጌልን የሚከተል ሰው የተፈፀመው ውርጂብኝ እንዳልተፈፀመ፣ ቀና ቀናውን በማሰብና (Positive thinking) በእምነት (strong faith) ድልን በማወጅ አንበጣውም ይጠፋል፣ ምርቱም ይተርፋል ነው የሚለው። ጥቃቱም በህዝቡ አለማመን፣ ወይም ህዝቡ በእግዚአብሄር ላይ በደል ፈፅሞ ወይም እምነት ስለጎደለው የተፈጠረ የሰማይ ላይ ቅጣት ነው ብሎ ነው የሚያምነው። ስለዚህም አዘኔታ የለውም፣ ለተጎዳው ህዝብ መራራት አይችልም። ስለዚህ ነው መሪያችን እርጉዝ ሆድዋ ተዘንጥሎ ፅንሱ ሜዳ ላይ ሲጣል፣ ዝንብ የሞተ ያህል እንኩዋን ርህራሄ ያላሳዩት። ለጠ/ሚኒስትሩ ያ ድርጊት አልተፈፀመም ወይም በሰለባዋ እምነት ጉድለትና ሃጢአት የተነሳ የተፈፀመ ስለሆነ ለሳቸው ምንም ማለት አይደለም። በሰለባዋና በእግዚአብሄር መካከል ያለ ነገር ነው ብለው ስለሚያምኑ ህዝብ ያለቅሳል እሳቸው ያፉዋጩብናል።
ጁዌል ኦስቲን የተባለው በአሜሪካን አገር በጣም የታወቀ የብልፅግና ወንጌል ፓስተር በመፅሃፉ “Become a better you” ላይ ያለው አይነት ነው።
“Dwell only on positive, empowering thoughts toward
yourself, “You will see God’s blessings and favor in a
greater way.”
“ሃሳብህን በገንቢ ሃሳቦች ላይ ብቻ አድርግ ያን ጊዜ የእግዚአብሄር በረከትና ሞገስ በህይወትህ በትልቅ መንገድ በሙላትህ ይገለፃል”
ብልፅግና ወንጌልን የሚከተሉ መሪዎች፣ የሌሎችን ችግር ማየት አይችሉም (No Empathy)፣ ችግር፣ በሽታና ደህነት ለእምነታቸው ተስማሚ የድል ትርክት ስለማይፈጥር፣ እያለ እንደሌለ መቁጠርና ጭንቅላታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው በምድር ላይ ያለውን እውነታ መካድ ይቀላቸዋል። እውነታው ግን አንታመምም ቢሉም ይታመማሉ፣ ሃዘንን ቢክዱም ሃዘን ይደርስባቸዋል፣ የተፈጥሮ አደጋን የለም ቢሉም የተፈጥሮ አደጋ ዙሪያቸውን ሲከሰት ያዩታል። ወይ አለበለዛ ዶ/ር አቢይ እንደሚያደርጉት ሃዘን በሰሜን ሲከሰት ወደ ደቡብ መፈርጠጥ፣ ፅንፈኞች ህዝብን ሲያርዱ ወደ ኢሳያስ አፈወርቂ ግዛት ማቅናት፣ በመተከል ከ 300 በላይ አማራዎችና አብረው የተገኙ አገዎችም በመንግስት በተደገፉ ፅንፈኞች ሲጨፈጨፉ ወደ ደቡብ ሄዶ ስለፓርክ ማውራት፣ ወሎ በአንበጣ ሲመታ እሳቸው በአሩሲ የለማ የእርሻ ማሳን መጎብኘት፣ Go kart እየነዱ፣ ኢላማ ተኩስ እየተለማመዱ መዝናናት፣ በጉራ ፈርዳ አማራዎች ሲታረዱ ስለሃዘኑና ጭፍጨፋው ላለማሰብና ላለመመስከር ዝምታን መምረጥ፣ በጠቅላላ አይንን ጨፍኖ አላየሁም ወይም አልሰማሁም ነበር ማለት ሊኖርባቸው ነው። ሌላስ? በጃልሜዳ ለብዙ አመታት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናት ተተተክሎ የነበረን መስቀል በአስተዳደሩ ትእዛዝ ከነበረበት ተነቅሎ አልሰማሁም ነበር ብሎ መሸምጠጥ፣ የቡራዩ ማፈናቀልንም አልሰማምሁም ነበር ማለትን ሊጠይቅ ነው። አልያማ ከለይ የዘረዘርኩዋቸውና ሌሎችም ያልተጠቀሱ በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎችና የተፈጥሮ አደጋዎች በምድራችን በተደጋጋሚ  አይናችን እያየ መከሰታቸውን የሚክድ ፍጥረት ከብልፅግና ወንጌል አማኞች፣ሰባኪዎችና ከ አሮሙማ ፖሊቲክስ  አመራሮቻችን በቀር ማን ይኖራል? በሃገሪቱዋ እንብርት ላይ አየተፈፀሙ ያሉትን ጉዶች አላየሁም ነበር አልሰማሁም ነበር በሚል ፌዘኛ መሪ 110 ሚሊዮን ህዝብ ሲመራ እንግዲህ ከዛ በላይ መቅሰፍትስ አለ እንዴ?  ጠ/ሚኒስትሩ በዋናነት ኢትዮጵያን የኦሮሞ ምድር ለማድረግ ካላቸው አጀንዳ ጋር የብልፅግና ወንጌል እምነት ፅንሰሃሳብ በአስተዳደር ስርአታቸው ገብቶ ታላቁንና የበለፀገውን የኦሮሞ  የምናብ ምድር በቅዠትና በሰመመን እያጣጣሙ ወደፊት መሄድን እንጅ ሃዘንን፣ ድህነትን፣ ሞትን፣ የማሰቢያ ጊዜውም ልቦናም የላቸውም። ስለዚህ ለቅሶ ቤት ከመሄድ ሰርግ ላይ ቢገኙ ይመርጣሉ።የጠ/ሚኒስትሩ ፀጥታን አለማስከበርና፣ የጥቃት ሰለባዎችን በጊዜውና በቦታው ተገኝቶ ችግራቸውን አለመጋራት፣ አለማፅናናት፣ አለመካስና ከሚመጡት ጥቃቶች አለመጠበቅ ምክንያት የብልፅግና ወንጌል እምነታቸው ብቻ ነው የሚል ካለ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ የቀበረ ሰጎን መሆን አለበት። እንዳውም ላስረግጥ የምፈልገው ነገር ከብልፅግናውም ቅዠት ይልቅ የኦሮሙማ አጀንዳቸው፣ አማራን፣ አማርኛንና  ኦርቶዶክስን የማጥፋት እቅዳቸው እጅግ የከፋና እንደሆነ ነው።
አንትያ በትለር (Anthea Butler) የተባሉ የስነመለኮት ፕሮፈሰር ስለፕሮስፔሪቲ ጎስፕል መሪዎች ሲናገሩ “ዶናልድ ትራምፕንና ጆዌል ኦስቲንን ያመሳስሉዋቸዋል። እንደ ፕሮፌሰሩዋ አባባል ሁለቱም ከአማኞች ትልቅ ቅቡልነት ያላቸው ናቸው፣ በስኬታማነትም ያምናሉ፣ ነገርግ ግን በወንጌል ቃል ላይ የተመሰረቱ ወይም የበሰሉ አይደሉም” ይላሉ። ሁለቱም ማለትም ዶናልድ ትራምፕና ጆዌል ኦስቲን እንደማንኛውም የብልፅግና ወንጌል ተከታይ፣ የአሸናፊነትን እንጅ የውድቀትንና የተሸናፊነትን ወሬ መስማት አይፈልጉም። ፕሮፌስሩዋ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ሲያስቀምጡት ታዲያ፣ ትራምፕንና ኦስቲንን የመሰሉ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች የጎርፍና የአውሎ ነፋስ ዜናዎች አይስማሙዋቸውም ምክንያቱም ከብልፅግና ወንጌል ዶክትሪናቸው ጋር የሚስማማ የድልና የፈንጠዝያ ወሬ ስለማያበስር። በዚያም ላይ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች አደጋንና ክፉ ክስተቶችን አደብስብሶና አቃሎ የማቅረብ፣ ሰለባዎች የደረሰባቸውን አደጋና አካላዊ ጉዳት ደግሞ ከግንዛቤ ያለማስገባትና ከጉዳይ ያለመፃፍ ባህሪይ አላቸው ይላሉ። ደግ ደጉን፣ አሸናፊነትን፣ መበልፀግን፣ አዎንታዊ ስነልቦናን (እምነትን) ይዞ ለቅሶና ዋይታ የሌለባትን አሮምያን መገባት።
ልብ ብላችሁዋል? የኛም ጠ/ሚኒስትር አንትያ በትለር (Anthea Butler) የገለፀችው የጆዌል ኦስቲንና የዶናልድ ትራምፕን ጠባይና ተግባርን ኮፒ ነው ሲያሳዩን የኖሩት። የማፅናናት ቃል ከአፋቸው እኮ አይወጣም። በወሎው አንበጣ ወረራ ሰአት እሳቸው Go-kart እየነዱ ኢላማ ተኩስ ጨዋታ እየተጫወቱ ልክ እንደነ ኦባማና እንደ ሌሎች የሰለጠኑና ሃብታም አገር መሪዎች ለመሆን፣ ነገረ አለሙን ረስተው ይቡዋርቁ ነበር። በጣም የሚገርም አይነት መደንዘዝ ይላሉ ያ ነው እንግዲህ። እነኦባማ ቢጫወቱ ያምርባቸዋል። ኦባማ በኤኮኖሚ የተንኮታኮተች አሜሪካንን ከቡሽ ተረክቦ ሌት ከቀን ሰርቶ ሃገሪቱን ከሪሰሽን (Recession) ያወጣ ጀግና መሪ ነው። ቢጫወትም ያምርበታል። የኛ መሪ የተረከቡትን ሃገር ጥለው አንዴ ዱባይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤርትራ የሚዞሩ፣ አገር መምራት አይደለም አንድ የጉራጌ ሱቅ ማስተዳደር የማያውቁ፣ ለካሜራና ለታይታ የሚንቀሳቀሱ፣ በብሄር ተበጣጥቃ የአንድ ብሄር የበላይነት በፈረቃ የሚለዋወጥባትን አገር ለፅንፈኞች አሳልፈው ሰጥተው አገር ሲታመስ እንዳልሰሙና እንዳላዩ የሚሆኑ መሪ ናቸው።
ብልፅግና ወንጌል በቤተክርስትያን
የብልፅግና ወንጌልን አሰራር በቅጡ ለተመለከተ ሰው፣ በውስጡ ያዘለው ትምህርት ህዝብን በባዶ ተስፋና በወሬ፣ ያለውን እምነትና ንብረት የሚያስጥል፣ የመሰሪዎች “ በጨ ጠቆረ” ቁማር እንደሆን በቀላሉ ይረዳል። እንዲያውም የወንጌል አገልግሎት ሳይሆን አይን ያወጣ ዝርፊያ ነው ቢባል ማጋነን እይሆንም። ህዝቡ ያለውን ይሰጣል፣ ወትዋቹ ሰባኪ ግን የብር ፍቅር አስክሮት ጨምሩ በረከቱ በሰጣችሁት መጠን እንዲጨመርላችሁ ይላል።  ብልፅግና ሰባኪው መድረክ ላይ ወጥቶ ህዝቡን ሲደልልና ሲሸጥ የጨረታ ገበያ አይነት ልፍለፋ መለፍለፍ አለበት። የምእመናኑን ልብ ለማባባት፣ ዝሩና አስር እጥፍ ታጭዳላችሁ ይላቸዋል። በኢየሱስ ስም የተለበጠ ወንጀል። በእስር ሊያስቀጣ የሚገባ ወንጀል።
በካፒታሊዝም ስርአት የተለመደው፣ ግለሰቦችን በብዙሃን ላይ በገንዘብና በስልጣን የመቆለል ልምምድ (Individual achivement) የብልፅግና ወንጌል መሰረቱ ነው። ምን ማለቴ ነው? ብልፅግና ወንጌልን በመስበክ ሃብት ያካበቱ እንደነ ክራፍሎ ዶላር፣ እንደ ቲዲ ጄክ፣ እንደነ ኬኔት ኮፕላንድና እንደነጆይስ ማየር አይነቶች በአባሎቻቸው ላይ ያላቸው ተፅእኖ የአሽከርና የጌታ ያህል ነው። የእነኝህ ብልፅግናውያን አገልግሎትና እንቅስቃሴ ዋና የደም ስር የሆነው አባላቸው ደህይቶ፣ እነሱ ስመጥር ባለፀጋዎች ሆነዋል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ የሚንደላቀቁበትን ሃብት የሚሰጣቸውን ህዝባቸውን ራሱን መልሰው ሲንቁትና እንደ ጀሌያቸው ሲቆሩጡት ነው።
የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች ምእመናኑን በእምነት ከጌታ በረከትን እንዲጠብቅ ያስተምሩታል እነሱ ግን “እጅ በእጅ ፍቅር እንዲደረጅ” እንዳለው የሃገሬ ጉራጌ፣ በእምነት ሳይሆን በሚታይና በሚጨበጥ ጥሬ ገንዘብ (cash) ነው የሚደራደሩት። የአባሎቻቸው አስራትና ስጦታ ለሽቶ፣ ለሱፍ፣ ለጫማ፣ ለውድ መኪናዎች፣ ለግል ፕሌኖች፣ ለወርቅ፣ ለብዙ ሚሊዮን ዶላር ቤቶችና ለወፍራም የግል ባንክ አካውንት ነው የሚውለው።
ስለብልፅግና ወንጌል ማንበብ የጀመርኩት ከብዙ አመታት በፊት ነበር። ከ 20 አመታት በፊት አሜሪካ በብልፅጋና ወንጌል ቴሌቪዢን ሰባኪዎች (Televisionpreachers/
Teleevangelists) ቁማርና ወንጀል ታምሳ በነበረበት ጊዜ እኔ እዚሁ አሜሪካ አሁን የምኖርበት ስቴት ነበር የምኖረው። እውቅና የነበራቸው የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች አንድ በአንድ ወደላይ እንደወጡ እንደ ሉሲፈር ወደታች የተወረወሩባቸውን ወቅቶች በደንብ አስታውሳለሁ። ከፀጋ ከወደቁት የዶክትሪኑ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ጂም ቤከር የምእመናንን ገንዘብ ወደግል አካውንት በማዘዋወር ተከሶ ከሚወዳት ሚስቱ ከታሚ ቤከር (ወደ ጌታ ሄዳለች ከብዙ አመታት በፊት) ተለይቶ በ48 አመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበት ወደ እስርቤት ሲላክ ቴሌቪዥን ላይ ተጣብቆ የተከታተለው የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር ቀላል አልነበረም። በሁዋላ ግን የጂም ቤከር ቅጣት በጥሩ ጠባይ ተቀንሶለት ከ 8 አመታት በሁዋላ ተፈታ። ያ ዘመን የብልፅግና ወንጌል ቴሌቪዥን ሰባኪዎች ዙሪያ ገፃቸውን በህዝብ ቁጣ ተከበው የነበረበት ዘመን ነበር። ሌላው ትልቅ የመነጋገሪያ ርእስ የነበረው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ኦራል ሮበርት በ 1987 በህዝብ ፊት፣ በህዝብ መገናኛ ወጥቶ “እግዚአብሄር በአንድ ወር ውስጥ 8 ሚሊዮን ዶላር ካልሰበሰብክ እገድልሃለሁ ብሎኛልና እባካችሁ ገንዘብ ስጡኝና ከሞት አድኑኝ” ብሎ ተናገረ። መቼም የአሜሪካን ህዝብ የዋህም ሩህሩህም ነውና የተባለውን ገንዘብ በተባለው ጊዘ ሰበሰበለት። የሚገርመው ግን ያም በቂ አይደለም ብሎ ሌላ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሰበስቡለት የጠየቀበት ሁኔታ ነበር ያለው። እግዚአብሄር ብር ካላዋጣህ እገድልሃለሁ ብሎኛል ማለቱ በማያምኑ መካከል ሳይቀር መሳለቂያ ነገር ሆኖ ነበር። ከዛም ወዲህ በተለያዩ ወቅቶች የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች እንደነ ቢሾፕ ላንግ (ነፍስ ይማር)፣ ሮበርት ቲልተን፣ ጆዌል ኦስተን፣ ቲዲ ጄክ፣ በኒሂን፣ ክራፍሎ ዶላር፣ ጆይስ ሜየርና ሌሎችም በርካታ ብልፅግናውያን የአገልግታቸውና የእለት እለት እስረሽ ምቺው ህይወታቸው ጉዳይ ለትልቅ ምርመራ (Scrutiny) ተዳርጎ ነበር።
መቼም ምን አለፋችሁ በወንጌል ታሪክ ውስጥ በጴንጤቆስጤና በሌሎችም ክርዝማቲክ ቤተክርስትያናት ውስጥ በተለያየ ወቅት ከተነሱት ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ አንደ ብልፅግና ወንጌል (prosperity Gospel) አማኙን ህዝብ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ የጎዳ ትምህርት የለም። ዛሬም እየተራባ ነው። ብልፅግና ወንጌል የማያሻማ ስርቆት ነው። ስለዚህም ይህ የአጭበርባሪዎች ትምህርት በብዙ መንገድ ቤተክርስትያናት ብቻ ሳይሆኑ መንግስትም ሊከታተለው የሚገባ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከልካይ ስላላገኘ ከአመት ወደ አመት እየሰፋና እያደገ ነው የሄደው። እውነትን ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮችም ጭምር ይህንን ትምህርት በሃገራችን ህዝብ መሃከል የሚዘሩ አጭበርባሪ ሰባኪዎችን ሁሉ በአንድነት እንዲያወግዙም ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ብልፅግና ወንጌል ከየት መጣ እነማን አመጡት?
የብልፅግና ወንጌል ፅንሰሃሳብ የተፈጤረው የእምነት ቃል (Word of faith) ከተባለ ትምህርት ነው። የእምነት ቃል በጭሩ አንድ አማኝ ቀና ቀናውን በማሰብና በእምነት ከፈጣሪ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር በንግግር/በአንደበቱ በመናዘዝ/በመናገር በአእምሮውም ሳይጠራጠር በመቀበል የልቡን መሻት ሊያገኝ ይችላል ብሎ የሚያስተጋባ ሀተታ ነው። ይህ ዱቄት እንኩዋን መያዝ የማይችል ወንፊት ትምህርት/እምነት በአጋጣሚ ከሚሊዮን እንድ ካልሆነ በተቀር የማይፈፀም የቅዠት ነፀብራቅ ነው። የእምነት ቃል (word of faith) በ 20 ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ በክርስማቲክ ጴንጤቆስጤዎች ጎራ የተፈጠረ ትምህርት ሲሆን ትምህርቱ እግሮች አውጥቶ እንዲሮጥ ያደረጉት ወስላታ የእምነት አስተማሪዎችና መሪዎች አሉት። ከነዚያም ውስጥ ኬኔት ሄገን የተባለው ሰው የትምህርቱ አባት በሚባል ይታወቃል። ነገር ግን ከእሱ በፊት የቃለ እምነትን መሰረት የጣለው ፋይነስ ፓርከርስት ኩዋምቢ (Phineas Parkhurst Quimby (1802-1866) የተባለ ሲሆን ፋይነስ ለኬንዮን፣ ኬንዮን ለኬነት ሄገን እንዳስተላለፉት ነው የሚታወቀው። የእምነት ቃል “የሰው እምነት እግዚአብሄርንም ያዘዋል ነው የሚለው። በዛም አባባል “”እምነት” ከእግዚአብሄር ውጭ የሚሰራ ራሱን የቻለ ሃይል ያስመስለዋል። እውነታው ግን ሰው እምነትም ኖሮት የጠየቀውን ወይም የፈለገውን ከእግዚአብሄር ላያገኝ ይችላል። ወይም “የፈልጉትን ሰጣቸው ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ” (መዝሙር 106: 15) እንደሚል አንዳንዴ የፀለይንበትን አግኝተን ነገር ግን ጥቅሙ ሳይሆን ጉዳቱን እናጭዳለን። የ ”ቃለ እምነት” ወይም “የእምነት ቃል” አስተማሪዎች በቃሉ ላይ ከመመስረት ይልቅ እግዚአብሄር በተለየ መንገድ ለእነሱ የሚገልጠው የተለየ የቃለ እምነት መገለጥ አለ እያሉ ነው ህዝብን የሚያጭበረብሩት። መፀሃፍ ቅዱስን የእነሱን አጀንዳ እንዲደግፍ እድርገው በመተርጎም ያው እንደሚታየው በህንፃ ላይ ህንፃ የሚገነቡ ቢሊዮነሮች ሆነው ቁጭ ብለዋል። መፀሃፍ ቅዱስን ቁጭ አድርገው በመገለጥ፣ አየን ወይም ሰማን በሚሉት መሰረት ዬለሽ ቅብጥርጥር ሰውን ይዋሹታል፣ይዘርፉታል፣ ያደሀዩታል፣ ያሞኙታል።
የቃለ እምነት (Word of faith)  በጨረፍታ
1/ሰዎች ትናንሽ እግዚአብሄሮች ናቸው ምክንያቱም ሲፈጥሩ ሙሉ የእግዚአብሄርን ባህሪይ ተሰጥቶአቸዋል ይላል። ሰው በምድርንና በውስጡዋ ባሉት ላይ ትንሹ እግዚአብሄር እንዲሆን እንዲያዝና እንዲገዛ፣ እግዚአብሄር ስልጣኑንና ሃይሉን ሰጠው። እግዚአብሄርን የሰማዩን መንግስት ሲመራ ሰው ደግሞ ምድሪቱን ሊገዛ
ማለት ነው (Capps, Authority in Three Worlds, pp. 16-17).
እውነታው ግን በሰማይም በምድርም አንድ እግዞአብሄር ብቻ ነው ያለው። ሰው መቼም እግዚአብሄር አልነበረም አይሆንምም (ዮሃንስ 17:3)። ከሱ በፊት ከሱ በሁዋላም ሌላ እግዚአብሄር አልተፈጠረም እይፈጠርምም (ኢሳያስ 43 : 10).
2/ እምነት በቃል የሚንቀሳቀስ ሃይል ነው። የሚጨበጥ የሚዳሰስ ያህል ነገራትን የሚያንቀሳቅስ፣ እግዚአብሄርን የሚያዝ ግፊ ነው።
እውነታው ግን እምነት በእግዚአብሄር ቃልኪዳኖች ላይ መታመን ብቻ ነው። (እብራይስጥ 11:1)። እምነት ብቻውን እግዚእብሄርን አያዘውም። እኛ የሰው ልጆች የማናውቃቸው ነገርግን እግዚአብሄር የሚያያቸው፣ የሚያገናዝባቸው ነገሮች ሁሉ ለጠየቅነው ነገር ከእግዚአብሄር ምን አይነት መልስ እንደምናገኝ፣ መቼ እንደምናገኝ ይወስናሉ። እምነት አለኝ ገንዘብ አምጣ የምንለው አምላክ አይደለም የምናመልከው።
ብልፅግና ወንጌል ከቃለ እምነት ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ አንድ ልዩነት ግን አላቸው። ያም ልዩነት የብልፅግና ወንጌል ወሮበላዎች በእምነት ውስጥ ገንዘብን አስተዋወቁ።ለመጀመሪያ ጊዜ  “የእምነትን ቅንጣት ዝሩ” ማለት የጀመረው ከላይ የጠቀስነው ኦራል ሮበርት የተባለው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ነበር። አያችሁ የእምነትን ቅንጣት የምትዘሩት በገንዘብ ነው ማለት ነው። አማኞች ለምን የእምነትን ቅንጣት በእምነት፣ ገንዘብና ወርቅ በሌለበት መዝራት አይችሉም?? ያቺ ለእምነት ቅንጣት የተጠየቀችው ገንዘብ ወደሰባኪዎቹ ኪስ የምትገባ ገንዘብ ናት። ያቺ ገንዘብ ቀላል ገንዘብ አይደለችም። ብዙዎቹን የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች የግል ጄት ባለቤቶች እንዲሆኑ ያደረገች ያቺ የእምነት ቅንጣት (seed of faith)ብር ናት። በአሜሪካን አገር በ”እምነት ቅንጣት” ዝሩ ሳቢያ የናጠጡ የወንጌል ወስላቶች በአሜሪካን አገር በአንድ ወቅት በኮንግረስ ሳይቀር ገቢና ወጪያቸው እንዲመረመር ተደርጎ ነበር።
ብልፅግና ወንጌል ከሌሎች ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ የከፋ ነው ብዬ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው?
የብልፅግና ወንጌል
1ኛ/ የእግዚአብሄርን መለዮና ባህሪይ ደልዞ የሌለውን ባህሪይ የሰጠዋል…!
 
እግዚአብሄርንና ምድራዊ ሃብትን ያዛምዳቸዋል። እግዚአብሄርና ገንዘብ ምን ያገናናቸዋል? ገንዘብ ለሰጡት ገንዘብ የሚሰጥ ላልሰጡት ደግሞ የማይሰጥ? ገንዘብ ከሰጡት ጤንነትንና ስኬትን የሚሰጥ፣ ገንዘብ ካልሰጡት ግን ግድ የሌለው? ለመሆኑ ይህ የእግዚኣብሄር ባህሪይ ነው? አይደለም (ማቴዎስ 19:23-24 ፣ 1 ጢሞቲዎስ 6:10)
2ኛ/ የእምነትን ምንነት፣ በአማኞች ህይወት ውስጥ የሚጫወተውንም ሚና ፍፁም ያጣምመዋል።
የእምነት ቅንጣት (ዘር) ና ገንዘብ ምን አገናኘው? እምነት የእግዚኣብሄር ስጦታ ነው። እምነት ሰው ከእግዚኣብሄር ጋር የሚዋሃድበት መለኮታዊ ልምምድ ነው። በገንዘብ አይገኝም። በገንዘብ አይሸጥም፣ በገንዘብ አይለወጥም (ኤፌሶን 2:8)
3ኛ/ በደህነት የሚማቅቁንና በበሽታ የጎሰቆሎ ሰዎችን ኢላማ ያደርጋል።
ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ወንጌል ዋና መራቢያ ቦታ አፍሪካ ሆኖአል።በኢትዮጵያም በግልፅ ይህንን የሌብነት ወንጌል እየሰበኩ ህዝቡን የሚሰርቁ ሰባኪዎች አሉ። እነሱን በህብረት ማውገዝ ይገባል። ያላችሁን ሙዋጣችሁ ከሰጣችሁ ሃብታም ትሆናላችሁ፣ ጤና ትሆናላችሁ ፣ በሚል የቀረቻቸውን ቤሳና በእግዚኣብሄርም ላይ ያላቸውን እምነት ይነጥቃቸዋል።
4ኛ/ ብልፅግና ወንጌል የሚያበለፅገው ሰባኪውን ወይም መጋቢውንና የእርሱ ፍርፋሪ  ለቃቃሚዎች የሆኑትን ኣጃቢዎቹን ብቻ ነው።
ህዝቡ ግን ያለውን ለመጋቢው ወይም ለሰባኪው ሰጥቶ ላም አለኝ በሰማይ እናዳለ በባዶ ተስፋ አይኑን እንዳፈጠጠ ይቀራል።
5ኛ/ ህዝቡ ያለውን እያሙዋጠጠ ከሰጠ በሁዋላስ:-
 በሰባኪው የተነገረው የሰማይ ብርና ወርቅ ሲዘገይና ሳይከሰት ሲቀር፣ ጮሌው ሰባኪ መልሶ እምነት ስለጎደለህ ነው፣ ሃጢትህን ስላልተናዘዝክ ነው ከእግዚኣብሄር ገንዘብ ወይም ጤንነት ያላገኘሀው ወይም ያላገኘሽው ብሎ  ጥፋቱን በተዘረፈው (ችዋ) ደሃ ይላክካል።
ይህም አሰራር ዋሾው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ (ዘራፊ) የእኔ ጥፋት አይደለም ብሎ እንዲያሳብብ ቀዳዳ ከመስጠቱም በላይ ተዘራፊዎቹ የደረሰባቸውን ጥቃት በራሳችን ጥፋት ነው ብለው እንዲቀበሉና ወደ ህግም እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል። የጥቃት ጥቃት።
6ኛ/ እግዚአብሄርን በፎርሙላ ማንቀሳቀስ ይቻላል ይላል:-
ልክ እንደ ሂሳብ ትምህርት የተደነገጉ የአሰራር ፎርሙላዎችን ለተከተለ ሁልጊዜ ወደተጠበቀው ውጤት እንደሚወስድ ሁሉ የብልፅግና ወንጌል ትምህርትም አንድ ሰው እምነት ካለውና ይሆንልኛል ብሎ እስካመነና በቃሉም እስከተናዘዘ ድረስ ወይም በአእምሮው የጠየቀውን ነገር ሲቀበል ማየት ከቻለ የጠየቀው ነገር ከእግዚአብሄር የሰጠዋል ይላል። ይህ ደግሞ ፍፁም ውሸት ነው። የእግዚአብሄር ምላሽ አወንታ ወይም አሉታ የሚሆንበት ምክንያት ሁልጊዜ ለሰዎች አይታወቅም። እግዚአብሄር ስራው በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ናቸው። እምነትም ኖሮን፣ በቃላችንና በስነልቦናችንም ተናዘን የጠየቅነው ነገር ላይሰጠን ይችላል። ወይም ገንዘብ ጠይቀን ጤንነት እንቀበል ይሆናል። እግዚአብሄር በፎርሙላ አይሰራም። ማንም አያዘውም።
አገራችን
የአገራችንን ምስኪን ህዝብ የሚግጡ የብልፅግናና የቃል እምነት (word of faith) ሰባኪዎች ደሃውን ህዝብ ሃብታም ትሆናለህ፣ ከበሽታህ በእምነት ትፈወሳለህ፣ ደህነት አይነካህም ከእንግዲህ እያሉ በጋጡት ገንዘብ ሚሊየነሮች ሆነዋል። እንዳንዶቹ ከየክልሉ ሌሎቹም ከዛው ከአዲስ አበባ የተጠራቀሙ የኢየሱስን ስም የሚሸቅጡ ነውረኞችና ዘራፊዎች ከፍተኛ ድጋፍ ከዚህ ከወንበዴ መንግስት ስላገኙ ያለምንም ፍራቻ ወንጀላቸውን እየፈፀሙ ነው።ዶ/ር አቢይ አህመድ የወንጀለኞች ሹዋሚ ጠ/ሚኒስትር ቤተመንግስታቸው ድረስ ከሚጋብዙዋቸው ውስጥ የቃል እምነቶችና የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ አጭበርባሪዎች ይገኙበታል። እንዲያውም እነኝህ ዘራፊዎችና ጤናማ ወንጌል ሰባኪዎች ይቅር ተባብለው አንድ ማህበር እንዲጠጡ ባዘዙት መሰረት ከጥቂቶች በተቀር ካውንስል መስርተው በአንድ ተቁዋዳሽ ሆነዋል። ጤነኛዎቹ ተብለው ይከበሩ የነበሩ ሰባኪዎችና መጋቢዎች፣ ሃሰተኛ ነቢያትንና ሃዋሪያትን (እነሱው ናቸው ብልፅግናና ቃል እምነትን የሚሰብኩት) አቅፈው ስመው “ድሮም እኮ ልዩነታችን ጥቃቅን ነበር” “ስራቸውን እንጅ እነሱን አልጠላም” የሚሉ ሰበቦችን እያዥጎደጎዱ በአንድ ላይ “በካውንስሉ” ስም ይሰራሉ። ጤናማ ዘማሪዎችና ሰባኪዎችም በካውንስሉ ስብሰባዎች እየተገኙ ፕሮግራማቸውን ያደምቁላቸዋ። ዛሬ “ሰው ትንሹ እግዚአብሄር ነው” የሚሉ ወሮበላዎች እድሜ ለጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ከርቸሌ መጋዝ ሲኖርባቸው ምላሳቸውን እያወጡ ያላግጡብናል። ባለዲዛይነር ሱፎች ናቸው። ከየት አመጡት ገንዘቡን አይሰሩ አይነግዱ? ከምስኪን ደሃዎች፣ ከህመምተኞች፣ እምነተ ለጋዎች ኪስ ነው የሰበሰቡት።
መንግስቱም ወስላታ
መሪውም የማይታመን
ሰባኪውም ኪስ አውላቂ የሆነባት አገር እግዚኦ  !!!!!!!!!!!!!!
ይህ ሴይጣናዊ ትምህርት በአሜርካም ሆነ በአፍሪካ እንደ ሰደድ እሳት የተሰራጨው በኢኮኖሚ በተጎዱት ህብረተሰቦች መካከል ነው። ምክንያቱም ግልፅ ነው። ደሃ ከደህነቱ የሚያላቅቀው ነገር አለ ከተባለ የትም ይሄዳል። ምንም ያድርግ ?። ህዝብ ሞኝ ስለሆነ ሳይሆን ቢጨንቀው ነው ብልፅግና ብልፅግና የሚሉትን ሰባኪዎች የሚከተለው። የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች አፍሪካ ድረስ ዘልቀው ታዋቂ መጋቢዎችን እየተጠቀሙ በቀን ከአንድ ዶላር በታች ከሚያገኘው ህዝብ ሳንቲም ይቃረጣሉ። የዚህ ስህተተኛ ትምህርት አዛማቾች በቀጣዩ አለም በእግዚኣብሄር ዘንድ የሚጠየቁ ቢሆንም በምድር ደግሞ ብዙ ጥፋት ሳያጠፉ በፍርድቤትና በዳኞች ፊት ሊቀርቡ የሚገባው ነው። እውነትን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ሊያወግዛቸው ይገባል።
Filed in: Amharic